የዓለም ባንክ ኢትዮጵያን ጨምሮ የበረሀ አንበጣ ወረርሽኝ ለበረታባቸው የአፍሪካ እና የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት የ500 ሚሊዮን ዶላር ዕርዳታ እና ብድር አጸደቀ። ዛሬ ሐሙስ ግንቦት 13፤ 2012 በዓለም ባንክ ሥራ አስፈፃሚ ዳይሬክተሮች የጸደቀው አስቸኳይ የአንበጣ መከላከያ ፕሮግራም ለደሀ እና ተጋላጭ ገበሬዎች፣ አርብቶ አደሮች እንዲሁም የገጠር ነዋሪዎች ፈጣን ዕርዳታ ለመስጠት የታለመ ነው።
በመርሐ ግብሩ የመጀመሪያ ዙር ለኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ፣ ኬንያ እና ዩጋንዳ 160 ሚሊዮን ዶላር እንደሚሰጥ ባንኩ ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ለኢትዮጵያ ባንኩ የመደበው 63 ሚሊዮን ዶላር ከአንበጣ ቅኝት እና መቆጣጠር ሥራ በተጨማሪ ከ150,000 በላይ የሚሆኑ ገበሬዎች በመጪው ክረምት ዘር እና ማዳበሪያ ለማቅረብ፤ ከ113,000 በላይ ለሚሆኑ አርብቶ አደሮች የቤት እንስሳት መኖ ለማዘጋጀት ይውላል።
ጎረቤታሞቹ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በ25 አመታት ታሪካቸው አይተውት የማያውቁት የአንበጣ መንጋ እንደገጠማቸው የተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት ከሰሞኑ አስታውቆ ነበር። የመሰረተ ልማት እጦት እና የኮሮና ወረርሽኝን ለመግታት ሥራ ላይ በዋሉ ክልከላዎች ሳቢያ የአንበጣ መንጋን ለመግታት የሚደረገው ጥረት አስቸጋሪ ሆኗል።
የዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት ዴቪድ ማልፓስ “የአንበጣ መንጋ ከኮሮና ወረርሽኝ ግብግብ ለገጠሙ አገሮች ተጨማሪ ፈተና ሆኗል” ሲሉ ተናግረዋል። ባንኩ የአንበጣ መንጋን በተቀናጀ ከፍተኛ እርምጃ መቆጣጠር ካልተቻለ በአፍሪካ ቀንድ አገራት እንዲሁም በየመን 8.5 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ኪሳራ ሊያስከትል እንደሚችል ሥጋቱን ገልጿል።
አንድ ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የአንበጣ መንጋ እስከ 40 ሚሊዮን አንበጦችን ይይዛል። ይህ አይነቱ የአንበጣ መንጋ 35 ሺህ ሰዎች ሊመግብ የሚችል ሰብል በአንድ ቀን የማውደም አቅም ጭምር አለው። አማካኝ የሚባል የአንበጣ መንጋ ደግሞ የ2,500 ሰዎችን የአመት ቀለብ ሊያጠፋ እንደሚችል ጥናቶች ያሳያሉ።
በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት መረጃ መሠረት እስከ ባለፈው ታህሳስ ወር ብቻ አንበጣ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ ከ70 ሺህ ሔክታር በላይ የእርሻ ማሳ አውድሟል። በኢትዮጵያ እና በኬንያ ባለፉት ወራት የታየው የአንበጣ መንጋ በመጪው ክረምት ሊከፋ እንደሚችል ተሰግቷል።
የዓለም ባንክ ዛሬ ካጸደቀው 500 ሚሊዮን ዶላር ዕርዳታ ውስጥ ኬንያ 43 ሚሊዮን ዶላር ድርሻ ይደርሳታል። ሌላኛዋ የምስራቅ አፍሪካ ሀገር ኡጋንዳ ደግሞ 48 ሚሊዮን ዶላር የዕርዳታ ገንዘብ ታገኛለች። በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እየታመሰች የምትገኘው ጅቡቲ ብርቱ ጉዳት እያደረሰባት ላለው የአንበጣ ወረርሽኝ መቋቋሚያ ስድስት ሚሊዮን ዶላር እንደሚሰጣት ባንኩ አስታውቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)