የሶማሌ ክልል ምክር ቤት ስብሰባ አፈ ጉባኤ ሳይመርጥ ተጠናቀቀ

ትላንት የጀመረውን አስቸኳይ ጉባኤ ዛሬ ያጠናቀቀው የሶማሌ ክልል ምክር ቤት ኃላፊነታቸውን በለቀቁት አፈ ጉባኤ ምትክ አዲስ ሰው ሳይመርጥ ቀረ። ምክር ቤቱ በዛሬው የአርብ ግንቦት 14፤ 2012 ውሎው የቀድሞውን አፈ ጉባኤ ጨምሮ የአራት የቢሮ ኃላፊዎችን ሹመት አጽድቋል።

የክልሉን ምክር ቤት በአፈ ጉባኤነት የመምራት ኃላፊነት በመስከረም 2011 የተረከቡት አቶ አብዲ መሐመድ ከስራቸው መልቀቃቸውን ያሳወቁት ከአንድ ወር በፊት ነበር። የአፈ ጉባኤው የስራ መልቀቂያ በክልሉ ምክር ቤት ከመጽደቁ በፊት በክልሉ የማዕድን እና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊነት እንደተሾሙ መነገሩ በክልሉ ፖለቲከኞች ዘንድ ውዝግብ ቀስቅሶ ከርሟል። 

ትላንት ሐሙስ ግንቦት 13፤ 2012 ለአስቸኳይ ስብሰባ በተቀመጠው የሶማሌ ክልል ምክር ቤትም የስራ መልቀቂያው በአጀንዳነት ተይዞ ነበር። አፈ ጉባኤው “ተገቢውን አካሄድ ባልተከተለ መልኩ ለቢሮ ኃላፊነት መሾም አልነበረባቸውም” ያሉ የምክር ቤት አባላት ተቃውሟቸውን በይፋ አቅርበዋል። ተጨማሪ የልዩነት ሀሳቦች ያነሱት እነዚህ የምክር ቤት አባላት ስብሰባ ረግጠው እስከ መውጣት ቢጓዙም የአቶ አብዲን መልቀቂያም ሆነ አዲስ ሹመት ማስቀረት አልቻሉም። 

የአፈ ጉባኤው የስራ መልቀቂያ በትላንቱ ስብሰባ መጽደቁን የሶማሌ ክልል መንግስት የኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ ሂቦ አህመድ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ሆኖም እርሳቸውን የሚተኩ ዕጩዎች በዛሬውም ሆነ በትላንትናው ስብሰባ አለመቅረባቸውን ገልጸዋል። “ፓርቲው ወደፊት ዕጩ አቀርባለሁ ብሏል” ሲሉም አክለዋል። የትላንቱንም ሆነ የዛሬውን ስብሰባ የመሩት የምክር ቤቱ ምክትል አፈ-ጉባኤ ወ/ሮ ፍርደውሳ መሐመድ ናቸው።  

ምክር ቤቱ በዛሬው ውሎው የክልሉን የማዕድን እና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊነት እንዲመሩ የተመደቡትን የቀድሞውን አፈ ጉባኤ ሹመት አጽድቋል። እንደ እርሳቸው ሁሉ ሶስት አዳዲስ የቢሮ ኃላፊዎችም ሹመታቸው ጸድቆ በምክር ቤቱ አባላት ፊት ቃለ መሃላ ፈጽመዋል። 

ሹመታቸው ከጸደቀላቸው ውስጥ የክልሉን የጸጥታ ቢሮ እንዲመሩ ከአንድ ወር በፊት የተመደቡት ዶ/ር ሁሴን አብዱላሂ ቃሲም ይገኙበታል። ዶ/ር ሁሴን ወደ ቦታው የመጡት ባለፈው መጋቢት ወር በሶማሌ ክልል የተከሰተውን የፖለቲካ አለመረጋጋት ተከትሎ ከክልሉ የጸጥታ ቢሮ ኃላፊነት ስልጣናቸው እንዲነሱ የተደረጉትን አቶ አብዲ አዲልን ተክተው ነው። 

የክልሉ የኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ የነበሩት አቶ ሃቢብ መሐመድ ከዚሁ ክስተት ጋር በተያያዘ ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ይታወሳል። በእርሳቸው ምትክ የተሾሙት የአቶ አሊ በደል እና የፐብሊክ ሰርቪስ ቢሮ ኃላፊነትን የተረከቡት የአቶ አብዲቃድር ረሺድ ሹመት በዛሬው የምክር ቤት ስብሰባ ጸድቋል። (በተስፋለም ወልደየስ – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር/ ፎቶ- የሶማሌ ክልል መንግስት የኮሚዩኒኬሽን ቢሮ)