ትግራይ እንዴት ሰነበተች? – (ክፍል 1)

የፈዘዘችው እና ያኮረፈችው መቐለ

በተስፋለም ወልደየስ

ወደ መቐለ ለመጓዝ ወደ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ እየሄድኩ ነው። ወደ ከተማይቱ በየዕለቱ ይደረግ የነበረው የአውሮፕላን በረራ እንደገና ከተጀመረ ገና ሶስተኛ ቀኑ ነው። ታህሳስ 17፤ 2013። ለአምስት ሰዓት በረራ፤ በአራት ሰዓት ላይ ቀድሜ እንድገኝ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ የሽያጭ ሰራተኛ በተነገረኝ መሰረት፤ በሰዓቱ በአውሮፕላን ማረፊያው ተገኝቻለሁ። 

በሞባይል አማካኝነት በኦንላይን የተገዛው የአውሮፕላን ትኬት፤ ወደ ከተማይቱ የሚያደርሰኝ (One-way ticket) ብቻ ነው። ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት በተመዘገበው ቁጥሩ ከፍ ያለ መንገደኛ ምክንያት፤ እኔ በፈልግሁባቸው ተከታታይ ቀናት የመመለሻ ትኬት ማግኘት ባለመቻሌ ነው፤ በሌጣ ትኬት መወሰኔ። የመመለሻው ነገር “እዛው ስደርስ ይታሰብበታል” በሚል እሳቤ ነበር ጉዞውን ለማድረግ የቆረጥሁት።

በእርግጥ ከዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ሌላም ምክንያት ነበረኝ። በትግራይ ክልል ከነበረው ውጊያ ጋር በተያያዘም ሆነ ከዚያ ቀደም ብሎ፤ በርካታ ሰዎች ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ለመመለስ መገደዳቸውን በማስረጃ ጭምር ተመልክቼ ስለነበር፤ የእኔም ዕጣ ፈንታ እንደዚያ ሊሆን ይችላል የሚል ጥርጣሬ ነበረኝ። ምን ያህል ቀናት እንደሚያቆየኝ ለማላውቀው ጉዞ የተሰናዳሁት እንግዲህ እንዲህ በግማሽ ልብ ሆኜ ነው። 

ዘገባውን በድምጽ ለማድመጥ ከላይ ያለውን የዩቲዩብ የድምጽ ማዕቀፍ ይጫኑ

በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ እንደደረስን፤ ለጫነኝ የ“ራይድ” ታክሲ አሽከርካሪ፤ የሀገር ውስጥ በረራ ሲስተናገድበት ወደማውቀው “ተርሚናል” መኪናውን እንዲያዞር ምልክት ሰጠሁት። እንደታዘዘው ሊያደርግ የሞከረው ሹፌር፤ መግቢያውን በሚጠብቁ የፌደራል ፖሊሶች ከርቀት በምልክት “ክልክል” መሆኑ ተነገረው። ዙሪያውን ስናጠያይቅ “ሁሉም በረራዎች የሚስተናገዱት በዓለም አቀፍ ተርሚናል ነው” ተባልን። ወደዚያው ተጣደፍን። 

ፓስፖርቴን እና ሞባይሌን አስቀድሜ፣ አነስተኛ ሻንጣዬን እየጎተትኩ ወደ መግቢያው ተጠጋሁ። የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት መስሪያ ቤት የደንብ ልብስ የለበሰ አንድ ግለሰብ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኛ ጎን ለጎን ቆመው የተጓዦችን መታወቂያ እና የአውሮፕላን ትኬት እየተመለከቱ ወደ ውስጥ ያሳልፋሉ። መንገደኞች ሰልፍ ይዘዋል። ለእኔ የአየር መንገዱ ሰራተኛ ደረሰኝ። ወዴት እንደምጓዝ ጠየቀኝ። ነገርኩት። ፓስፖርቴን እና በሞባይሌ የተዘረዘረውን የበረራ መረጃ ተመልክቶ አሳለፈኝ። 

ወደ ተርሚናሉ እንደተገባ ያለውን የመጀመሪያ ፍተሻ ያለምንም ችግር ከጨረስኩ በኋላ፤ ራስን ችሎ “ቼክ ኢን” ማድረግ ወደምታስችለው አነስተኛ ኪዮስክ አመራሁ። የተጠየቅኋቸውን መረጃዎች ለኪዩስኳ ኮምፒውተር ከመገብኩ በኋላ፤ ወደ መቐለ መጓዝ የሚያስችለኝን የወረቀት ትኬት አቀበለችኝ። አሁን ጉዞዬ እውን ወደ መሆኑ የተቃረበ መሰለ። እንዲያም ሆኖ ግን አውሮፕላኑ ተነስቶ በአዲስ አበባ አየር ላይ እስኪንሳፈፍ ድረስ ወደ ከተማይቱ መጓዜን እርግጠኛ አልነበርኩም። ከዚህ ቀደም አውሮፕላን ውስጥ ከገቡ በኋላ እንዲወርዱ ተደርገው፤ ከመንገዳቸው የተስተጓጉሉ ሰዎች እንዳሉ የሰማ ሰው እርግጠኛ ባይሆን ይፈረድበታልን?  

የሀገር ውስጥ በረራ “ተርሚናል” የት እንደሆነ በቀስት የሚያሳየውን ምልክት ተከትዬ ወደፊት ገስገስኩ። ሁለተኛውን ፍተሻ አልፌ፣ የመንገደኞች የመጠበቂያ ቦታ ላይ የበረራ ሰዓት እስኪደርስ፣ በድምጽ ማጉያ የሚተላለፈውን እየሰማሁ ጠበቅሁ። የጎንደር እና የጅማ መንገደኞች ተጠርተው ተሳፈሩ። በስተመጨረሻ የመቐለ ስም ተጠራ። በርከት ያሉ መንገደኞች ወደ በሩ አመሩ። የጠበቅሁት “ማነህ? ወዴት ነህ?” የሚሉ ጥያቄዎች እስካሁን ባለመከሰታቸው እየተገረምኩ ወደ አውሮፕላን የሚወስደን አውቶብስ ላይ ተሳፈርኩ። 

አውቶብሳችን እስኪሞላ ባለው ጊዜ መንገደኞችን ማስተዋል ጀመርኩ። ወጣቶች ይበዙበታል። ከፊት ለፊቴ የተቀመጠው ወጣት፤ አጠገቡ ላለው ሰው የጉዞውን ምክንያት ሲያስረዳ፤ “ሚስቴ መድኃኒት አልቆባት ነው” ሲል ሰማሁት። “ያው ካሽም ችግር ስላለ እኔ ከዚህ መውሰድ አለብኝ” በማለት በቤተሰቦቹ ላይ የደረሰውን ችግር እያጫወተው እያለ ስልክ ተደወለለት። ወጣቱ የሰዎችን ስም እያነሳ ደህና መሆናቸውን ካጠያየቀ በኋላ፤ የእርሱም ሚስት አክሱም ከተማ መሆኗን እና ወደዚያ መጓዝ አስቸጋሪ መሆኑን መስማቱን ለደዋዩ ሲነግረው ሀዘን በተጫነው ስሜት ነበር።  

ይህን እየሰማን አውቶብሳችን ተንቀሳቀሰች። ከጥቂት አፍታ በኋላ ካናዳ ሰራሽ ከሆነችው ቦምባርዲየር Q400 ከተሰኘችው አውሮፕላን ፊት ስትደርስ ቆመች። መንገደኞች ከወረድን በኋላ በሁለት መስመር እንድንሰለፍ ተደረገ። ልክ ተርሚናሉ መግቢያ ላይ እንዳጋጠመን ሁሉ፤ እዚህም የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት መስሪያ ቤት የደንብ ልብስ የለበሰ ግለሰብ ቆሞ የመንገደኞችን መታወቂያ እየተመለከተ ወደ አውሮፕላኗ እንድንገባ ይፈቅዳል። የኮሮና መከላከያ ማስክ ያደረጉትን ዝቅ አድረገው ፊታቸውን እንዲያሳዩ ያደርጋል።

ተራዬ ደርሶ ፓስፖርቴን ሰጠሁ። ፎቶዬን እና እኔን ካነጻጸረ በኋላ ለምን እንደምሄድ ጠየቀኝ። “የፈራሁት ደረሰ” አልኩ ለራሴ። ምክንያቴን ከነገርኩት በኋላ እንዳልፍ ፈቅዶልኝ ወደ አውሮፕላኑ ገባሁ። በአጋጣሚ ከፊት ከነበሩት ወንበሮች ነበር የደረሰኝ። ያ ደግሞ ገቢ፤ ወጪውን ለመመልከት ምቹ ዕድል ፈጠረልኝ። በሁለት አውቶብስ የመጣነው ሰዎች ተጠናቅቀን ገብተን፤ ቀሪ መንገደኞችን መጠበቅ ያዝን። 

ጥቂት ቆየት ብሎ አዲሶቹ መንገደኞች መግባት ጀመሩ። ቦታ ቦታቸውን እየያዙ እያለ፤ ቀደም ሲል መታወቂያችንን የተመለከተ የደህንነት መስሪያ ቤቱ ሰራተኛ በድንገት መጣና የአንደኛውን ጎልማሳ መንገደኛ መታወቂያ ጠየቀው። መታወቂያውን አይቶ ለመንገደኛው መለሰለት። የደህንነቱ ሰው ከአውሮፕላኑ ከወረደ በኋላ እንደገና ተመልሶ መጣና ከእኔ ትይዩ የተቀመጡ ሁለት ሸምገል ያሉ ሰዎችን መታወቂያቸውን ጠየቃቸው። 

የሰጡትን እየተመለከተ እያለ ስልክ ተደወለለት። ትንሽ ከተነጋገረ በኋላ “ደብዳቤ እንደያዙ ልጠይቃቸው?” ሲል ሰማሁት። ከዚያም አከታትሎ “ደብዳቤ ይዛችኋል?” አላቸው። በመስኮት በኩል የተቀመጡት መንገደኛ ማህተም ያለበት ደብዳቤ አውጥተው አቀበሉት። የደህንነት መሥሪያ ቤቱ ባልደረባ “አብራችሁ ናችሁ?” በማለት ሁለቱን መንገደኞች በድጋሚ ጠየቃቸው። በጋራ የአዎንታ ምላሽ ሰጡት። ይሄኔ ደብዳቤውን ይዞ፣ ስልኩን እያወራ ወረደ። ከጥቂት ደቂቃዎች ቆይታ በኋላ ደብዳቤውን ይዞ በመመለስ ለሁለቱም “መልካም በረራ” ሲል ምኞቱን በመግለጽ ሲሰናበታቸው አየሁ። 

ከዚህ ሁነት በኋላ ብዙም አልቆየን። አንድ ሰዓት ከአምስት ደቂቃ የሚፈጀውን በረራ ለመጀመር አውሮፕላኗ መንደርደሪያው ላይ መሮጥ ጀመረች። ከደቂቃዎች በኋላ ራሴን አዲስ አበባ ሰማይ ላይ አገኘሁት። አሁን እርግጠኛ ሆንኩ። ባለፉት ሁለት ወራት ብዙ የተባለላትን መቐለን ልመለከት ነው። ከጉዞዬ በፊት ስለ ከተማይቱ የሰማሁኋቸውን ነገሮች እያወጠነጠንኩ እና የያዝኩትን የቅዳሜ መጽሔት እያገላበጥኩ በራራውን ፉት አልኩት። 

* * *       

አውሮፕላናችን ከቀኑ ስድስት ሰዓት ከሩብ ገደማ ወደ መቐለ አሉላ አባ ነጋ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ለመውረድ ማንዣበብ ጀመረች። ይሄኔ መስኮት አጠገብ ከተቀመጠችው መንገደኛ አሻግሬ ከተማይቱን ከአየር ላይ ለመመልከት ሞከርኩ። በውጊያው ምክንያት የደረሰ፣ የሚታይ ጉልህ ነገር ይኖር እንደው ለማየት የቻልኩትን ያህል ዙሪያ ገባውን ቃኘሁ። ሁኔታዬን ያስተዋለችው መንገደኛ ለከተማይቱ እንግዳ መሆኔን ጠየቀችኝ። 

ወደ መቐለ ስጓዝ የመጀመሪያዬ አይደለም። ለመጨረሻ ጊዜ የጎበኘኋት ባለፈው ዓመት የካቲት ለስራ ጉዳይ ብቅ ባልኩበት ወቅት ነበር። በቀደሙ ጉዞዎቼ የማውቃትን ከተማ፣ ከሰሞኑ በቴሌቪዥን ሳያት ከከረምኩት እና በእርግጥም በእውን በመሬት ላይ ካለው ሁኔታ ጋር ማነጻጸር፤ የዛሬ እና የመጪዎቹ ቀናት አንዱ ስራዬ መሆኑን እያሰላሰልኩ ከአውሮፕላን ወረድኩ።

ተጓዦች፤ ያንጠለጠሉትን ነገር ተሸክመው፤ ከአውሮፕላኑ እስከ መንገደኞች ማስተናገጃ ህንጻው ድረስ ያለውን ርቀት ፈጠን ፈጠን ባለ እርምጃ ተያይዘውታል።። የናፈቋቸውን ቤተሰቦች ለማየት የጓጉ ይመስላሉ። ወደ መንገደኞች መግቢያ በር ስቃረብ፤ እኒያ ከአዲስ አበባ ከመነሳታችን በፊት በደህንነቱ ሰው ደብዳቤ የተጠየቁ ሁለት ሰዎች፤ ከሌላ ሰው ጋር በመሆን እያወጉ በተለየ በር ሲገቡ ተመለከትኩ። “አዲሶቹ የክልሉ ባለስልጣናት ይሆኑ እንዴ?” – ምላሽ ባላገኝም ለራሴ ጥያቄ አቀረብኩ። 

ወደ መንገደኞች ማስተናገጃ ህንጻ ስገባ ጭር ብሏል። ከእኔ የቀደሙ መንገደኞች ሻንጣዎቻቸውን ኮልኩለው ዙሪያ ገባውን ይመለከታሉ። አንዳንዶች በሞባይላቸው ይነጋገራሉ። የተወሰኑት መጻዳጃ ቤት በየት በኩል እንደሆነ መውጪያው ላይ የቆመውን የፌደራል ፖሊስ አባል ይጠይቃሉ። መንገደኞች መምጣታቸውን የተመለከቱ አራት ጫኝ እና አውራጆች፤ ሻንጣ ተጭኖ የሚገፋበትን ተሽከርካሪ ይዘው ሲመጡ አልፊያቸው ወደ ውጭ ወጣሁ። 

ውጪውም እንደ ውስጡ ጭር ብሏል። በመኪና ማቆሚያ ቦታው ላይ የተለመዱት ቢጫ ቀለም ያላቸው የኤርፖርት ታክሲዎችም ሆኑ ሌሎች ተሽከርካሪዎች የሉም። በአካባቢው ቆሞ ያገኘሁትን አንድ ወጣት መኪና የት አገኝ እንደው ጠየቅሁት። ታክሲዎች ከግቢ ውጪ እንዳሉ ጠቆመኝ።

በእርግጥም ከአየር ማረፊያው መግቢያ አጠገብ ወደ 20 የሚሆኑ መኪኖች በተርታ ተሰልፈው ይታያሉ። መንገደኞቹን የሚጠብቁ ሹፌሮች እና ሌሎች በርከት ያሉ ሰዎችም መንገዱን ሞልተውታል። ገቢ ወጪውን በጥብቅ የሚከታተሉ እና የሚያነጋግሩ የመከላከያ ሰራዊት አባላትን አልፌ ከሰው ጋር ተቀላቀልኩ። ታክሲ ስጠይቅ፤ ተረኛውን ሹፌር አመላከቱኝ። ሹፌሩ ሻንጣዬን ተቀብሎ እየጫነ ታክሲው አጠገብ ከቆሙ ሴቶች ጋር ይነጋገራል። 

“ምን ፈልገው ነው?” አልኩት። “የኤርፖርት ሰራተኞች ናቸው። ወደ ከተማ መሄድ ፈልገው መኪና አጥተው ነው” አለኝ። “ምን ችግር አለው ታዲያ! ጫናቸው!” ብዬ ጋቢና እርሱ አጠገብ ተቀመጥኩ። ሁለቱ ሴቶች ምስጋናቸውን እያዥጎደጎዱ ከኋላ ተደላደሉ። ታክሲዋ አፍንጫዋን ወደ መቐለ ስታቀና ትግርኛ እና አማርኛ ቋንቋ የቀላቀለ ጨዋታ ተጀመረ። “እንዴት ከረማችሁ?” ጥያቄ ተከተለ። 

የመከላከያ ሰራዊት መቐለን ከመቆጣጠሩ በፊት በከተማይቱ ሲያንዣብቡ ስለከረሙት ጀቶች፣ ዙሪያውን ሲሰሙ ስለቆዩ የከባድ መሳሪያ ድብደባዎች ሶስቱም እየተቀባበሉ እየነገሩኝ እያለ የፍተሻ ኬላ ላይ በመድረሳችን ጨዋታችን ቆመ። “የኤርፖርት ትኬት አለህ?”- የታክሲው ሹፌር ጠየቀኝ። አገልግሎቱን ቢጨርስም የበረራ ትኬቴን በጥንቃቄ መያዜ በጀኝ።    

በየመኪናዎቹ ያሉ ተሳፋሪዎችን እያስወረዱ ከሚፈትሹ ወታደሮች ለአንዱ የአውሮፕላን ትኬቴን አሳየሁ። ትኬቴን እና ፓስፖርቴን መልከት አድርጎ አካላቴን ከፈተሸኝ በኋላ ወደ ታክሲው ጋቢና ተመለስኩ። ሁለቱ የአየር ማረፊያ ሰራተኞች ግን በፈተሸቻቸው ሴት ወታደር ተጨማሪ መታወቂያ መጠየቃቸው አልተመቻቸውም። የመስሪያ ቤታቸውን መታወቂያ ሲያሳዩዋት “ሌላ መታወቂያ የለም?” ስትል እንደጠየቀቻቸው አንስተው፤ ነገሩን ለአፍታ የመነጋገሪያ አጀንዳ አደረጉት።

በመንገዳችን ላይ የማየው ተሽከርካሪ ቁጥር ቢያንስብኝ የታክሲውን ሹፌር “መኪና የለም እንዴ?” ስል ጠየቅሁት። በከተማይቱ የነዳጅ እጥረት በመኖሩ ምክንያት እና አብዛኞቹ የነዳጅ ማደያዎችም ስላልተከፈቱ መኪናዎች መቆማቸውን ነገረኝ። ነዳጅ ቢኖር እንኳ ባንክ ቤቶች አገልግሎት መስጠት ባለመጀመራቸው የገንዘብ ችግር እንዳለም አከለልኝ። 

“ገንዘብ ታዲያ ከየት ነው የምታገኙት?” በድጋሚ ጠየቅሁ። “በቃ! ከሰው ከሰው እንበደራለን። ትንሽ ትንሽ እንቅስቃሴም ስላለ ከዚያም እናገኛለን” ሲል ምላሽ ሰጠ። በኋላ ወንበር ከተቀመጡት የኤርፖርት ሰራተኞች አንዷ፤ ባለፉት ሁለት ቀናት የተጀመረ ገንዘብ የማግኛ ሌላ ዘዴ እንዳለ አስታወሰችው። ሹፌሩም ቀበል አድርጎ “ከአዲስ አበባ ገንዘብ ያመጡልናል። ትላንት በአውሮፕላን ሲመጡ ይዘውልን መጥተዋል” በማለት የሴትዬዋን ንግግር አጠናከረ። 

አንዳንዶች የኤ.ቲ.ኤም ካርዳቸውን አዲስ አበባ ልከው ገንዘብ እንደሚያወጡም አንስተው፤ ሁኔታው በዚሁ ከቀጠለ እነርሱም ተመሳሳይ ዘዴ ተጠቅመው ገንዘብ ሊያስመጡ እንደሚችሉ ነገሩኝ። የጀመርነውን የገንዘብ ጉዳይ ሳንቋጭ፣ በአምስት ደቂቃ ልዩነት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ለፍተሻ ቆምን። ፍተሻው ወደ መቐለ በሚገቡት ላይ ብቻ ሳይሆን፤ መነሻቸውን ከከተማ አድርገው ወደ አየር ማረፊያ አቅጣጫ በሚሄዱት ላይ ጭምር የሚካሄድ ነው። ከአየር ማረፊያው ተቀብሎ ከተማ ሊያደርሰኝ ቃል ገብቶ የነበረው የጓደኛዬ ጓደኛ፤ በዚህ መሰል ፍተሻ በመማረሩ ምክንያት ነበር እኔ ራሴ ኮንትራት ታክሲ ለመጠቀም የተገደድኩት። ሳይደግስ አይጣላም” እንደሚባለው፤ አጋጣሚው “ሳንሱር ያልተደረገውን” የሶስት የከተማይቱ ነዋሪዎችን አስተያየት፣ ያለምንም ማሽሞንሞን፣ በቀጥታ ከአንደበታቸው ለማድመጥ አስችሎኛል።       

ከፍተሻ መልስ ከሁለቱ እንስቶች እና ከሹፌሩ ጋር የሰሞኑ አክራሞታቸውን የተመለከተው ጨዋታችን ቀጠለ። በምግብ ሸቀጦች አቅርቦት በኩል በመቐለ ያለው ሁኔታ ከሌሎቹ የትግራይ አካባቢዎች የተሻለ እንደሆነ ሁለቱ ሴቶች አጫወቱኝ። “እዚህ አንድ ወር ነው የተቸገርነው። እዚህ ተሻሽሏል ደህና ነው። ሌላ ሀገር ግን መብራት ስለሌለ ይቸገሩ ይሆናል” አለች አንደኛዋ። ለዚህም በምሳሌነት አዲግራት እና ሽረን አነሳች። የታክሲው ሹፌር በበኩሉ “ችግር ያለው በረሃ በረሃውን ነው” አለ። ሶስቱም ከመቐለ ውጪ ያለውን ሁኔታ ሲገልጹ አሳሳቢ እና አስጊ አድርገው ነው። 

ወደ አዲግራት አቅጣጫ ትራንስፖርት መጀመሩን ያነሳው ሹፌሩ ወደዚያ ለመሄድ እንዳላስብ መከረኝ። ሁለቱ እንስቶችም ሀሳቡን ደገፉት። “መሃል መሃል ላይ ውጊያ አለ። የሽምቅ ውጊያ ነው። ወደዚያ ተቀይሯል” አለ ሹፌሩ። አንደኛዋ ሴት በሀገረ ሰላም ዘመዶች እንዳሏት እና የእህቷ ባለቤት እንደተገደለባት አንስታ “ከባድ ነው በጣም” ስትል ያለውን ሁኔታ ልታስረዳኝ ሞከረች። “ሻዕቢያ እኮ አልተቻለም!” አለ ሹፌሩ ከግድያው ጀርባ ያሉት የኤርትራ ወታደሮች መሆኑን በሚያመለክት አኳኋን። 

የኤርትራ ወታደሮች አሁንም በትግራይ ክልል የተለያዩ ቦታዎች ስለመኖራቸው፣ ስለፈጸሟቸው ግድያዎች እና ዘረፋዎች ሶስቱም ያዩት እና የሰሙትን እያጣቀሱ ገለጹልኝ። አንደኛዋ ሴት የመቐለ የጸጥታ ሁኔታ አሁንም አሳሳቢ እንደሆነ፣ ቀን በቀን ዘረፋ እንደሚፈጸም እና እኔም መጠንቀቅ እንዳለብኝ አሳሰበችኝ። ሌላኛዋ ተደርባ “ከአስራ ሁለት ሰዓት በኋላ አታምሽ” አለችኝ። ለምን እንደዚያ እንዳሉኝ ስጠይቅ ሹፌሩ “አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇልኮ። አይመሽም። ካመሸህ በጥይት ነው የምትመታው” ሲል ተጨማሪ ማስጠንቀቂያ ሰጠኝ። 

*    *    *

ወደ መቐለ ከተማ ስንገባ ከሁሉ ነገር መጀመሪያ ልብ ያልኩት፤ የከተማይቱን መንገዶች ያጨናንቁ የነበሩት በተለምዶ ባጃጅ ተብለው የሚጠሩ ባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪዎች ለአይን መናፈቃቸውን ነው። በመንገዱ ላይ በአብዛኛው የሚታዩት የግል መኪናዎች እና ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ናቸው። ቀኑ ቅዳሜ፤ ሰዓቱ ተሲዓት ላይ ቢሆንም እምብዛም የሰዎች እንቅስቃሴ አይታይም። 

ከአየር ማረፊያ ያሳፈረኝ ታክሲ ከከተማይቱ ሁነኛ ቦታዎች አንዱ በሆነው አክሱም ሆቴል አጠገብ አውርዶኝ፤ ሁለቱን የኤርፖርት ሰራተኞች ይዞ ጉዞውን ወደ ከተማ ቀጠለ። በአየር ማረፊያ ሊቀበለኝ የነበረው ሰው፤ በአካባቢው ጉዳይ እንዳለው ነግሮኝ ስለነበር እርሱን ለመጠበቅ ከሆቴሉ ፊት ለፊት ካሉ “ኮፊ ሃውሶች” ወደ አንዱ አመራሁ።

የመቐለ ድምቀት የሆኑት ኮፊ ሃውሶች እና ወጣቶች የጠበቀ ቁርኝት አላቸው። በእነዚህ ቦታዎች በርካታ ወጣቶች ተሰባስበው ሲጫወቱ መመልከት የዘወትር ትዕይንት ነው። በመስመር በተደረደሩት ኮፊ ሃውሶች በረንዳ ላይ የሚታዩ ወጣቶች ቁጥር ከተለምዶው ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ የሚባል ነው። ከአንደኛው “ኮፊ ሃውስ” በረንዳ ላይ ቁጭ ብዬ ዙሪያ ገባውን ማስተዋል ጀመርኩ። 

አንዳንዶቹ ወጣቶች ዞር እያሉ ሲያስተውሉኝ “ምናልባት በአማርኛ በስልክ ስነጋገር ሰምተው ተጠራጠረውኝ ይሆን?” ስል ራሴን ጠየቅሁ። ካለሁበት ኮፊ ሀውስ ውስጠኛ ክፍል የሚወጣው የብዙአየሁ ደምሴ የአማርኛ ዘፈን ደግሞ ለጥርጣሬዬ ብዙም ቦታ እንዳልሰጠው አደረገኝ። ነገሩ የገባኝ ዘግይቶ ነው። ለካስ ከአዲስ አበባ ጀምሮ ያደረግሁትን የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል (ማስክ) ባለማወልቄ ከሰው ሁሉ ተለይቼ እንድታይ አድርጎኛል ኖሯል። ዙሪያዬን ያሉትም ሆነ፤ ከሆቴሉ የሚገቡ እና የሚወጡ አንዳቸውም ሰዎች “ማስክ” አላደረጉም። 

ከአየር ማረፊያ ጀምሮ እዚህ እስክንደርስ ድረስ የነበረውን ጊዜ መልሼ ሳጠነጥንም ያለው ተመሳሳይ ነገር እንደነበር አስታወስኩ። የውጊያ እና የጦርነት ሁነቶችን ሲያዩ እና ሲሰሙ ለከረሙ የመቐለ ነዋሪዎች፤ የኮሮና ወረርሽኝም ሆነ በማስክ የመከላከል ጉዳይ፤ ቅድሚያ የሚሰጠው ነገር እንዳልሆነ ተገንዘብኩ። “በ’ሮም እስካለህ ሮማውያን የሚያደርጉትን አድርግ” እንደሚባለው የፊት መሸፈኛዬን ጠቅልዬ ወደ ጃኬት ኪሴ አስገባሁና ወደ ትዝብቴ ተመለስኩ።

በኮፊ ሀውሱ በረንዳ በቆየሁበት አንድ ሰዓት በሚጠጋ ጊዜ በተደጋጋሚ የተመለከትሁት ነገር ከተማይቱ ምን ያህል በወታደሮች ቁጥጥር ስር እንዳለች ነው። መሳሪያቸውን በተጠንቀቅ የደገኑ ወታደሮች ያሳፈሩ ፒክ አፖች እና በርካታ ፍራሽ የጫኑ ወታደራዊ የጭነት መኪናዎች አሁንም አሁንም በመንገዱ ላይ ይመላለሳሉ። ከመደበኛ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በተጨማሪ፤ ቀይ ኮፍያ ለባሽ ወታደሮች በመኪናዎች ተጭነው ይወጣሉ፤ ይወርዳሉ። አፈሙዙ ወደ መሬት የተዘቀዘቀን መሳሪያ፣ በቃታው የያዙ እግረኛ ወታደሮችም አንድም፤ ሁለትም እየሆኑ ላይ ታች ይላሉ።  

ከወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ሌላ በመንገዱ በብዛት የሚታዩት የየተቋማቸውን ባንዲራ እያወለበለቡ የሚጓዙ መኪኖች ናቸው። ገሚሶቹ መኪኖች፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የተለያዩ መስሪያ ቤቶች እና የእርዳታ ድርጅቶች የሚጠቀሙባቸው መሆኑን ከባንዲራቸው መለየት ይቻላል። የዓለም የምግብ ድርጅት (FAO)፣ የተመድ የስደተኞች መርጃ ድርጅት (UNHCR)፣ ቀይ መስቀል፣ ድንበር የለሽ የሃኪሞች ቡድን (MSF)፣ ማህበረ ረድኤት ትግራይ (ማረት) በምሳሌነት ይጠቀሳሉ። ሌሎቹ በባንዲራቸው የሚለዩ መኪናዎች ደግሞ የመንግስት ተቋማት ናቸው። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ኢትዮ-ቴሌኮም በዚህኛው ምድብ ውስጥ ይካተታሉ። 

እኒህን መሰል ጉዳዩች እየታዘብኩ ከኮፊ ሀውሱ የሚለቀቁ የአማርኛ እና ትግርኛ ሙዚቃዎች ቅልቅል ግብዣዎችን እሰማለሁ። “ኢትዮጵያ” የተሰኘው የጸሐዬ ዮሃንስ ዜማ “ሰላም አይለየን” ከሚለው አዝማቹ ጋር ሲመጣ የሁኔታው ግጥምጥሞሽ አስገርሞኝ ዙሪያዬን አየሁ። ማንም ልብ ያለው የለም። ጥቂት ቆየት ብሎ የአለማየሁ እሸቴ “አልተለየሽኝም” ቀጠለ። አለማየሁ በዚህ የፍቅር ዘፈኑ “ነበረችኝ” ስለሚላት ፍቅሩ፣ ስለ “መለየት መርዶ” እና ስለ“ሐዘን በረዶነት” እያነሳ ይብሰከሰካል። ግጥሞቹን ከወቅታዊ ሁኔታ ጋር ለማዛመድ እየሞከርሁ ተቀባዬን መጠበቄን ቀጥያለሁ። 

በዚህ ሀሳብ ውስጥ እያለሁ ሶስት ሰዎች ከአክሱም ሆቴል አቅጣጫ ወደ ኮፊ ሀውሱ ሲመጡ ተመለከትሁ። አንደኛውን ጎልማሳ የማውቀው መሰለኝ። ትኩር ብዬ ስመለከት በእርግጥም እርሱ ነው። በትግራይ የተቃዋሚ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ ስማቸው በጉልህ ከሚጠሩ ሰዎች አንዱ ነው። የአረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ለሉዓላዊነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሆኖ በሰራባቸው ዓመታት፤ የትግራይ ክልልን ሲያስተዳድሩ ከቆዩት የሕወሓት አመራሮች ጋር አይን እና ናጫ ሆኖ ነው የቆየው። 

“ታሰረ፣ ተፈታ፣ ተዋከበ፣ ከጥቂት ሰዎች ጋር ሆኖ በመቐለ ሰላማዊ ሰልፍ ወጣ” የሚሉ የመገናኛ ብዙሃን ዘገባዎች ስለ እርሱ ብዙ አውርተዋል። አዎ! ራሱ ነው። አምዶም ገብረስላሴ። በአካል ባያውቀኝም በስልክ ቃለ መጠይቆች ሰጥቶኝ ያውቃል። “ሰላም ልበለው ወይስ ይቅርብኝ” እያልኩ ሳመነታ፤ አብረውት ካሉ ሰዎች ጋር ወደ ኮፊ ሀውሱ ውስጠኛ ክፍል ዘለቀ። ብዙም ሳይቆይ፤ ተቀባዬ የከተማይቱ ነዋሪ ጉዳዩን ጨርሶ ወደ እኔ መጣ። ወደ መኪናው እየገባሁ የአምዶምን ጉዳይ አነሳሁለት። ደስተኛ ባልሆነ ድምጽ እርሱም ሆነ ሌሎች የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ተሿሚዎች ከዚህ አካባቢ እንደማይጠፉ አረጋገጠልኝ። 

በጊዜያዊ አስተዳደር አማካኝነት የክልሉን ቢሮዎች እንዲመሩ ከተሾሙ ግለሰቦች ዝርዝር ውስጥ የአምዶምን ስም አለማየቴን አስታውሼ፤ በየትኛው የኃላፊነት ቦታ እንደተሾመ ጠየቅሁ። አስተናጋጄ አሁንም ቀዝቀዝ ባለ ድምጽ፤ የአረናው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የክልሉ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ምክትል ኃላፊ ተደርጎ መሾሙን አስረዳኝ። አረናን በሊቀመንበርነት የሚመራው አብርሃ ደስታም እንዲሁ በጊዜያዊ አስተዳደሩ የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ሆኖ መሾሙን በማንሳት፤ እንዲህ በህዝብ ዘንድ እውቅና ያላቸው አመራሮች መሾማቸው፤ በእርሱም ሆነ በህዝቡ ዘንድ የፈጠረውን ስሜት ጠየቅሁት። 

አስተናጋጄ፤ ሁለቱ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችም ሆነ ሌሎች ተሿሚዎች “የብልጽግና ፓርቲ ጉዳይ አስፈጻሚ ናቸው” የሚል እምነት አለው። የብልጽግና ፓርቲ ደግሞ በትግራይ ስላልተመረጠ በክልሉ ጉዳይ “እጁን ማስገባት አይችልም” ባይ ነው። “የትግራይ ህዝብ መተዳደር ያለበት በመረጣቸው ሰዎች ብቻ መሆን አለበት” የሚለው አመለካከት፤ በአብዛኛው ህዝብ ዘንድ የሚንጸባረቅ እንደሆነም ያስረዳል። ይህን መሰሉን የፖለቲካ ወሬ እየሰለቅን የመቐለን ዋና ዋና ጎዳናዎች ማቆራረጥ ያዝን። 

ሰዓቱ ከቀኑ ስምንት ሰዓት ገደማ ቢሆንም በመንገዱ ዳር የማያቸው አብዛኞቹ የንግድ መደብሮች ዝግ መሆናቸው ገርሞኝ ጠየቅሁ። ለአንድ ወር ገደማ በከተማይቱ ያለው ሁነት ከዚህ ያልተለየ መሆኑን አስረዳኝ። እርሱ ከመምጣቱ በፊት የደውልኩላቸው ሌሎች ነዋሪዎች፤ ብዙዎቹ ሆቴሎች ዝግ መሆናቸውን እንደነገሩኝ ገልጬ፤ ማረፊያ የት ማግኘት እንደምችል እንዲያመላክተኝ ጠየቅሁት። ከተማ መሃል ያሉ እና እርሱ የሚያውቃቸው ሆቴሎችን ለመሞከር ተሰማምተን መኪናዋን ወደዚያው አሽከረከራት።

ገና ትላንት በድጋሚ ስራ መጀመሩ የተነገረን፣ የተሻለ የሚባለው ሆቴል፣ ያለበት የጽዳትም ሆነ የአያያዝ ሁኔታ፣ እንኳ ለአዳር ለአይን የሚማርክ አልነበረም። አስተናጋጄ “ከተማ መሃል ሆቴል መያዝ” የሚለውን ሀሳቤን መቀየር እንዳለብኝ ነግሮኝ፤ ወጣ ብሎ ወደሚገኘውና “አዲ ሃውሲ” ወደተሰኘው የከተማይቱ ክፍል ይዞኝ ሄደ። በእዚህ አካባቢ ከአንድም ሁለት ሆቴሎች ተከፍተው ስራ ጀምረዋል። አንደኛው ሆቴል እንደውም በፌደራል ፖሊሶች ጭምር የሚጠበቅ ነው። ለማረፍ የመረጥኩት ሆቴል ወደ ስራ የተመለሰው ወደ መቐለ የአውሮፕላን በረራ መጀመሩን ተከትሎ እንደሆነ ሰራተኞቹ ነገሩኝ።    

*    *    *

“አዲ ሃውሲ” የተሰኘው አካባቢ በተለምዶ ለአዲስ አበባው ቦሌ የሚሰጠውን ደረጃ የያዘ ነው። በአካባቢው ያሉት አብዛኞቹ ቤቶች “ግራውንድ ፕላስ ዋን” እና ከዚያ በላይ የሆኑ ዘመናዊ መኖሪያዎች ናቸው። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መስሪያ ቤቶች እና የተለያዩ የእርዳታ ድርጅቶች፤ ቅርንጫፍ ቢሮዎቻቸውን የከፈቱት በዚህ ነው። 

በመቐለ ሰማይ ላይ ጄቶች በሚያንዣብቡባቸው እና የከባድ መሳሪያ ድብደባ በተከታታይ በሚሰማባቸው ቀናት፤ የተወሰኑ የከተማይቱ ነዋሪዎች ወደዚህ አካባቢ ለመጠለል መጥተው እንደነበር ሰማሁ። አንድም “በአካባቢው ዓለም አቀፍ ተቋማት የሚበዙ በመሆኑ ለጥቃት አይጋለጠም” በሚል ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ጥቃት ቢፈጸም እንኳ በፎቆቹ ቤቶች ምድር ቤት በመጠለል ራስን ከአደጋ ለመጠበቅ በማሰብ ነው ተባልኩ። ይህንኑ እውነታ፤ በዚያው አካባቢ ወደሚገኘው ቤቱ ለምሳ ግብዣ እየወሰደኝ የነበረው አስተናጋጄም አረጋግጦልኛል።

ወደ አስተናጋጄ ቤት መታጠፊያ ጋር ስንደርስ ወደ ውስጥ የሚያስገባው የውስጥ ለውስጥ መንገድ በውሃ ማስተላለፊያ ትልልቅ ቱቦዎች ተዘግቶ ተመለከትኩ። አስተናጋጄ ቀለል አድርጎ ይህ የሆነበትን ምክንያት ያብራራልኝ ገባ። መንገዶቹ በቱቦዎቹ የተዘጉት በአካባቢው ነዋሪዎች እንደሆነ እና ያም የተደረገው መቐለ በመከላከያ ሰራዊት ቁጥጥር ስር ስትውል፤ “የሻዕቢያ ወታደሮች ለዝርፊያ ተሰማርተዋል” የሚል ወሬ በከተማይቱ በመናፈሱ፤ እርሱን ለመከላከል በሚል ተጀምሮ፤ በዚያው መቀጠሉን አጫወተኝ። ያን ቀን የከተማይቱ ነዋሪ ፤ ዋና ዋና መንገዶችንም ጭምር በድንጋይ ዘግቶ መዋሉን አከለልኝ። 

በመቐለ በአሁኑ ወቅት የኤርትራ ወታደሮች ባይኖሩም የመከላከያ ሰራዊት አባላት በየቤቱ እየገቡ ፍተሻ እንደሚያደርጉ ነገረኝ። ትላንትና እንኳ የሌተናል ጄነራል ታደሰ ወረደ ቤት ተፈትሾ “ብዙ ዕቃዎች መውሰዳቸውን ሰምቼያለሁ” አለ። በአካባቢው ያሉ ነዋሪዎች “ዕቃ አልተወሰደም” ብለው እንዲፈርሙ መገደዳቸውንም ጭምር መስማቱንም ገለጸልኝ። ከቀናት በፊት በእሱ ቤት አቅራቢያ በሚገኘው የአባይ ጸሐዬ ቤት ተመሳሳይ ፍተሻ መደረጉን፤ ነገር ግን ምንም ነገር አለመገኘቱን በተጨማሪ ምሳሌነት ጠቀሰልኝ። 

ከዚሁ ጋር ተያያዞ በከተማይቱ ስላለው የጸጥታ ጉዳይ ተነሳ። በከተማይቱ የነበረው የጸጥታ መዋቅር ሙሉ በሙሉ ከስራ ውጪ በመሆኑ፤ ለዘራፊዎች ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን አስተናጋጄ አስረዳኝ። በመቐለ የቀን ተቀን ዝርፊያ በተደጋጋሚ እንደሚፈጸም እና ፖሊሶች ስለሌሉ፤ ነዋሪው ለማን አቤት ማለት እንዳለበት እንኳ ለማወቅ እንደተቸገረ አብራራልኝ። እርሱ እና ጎረቤቶቹ ዘራፊ ሲመጣ በፊሽካ ድምጽ ማስጠንቀቂያ እንደሚሰጣጡም ነገረኝ። 

አስተናጋጄ ምሳ እስኪደርስ ይህን መሰሉን መረጃ እያካፈለኝ ቆየ። በተከፈተው ቴሌቪዥን፤ የትግራይ ሚዲያ ሃውስ (TMH) ስርጭት ይተላለፋል። የትግርኛ የትግል ዘፈኖችን እያከታተለ የሚያሳየው የቴሌቪዥን ጣቢያ በየመሃሉ አዳዲስ መረጃዎችን ያቀርባል። የጣቢያው የዜና ሰዓት ሲደርስ የጀመርነው ጨዋታ ተቋርጦ ሁሉም አይኑን በቴሌቪዥን መስኮት ላይ ተከለ። 

ዜና አንባቢው ጫን ባለ ድምጽ በትግራይ ክልል ስላለው ሁኔታ እንዲሁም በውጭ ሀገር ስለተካሄዱ የተቃውሞ እና የሀዘን መግለጫ ሰልፎች እያከታተለ ሲያቀርብ ሁሉም በጥሞና ይከታተላል። የአዋቂዎቹን ጥሞና ያልተረዱት የቤቱ ህጻናት በመሃል ጨዋታ ጀመሩ። የሚባለው ነገር እንዳያመልጠው የፈለገው አስተናጋጄ ልጁን ዝም እንዲል ተቆጣው። 

TMH የቴሌቪዥን ጣቢያ በትግራይ ዋነኛ የመረጃ ምንጭ እየሆነ መምጣቱን ሰምቼ ነበር። በተከራየሁበት ሆቴል ክፍል ያለውን የሳተላይት ቴሌቪዥን ዝርዝር ስከፍት በመጀመሪያው ረድፍ ላይ ተቀምጦ ያየሁት ይህንኑ ቴሌቪዥን ጣቢያ ነው። ላለፉት ሁለት ወራት የኢንተርኔት አገልግሎት የተቋረጠባቸው የመቐለ እና በክልሉ ሌሎች ከተሞች ያሉ ነዋሪዎች፤ በ“ኦንላይን” ላይ የሚባል፣ የሚጻፈውን መልሰው የመመልከት ዕድል ያገኙት በዚህ ጣቢያ አማካኝነት እንደሆነ ሲገልጹ ሰምቻለሁ። 

በእርግጥም ጣቢያው ፌስቡክን በመሳሰሉ ማህበራዊ ድረገጾች የሚሰራጩ መረጃዎችን እና በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን የሚቀርቡ ትግራይ ነክ ጉዳዩችን፤ መርጦ እና በራሱ ቅኝት አስተካክሎ ሲያስተላልፍ ታዝቤያለሁ። ከTMH ሌላ የኤርትራ መንግስት ተቃዋሚ የሆነው “አሰና” የተሰኘው የቴሌቪዥን ጣቢያም እንዲሁ ብዙ ተመልካች እንዳለው አረጋግጪያለሁ።

ሰዓቱ ወደ 11 ሰዓት ሲጠጋ በጊዜ ወደ ቤት ስለመግባት መወራት ጀመረ። አስተናጋጄ መኪናውን አቁሞ በእግር ሊሸኘኝ መሰናዳት ያዘ። ባለቤቱ ሁኔታው አላማራትም። ስጋት በተጫነው ድምጽ 12 ሰዓት ከመድረሱ አስቀድሞ ወደ ቤት እንዲመለስ ደጋግማ አስጠነቀቀችው። የባለቤቱን ያህል የሰጋው አስተናጋጄም ወደ ሆቴሌ የሚወስደኝ ዋና መንገድ ላይ ካደረሰኝ በኋላ ወደ ቤቱ ተመለሰ። 

ሰዓቴን ስመለከት 11:28 ይላል። በርከት ያሉ ሰዎች በመንገድ ዳር ባሉ ኮፊ ሃውሶች በቡድን፣ በቡድን ሰብሰብ ብለው ተቀምጠው ማውጋታቸውን ቀጥለዋል። ወደ ሆቴሌ እየተመለስኩ ከታክሲ ተጠቃሚው ይልቅ እግረኛው እንደሚበዛ አስተዋልኩ። ሰዓት እላፊው ሲደርስ ያለውን ሁኔታ ለመታዘብ ከሆቴሌ አጠገብ ባለ ኮፊ ሃውስ በረንዳ ላይ ተቀመጥኩ። ለ12 ሰዓት አስር ደቂቃ ሲቀረው የኮፊ ሃውሷ አስተናጋጅ አጠገቤ ያሉትን ወንበሮች መሰብሰብ ጀመረች። እኔ እና አጠገቤ የተቀመጠ በሃያዎቹ ውስጥ ያለ ወጣት ብቻ ቀረን። 

ሰዓቱ አስራ ሁለት ሰዓት ቢሞላም መኪናዎች አሁንም አላቆሙም። ባጃጆች ይመላለሳሉ። ለአካባቢው እንግዳ መሆኔን ያስተዋለው ወጣት ሰዓት እላፊው በቅርቡ እስከ አንድ ሰዓት መራዘሙን ነገረኝ። አብዛኛው የከተማው ነዋሪ ግን፤ ቀደም ሲል በነበረው የጊዜ ገደብ፤ አስራ ሁለት ሰዓት ሳይደርስ ከቤቱ እንደሚከተት አወራኝ። ሰዓት እላፊውን ተላልፎ የቆየ በጥይት የመመታት እጣ ፈንታ እንደሚገጥመው በሚኖርበት አካባቢ ያያቸውን ምሳሌዎች እያጣቀሰ አስረዳኝ። 

ከቀናት በፊት በዚሁ ሰፈር አካባቢ የሚኖር፤ የአእምሮ ችግር ያለበት ወጣት ከለሊቱ ስድስት ሰዓት በኋላ ወጥቶ መንገድ ላይ ሲዞር በጥይት ተመትቶ ሆስፒታል መግባቱን በሀዘን ተውጦ አጫወተኝ። ህግ መከበር ቢኖርበትም በወታደሮች እየተወሰዱ ያሉ እንዲህ አይነት እርምጃዎች ግን ተገቢ አለመሆናቸውን በአጽንኦት አነሳልኝ። ተጨዋች እና ከሰው ጋር በቀላሉ ተግባቢ ከሆነው ከዚህ ወጣት ጋር በሌላ ጊዜ ለመገናኘት ስልክ ተለዋውጠን ተሰነባበትን። ኮፊ ሃውሱም የመጨረሻ ተስተናጋጆቹን አሰናብቶ ተዘጋ።

ከምሽቱ አንድ ሰዓት እንኳ ሳይሞላ ከሆቴል ክፍል መግባቴን አልወደድኩትም። በሆቴሉ ሎቢ ተቀምጬ ከሆቴሉ እንግዳ ተቀባይ ጋር ስለ ከተማይቱ ሁኔታ እና ስለ ሰዓት እላፊው ማውራት ጀመርኩ። ከሆቴሉ አቅራቢያ፤ በር ተዘግቶ ከውስጥ የሚመሽበት መጠጥ ቤት እንዳለ ስሰማ ወደዚያው ለመሄድ ተነሳሁ። “ሆድ ያባውን ብቅል ያወጣዋል” ሆኖ በእንዲህ አይነት ቤቶች የልባቸውን የሚናገሩ ሰዎች አይጠፉም። እርሱን መመልከቱ በከተማይቱ ስላለው ስሜት ተጨማሪ ማሳያ እንደሚሆነኝ በማሰብ፤ በሩ ገርበብ የተደረገውን መጠጥ ቤት ከፍቼ ገባሁ። 

በቀይ ደብዛዛ ብርሃን የደመቀው መጠጥ ቤት በሰው ተሞልቷል። ክፍት ወደሆነው ጥግ ቦታ ሄጄ ተቀመጥኩ። ሙዚቃው፣ ጨዋታው ደርቷል። መቐለን ከረገጥኩ ጀምሮ ሲነገረኝ እና ሳየው የነበረው ስጋት እና ፍርሃት እዚህ ያለ አይመስልም። ብዙዎቹ ተስተናጋጆች በቤቱ ውስጥ ረዘም ላለ ጊዜ መቆየታቸውን ከፊታቸው ከተደረደረው የቢራ ጠርሙስ ብዛት ተነስቶ መገመት ይቻላል። 

አጠገቤ ያለው ጠረጴዛን የከበቡ ወጣቶች ሞቅ ብሏቸዋል። የሌተናል ጄነራል ባጫ ደበሌን ስም እያነሱ ይበሻሸቃሉ። የመከላከያ ሰራዊት መቐለን ከመቆጣጠሩ ጥቂት ቀናት በፊት “ባጫ ተያዘ” በሚል በከተማይቱ ለደቂቃዎች የቆየ፣ በተኩስ የታጀበ የደስታ መግለጫ ሲካሄድ እንደነበር ሲወራ ሰምቼያለሁ። በዚህ ምክንያት ይሁን በሌላ፤ ወጣቶቹ የጄነራሉን ስም በተደጋጋሚ እያነሱ ይሳለቃሉ። በየመሃሉም ጥቂት የኦሮምኛ ቃላትን ይወረውራሉ። የጃምቦ ጆቴ የኦሮምኛ ዘፈን ሲመጣ ግን “ይቀየርልን” ባይ ሆኑ። የትግርኛ ዘፈኖች ቀጠሉ። 

በቤቱ ውስጥ ያለው አብዛኛው ወሬ ፖለቲካ ነው። እዚህኛው ጠረጴዛ የተጀመረ ጨዋታ፤ እዚያኛው ላይ ይቀጥላል። በዚህ አይነት የተጀመረ ንግግር ሳይታሰብ ወደ እሰጥ አገባ እና ትንቅንቅ አደገ። በአንደኛው ጠረጴዛ ካሉ ወጣቶች አንዱ ደጋግሞ “ደርግ፤ አምሃራይ” ይላል። ውዝግቡ በምን ምክንያት እንደተቀሰቀሰ ባይገባኝም አጠገቤ ባለው ጠረጴዛ ላይ ያለውን አንድ ወጣት አስቆጥቶታል። 

አንድ፣ ሁለት በመባባል የተጀመረው ውዝግብ ወደ ጸብ ማደግ ሲጀምር፤ የቤቱ ባለቤት የሆነች ወጣት ሴት መጥታ “ቶሎ እንድወጣ” መከረችኝ። ሰዓቴን ስመለከት 1:50 ይላል። በዚህ የሰዓት እላፊ ጊዜ፤ በአካባቢው የሚዘዋወሩ ወታደሮች፤ ጸቡን ሰምተው ወደ መጠጥ ቤቱ ቢገቡ የሚፈጠረውን ገምቼ ለመውጣት ተጣደፍኩ። 

ወደ ውጪ ስወጣ ጨልሟል። አንድም መኪና በመንገድ አይታይም። ዙሪያ ገባው ጸጥ ረጭ ብሏል። ሁኔታው እኩለ ለሊት ያለፈ አስመስሎታል። ቀን ላይ ያገኛኋቸው ሰዎች ስለ ምሽት የከተማይቱ ሁኔታ በፍርሃት ያጫወቱኝን አስታወስኩ። በአካባቢው አንድም ወታደር አለመኖሩን እያስተዋልሁ በደቂቃዎች ውስጥ ሆቴሌ ደረስኩ። ወደ ሆቴል ስገባ የምሽት ተረኞች የደንበኞቻችውን ትዕዛዝ በማስተናገድ ተጠምደዋል። ውጪ ወጥቶ መመገብም ሆነ ቢራ መጎንጨት ያልቻለ ሁሉ፤ በሆቴሉ ተወስኖ ትዕዛዙን ያዥጎደጉዳል። 

ወደ ክፍሌ አቅንቼ ወደ ፎቁ በረንዳ ወጣሁ። ምሽቱ ቀዝቃዛ የሚባል ነው። በኃይል የሚነፍሰው ንፋስ የዛፎቹን ቅርንጫፎች በተደጋጋሚ ያስጎነብሳቸዋል፤ በሆቴሉ ፊት የተደረደሩ ባንዲራዎችን ያስረግዳቸዋል። ለአስር ደቂቃ ገደማ በጸጥታ የተዋጠችውን ከተማ እያየሁ ቆየሁ። ብርዱ ሲጸናብኝ ወደ ክፍሌ ተመልሼ ወደ አልጋዬ አመራሁ። ሰዓቱ ገና ሶስት እንኳ አልሞላም ነበር።      

(ክፍል ሁለትን ለማንበብ ይህን ሊንክ ይጫኑ https://ethiopiainsider.com/2021/2398/ )