በተስፋለም ወልደየስ
አረፋፍጄ ነው ከእንቅልፌ የተነሳሁት። ትላንት አመሻሽ ላይ በነበርኩበት የኮፊ ሃውስ በረንዳ ላይ ወደተዋወቅሁት ወጣት ደወልኩ። ካረፍኩበት ሆቴል አቅራቢያ ቁርስ ቤት አገኝ እንደሁ እንዲጠቁመኝ ነበር አደዋወሌ። ወደ መቐለ በተጓዝኩ ቁጥር ቁርስ ቤቶቻቸውን የማደን ልማድ አለኝ። የከተማይቱ ቁርስ ቤቶች የሚሰሯቸው ምግቦች ጥዑም ናቸው። ከፉል እስከ ፈታ ያሉ ምግቦች እዚህ በጣፈጠ መልኩ ይሰራሉ።
የደውልኩለት ወጣት የቆየ ልማዴን እንዳላስተጓጉል ሊያግዘኝ በተለምዶ “ሃያ ሁለት” ወደ ተባለው ሰፈር ይዞኝ ሄደ። ቁርሳችንን ተመግበን፣ የሚጠበቅብንን ከፍለን፣ ዝርዝር መልስ ሲመጣ ለየት ያለ ነገር አስተዋልኩ። ከተሰጠኝ መልስ መካከል የድሮው የ10 ብር የገንዘብ ኖቶች በብዛት ይታያሉ- ላለመቀበል አንገራገርኩ። መልሱን ያመጣችልኝ ልጅ ግር ሲላት ተመለከትሁና “አሮጌው እኮ አይሰራም። አዲስ አበባ መስራት አቁሟል” አልኳት። “አይ! አስር አስር ብሩ እዚህ ይሰራል። ምንም አይሉህም። ይቀበሉሃል” ስትል ልታግባባኝ ሞከረች። በእምቢታዬ ስለጸናሁ አዲሱን የገንዘብ ኖት ሰጠችኝ።
አብሮኝ ያለውን ወጣት ስለጉዳዩ ስጠይቀው፤ በእርግጥም የድሮው የገንዘብ ኖት አሁንም ለግብይት እንደሚውል አረጋገጠልኝ። ለነገሩ ገንዘቡን ልቀይር ቢሉስ የት መቀየር ይችላሉ? በትግራይ ውጊያ ከተቀሰቀሰ በኋላ አልፎ አልፎ ስራቸውን ሲያከናውኑ የቆዩት ባንኮች ባለፈው አንድ ወር ሙሉ ለሙሉ አገልግሎት መስጠት አቁመዋል። ትላንት በመቐለ ከተማ ስዘዋወርም ይህንኑ አስተውያለሁ። ትላንት ስል ታህሳስ 17 ማለቴ መሆኑን ይዛችሁ ተከተሉኝ።
በሆቴሌ አቅራቢያ የስድስት ባንኮች ቅርንጫፎች መኖራቸውን ትላንት ልብ ብዬ ነበር። መንግስታዊው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ወጋገን፣ አንበሳ፣ አቢሲኒያ፣ ዳሽን እና ንብ ባንኮች አጠገብ ላጠገብ በቅርብ ርቀት በሚገኙ ህንጻዎች ላይ ቅርንጫፎቻቸውን ቢደረድሩም ሁሉም በራቸውን መጠርቀማቸውን አይቼያለሁ። አቢሲኒያ ባንክ እንደውም በኤቲኤም ማሽኑ ላይ አገልግሎት እንደማይሰጥ በይፋ ለጥፏል።
የገንዘብ እጥረት የከተማይቱን ነዋሪዎች ለብዙ ችግር እንዳጋለጠ ወጣቱን ጨምሮ በስተኋላ ያገኘኋቸው ሌሎችም ሰዎች አጫውተውኛል። በየዕለቱ በሚሰሩት ልክ ገቢ የሚያገኙ እንደ ባጃጅ ሹፌሮች ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች በቀን ሶስቴ መመገብ አቅቷቸው የተገኘ ጊዜ ሁለቴ፣ ባስ ሲልም አንዴ ብቻ በልተው ለማደር መገደዳቸውን ከተለያዩ ሰዎች ሰምቻለሁ። እህል ውሃውም ቢሆን ብዙዎቹ ምግብ ቤቶች ዝግ ስለነበሩ እንደልብ ማግኘቱ ችግር ሆኖ ሰንብቷል።
የገንዘብ ችግር የጠናባቸው በርካታ የከተማይቱ ነዋሪዎች ለታክሲ የሚከፍሉትን ገንዘብ ቆጥበው በእግር መጓዝ መልመዳቸውን በቆይታዬ ተመልክቻለሁ። የጓደኞቼ ጓደኞችን ጨምሮ በርካታ ወጣቶች የተከራዩትን ቤት ለቅቀው ከቤተሰቦቻቸው ጋር መጠቃለላቸው ተነግሮኛል። አስቀድመው ተቀማጭ ገንዘባቸውን ከባንክ ያወጡ አሊያም የተወሰነ የጥሬ ገንዘብ በቤታቸው ያኖሩ፤ ለሚያውቋቸው ወዳጅ ዘመዶቻቸው እያበደሩ የችግር ጊዜ ባይገፋ ኖሮ፤ በከተማይቱ ነዋሪዎች ዘንድ የከፋ ሰብዓዊ ቀውስ ሊከሰት ይችል እንደነበር ያነጋገርኳቸው ሰዎች ይስማማሉ።
ከሁሉ በላይ ኑሮ የከበደባቸው ግን ጨርቄን ማቄን ሳይሉ ድንገት ከቀያቸው የተፈናቀሉ የክልሉ ነዋሪዎች ናቸው። የእነዚህ ነዋሪዎችን ሁኔታ የከፋ የሚያደርገው ደግሞ በአካባቢያቸውን የተቀሰቀሰውን ውጊያ ሸሽተው በሄዱበት ቦታ ውጊያው እየደረሰ በየጊዜው የመፈናቀላቸው ሁኔታ ነው። በትግራይ ክልል ውጊያ በተቀሰቀሰ በሁለት ሳምንት ውስጥ የተፈናቃዮች ቁጥር 1.2 ሚሊዮን ገደማ ደርሶ እንደነበር የክልሉ መንግስት በወቅቱ አስታውቆ ነበር። የተፈናቃዮቹ ቁጥሩ በሁለት ወር ውስጥ በእጥፍ አሻቅቦ 2.2 ሚሊዮን መድረሱን የትግራይ የአስቸኳይ ጊዜ ማስተባበሪያ ማዕከል ባለፈው ሳምንት ያወጣው ይፋዊ መረጃ ያመለክታል።
ከእነዚህ ተፈናቃዮች ውስጥ የተወሰኑት በመቐለ ሃድነት ክፍለ ከተማ ባለ ትምህርት ቤት ውስጥ መጠለላቸውን ስሰማ ወደዚያው ውሰዱኝ አልኩ። ትምህርቱ ቤቱ የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች የሚማሩበት ነው። ቅሳነት ይባላል። ትርጉሙ “እፎይታ” ለሚለው የአማርኛ ቃል የቀረበ ነው ይላሉ ቋንቋውን የሚያውቁት። በትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ መግቢያ ላይ አጀብ ብለው የተሰበሰቡትም ሆነ ከበሩ ተሻግረው ባሉ ኮፊ ሃውሶች የተኮለኮሉት ሰዎች ግን እፎይታ እንደራቃቸው ገጻቸው ይመሰክራል።
ከመግቢያው ላይ ከቆሙት የተወሰኑት በግድግዳው ላይ የተለጠፈ የስም ዝርዝር ላይ አተኩረዋል። ከየቦታው የተፈናቀሉ ሰዎችን ስም የያዘ እንደሆነ ሰማን። ማይካድራ፣ ሁመራ የሚሉ ከተሞችም ጆሮአችን ጥልቅ አለ። ወደ ውስጥ ዘለቅን። የትምህርቱ ቤቱ ግቢ በአቧራ የተሸፈነ ነው። ከመግቢያው ብዙም ሳይርቅ በቆመው የባንዲራ መስቀያ ላይ ያለው ሰንደቅ እንዳይወለበለብ ተጠቅሎ ተቋጥሯል። በባንዲራው በስተቀኝ ካለው የመጀመሪያ ክፍል የውጭ ግድግዳ ላይ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ትልቅ ስዕል ይታያል።
በዚህ ክፍል በረንዳ ላይም ሆነ በሌሎቹ ክፍሎች መግቢያ ላይ ባሉ ደረጃዎች ጥቂት ሰዎች ተቀምጠዋል። በአንደኛው የግቢው ጥግ ህጻናት እየተጫወቱ ነው። በግቢው ታች ካለው አነስተኛ ሜዳ አጠገብ ታጥበው እንዲደርቁ የተሰጡ ልብሶች ይታያሉ። በመማሪያ ክፍሎቹ እየገባን የተፈናቃዮቹን ሁኔታ ተመለከትን። ብዙዎቹ ክፍሎች የተጠጋጉ ፍራሾች ተነጥፎባቸዋል። ተፈናቃዮቹ ፍራሾቹ ከተሸፈኑባቸው አልጋ ልብሶች እና አንሶላዎች፣ ጥቂት ልብሶች ከያዙ ፌስታሎች እና የውሃ መያዣ ፕላስቲኮች ውጭ ሌላ ንብረት የላቸውም።
በመጨረሻ ባየነው የመማሪያ ክፍል ውስጥ ከተጠለሉ ተፈናቃዮች መካከል አንዱን ያሉበትን ሁኔታ እንዲነገርን ጠየቅነው። አወት ይባላል። ነዋሪነቱ በሁመራ ከተማ ነበር። በከተማይቱ የአንድ አስመጪ እና ላኪ ወኪል እንደነበር ይናገራል። “ሰሊጥ አበጥሬ ኤክስፖርት አደርግ ነበር” ይላል የቀድሞ ህይወቱን በሀዘን መለስ ብሎ ሲያስታውስ። ሁመራን ጥሎ ከተሰደደ በኋላ ለበርካታ ቀናት በእግሩ መጓዙን ይገልጻል። “ገጠር ለገጠር ነው የነበርኩት” ሲልም የነበረበትን ያስረዳል።
የቀድሞው ሰሊጥ ነጋዴ አስር ፍራሾች በተነጠፋባት አንድ የመማሪያ ክፍል ውስጥ ውሎ አዳሩን ካደረገ አንድ ሳምንት ሆኖታል። በየክፍሎቹ ያሉት ፍራሾች የተሰባሰቡት ከመቐለ ዩኒቨርስቲ እና ወህኒ ቤት መሆኑን ሰምቷል። ፍራሾቹን በማሰባሰብ የጋዜጠኛ ሙሉ ሃይለስላሴ ድርሻ ላቅ ያለ መሆኑንም ይናገራል። ጋዜጠኛ ሙሉ የተቸገሩ እና ልዩ ድጋፍ የሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎችን የሚያስተዋውቅ እንዲሁም እርዳታ እንዲያገኙ የሚያመቻች ሳምንታዊ የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅ ነበር። በድምጸ ወያኔ ቴሌቪዥን ይተላለፍ ከነበረው ከዚህ ፕሮግራሙ በተጨማሪ የኮሮና ወረርሽኝ በበረታበት ወቅት ለተቸገሩ ሰዎች እርዳታ ያሰባስብ እንደነበር የሚያውቁት ይመሰክራሉ።
እንደ ጋዜጠኛው ሁሉ በአካባቢው የሚኖሩ ባለሀብቶችም እንደረዷቸው አወት ይገልጻል። የለበሰውን ልብስ እንኳ የሰጡት ሁመራ ሲሰራ የሚያውቁት ነጋዴዎች እንደሆኑ ይናገራል። በትምህርት ቤቱ አካባቢ የሚኖረው ማህበረሰብም የሚበሉትን በማቅረብ ያላሰላሰ ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው ሲጠቅስ “የእዚህ ሀገር ሰው ግን በጣም የዋህ ነው” ይላል በምስጋና መንፈስ። “የአካባቢው ህዝብ ነው አዋጥቶ ፓስታ፣ ማኮሮኒ፣ ሩዝ ገዝቶ የሚያመጣልን። ከዚያ ቁርስ በየክፍሉ በፕሮግራም በፕሮግራም እያበሰልን እንበላለን” ሲልም ዕለታዊ የአመጋገብ ሁኔታቸውን ያብራራል።
በቅሳነት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ 350 ተፈናቃዮች እንዳሉ ከራሳቸው የተገኘው መረጃ ይጠቁማል። ይህ ቁጥር ህጻናትንም ይጨምራል። አብዛኞቹ ተፈናቃዮች የመጡት ከምዕራብ ትግራይ ዞን ነው። ከሁመራ የመጡት በርከት ቢሉም ከማይካድራ፣ በረከት፣ አደባይ፣ ዳንሻ ሳይቀር ተፈናቅለው እዚህች አነስተኛ ትምህርት ቤት የተጠለሉ አሉ። የተፈናቃዮቹ ቁጥር እየበዛ ሲመጣ፣ የኮሮና ወረርሽኝ እንዳይስፋፋ በመስጋት፣ በቅርቡ የተወሰኑትን በአቅራቢያው ወዳለ “አዲ ሃቂ” ወደሚባል ትምህርት ቤት እንዳዛወሯቸው አወት አጫውቶናል።
“እዚህ ከመጡ በኋላ የወለዱም አሉ። የሚጥል በሽታም ያላቸው አሉ። ከእነርሱ እኛ እንሻላለን። ወጣ ብለን እዚህ አካባቢ ‘እንጀራ ስጡን’ ማለት እንችላለን” ይላል አወት። ከግለሰቦች በተጨማሪ እርዳታ የሚያቀርብላቸው አካል እንዳለ አወትን ጠየቅሁት። “ቀይ መስቀልም አለ። ማህበራዊ ጉዳይም የሚባሉ አሉ። ብልጽግና ናቸው። እገዛቸው ግን አያረካህም። ማህበረ ልማት ትግራይ (ማረት) አሁን ስንዴ ጀምረዋል። ሰላሳ ኪሎ ስንዴ፣ አንድ ሊትር ዘይት ለሁለት ወር ነው የሚሰጡን። እንዴት አድርጎ ያስበላል አሁን ይሄ ለሁለት ወር?” ሲል ጥያቄ ያዘለ ምላሽ ሰጠኝ።
የሁመራው ተፈናቃይ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮን “ብልጽግና” እያለ ነው የሚጠራው። ምጸታዊው ነገር ቢሮውን እንዲመሩ በጊዜያዊው አስተዳደር የተሾሙት የተቃዋሚው የአረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ሉአላዊነት ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ አብርሃ ደስታ መሆናቸው ነው። ይህን እውነታ ልብ ያላለ የሚመስለው አሊያም እንደ ሌሎቹ የመቐለ ነዋሪዎች “ስልቻ ቀልቀሎ….” አድርጎ የወሰደው አወት፤ በቢሮው በኩል የተደረገላቸውን እርዳታ እንደ ብልጽግና ፓርቲ ድጋፍ ቆጥሮ ማብራራቱን ቀጥሏል።
“ብልጽግና ፊኖ [ፉርኖ] ዱቄት አምጥታ ነበር ። 15 ኪሎ፣ 30 ኪሎ ሰጡን። የደረሰውም አለ፤ ያልደረሰውም አለ። የእዚህ ሀገር ወጣቶች ቅልቅል ናቸው። ዱርዬዎች ይገባሉ። በቃ ! ገብተው ያለ ስማቸው ‘አቤት’ ብለው ይወስዳሉ። የመታወቂያ አሰራራቸው ስርዓት የለውም” በማለት ትችት አዘል አስተያየቱን አካፈለን።
የተፈናቃዮች ጉብኝታችንን በዚሁ አጠቃለን ወደ ውጪ ወጣን። አስጎብኚም፣ ረዳትም ሆኖ አብሮኝ የሚዞረውን የ23 ዓመት ወጣት ወደ ከተማ እንዲወስደኝ ጠየቅሁት። “ከተማ መሃል በከባድ መሳሪያ የተመቱ ቦታዎች አሉ” መባሉን ስለሰማሁ በአይኔ አይቼ ለማረጋገጥ ነበር ውጥኔ።
* * *
የተሳፈርንበት መኪና፤ የትግራይ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያለበት ስፍራ ሲደርስ ወደ ቀኝ ታጠፈ። ይሄኔ ወጣቱ ከፊት ለፊት የማየውን የአስፋልት መንገድ ልብ ብዬ እንድመለከት ጠቆመኝ። አስፋልቱ ተቆፋፍሯል። ጠጋ ብዬ ስመለከት ወደ ጠርዝ ያለው ክፍሉ ተገምሶ ከታች ያለው አፈር ይታያል። የተቆራረጡ የአስፋልቱ ክፍሎች ተበታትነዋል። የመከላከያ ሰራዊት መቐለን የተቆጣጠረ ቀን በዚህ አስፋልት ላይ የከባድ መሳሪያ አረር አርፎ እንዲህ እንዳደረገው ገለጸልኝ። ከዚያ ብዙም ሳይርቅ በከባድ መሳሪያ የተመቱ ሌሎች ቦታዎች እንዳሉ ነገረኝ። በቀጥታ ወደዚያው አመራን።
መጀመሪያ የተመለከትኩት አንድ የክልሉ መንግስት ጽህፈት ቤትን ነው። መንገድ ዳር ያለው የዚህ ጽህፈት ቤት ፍራስራሽ ከአንድ ወር በኋላም ከቦታው አልተነሳም። አገልግሎት መስጫ መስሪያ ቤቱ፤ በቀዳማይ ወያነ ክፍለ ከተማ ስር ያለ መሆኑን የሚገልጸውና ከመግቢያ በሩ ላይ ተሰቅሎ የነበረው ታፔላ ተገንጥሎ ወደ መሬት ወድቋል። የጽህፈት ቤቱ ብሎኬት አጥርም ተደርምሶ ወደ አስፋልት ፈስሷል።
አስፋልቱን ተሻግሮ፣ ከዚሁ መስሪያ ቤት ፊት ለፊት የሚገኙ ሌሎች ቢሮዎችም ተቃጥለው እና ተገነጣጥለው፣ በውስጣቸው የነበሩ ሰነዶች እና ወረቀቶች በሜዳ ላይ ተዘረክርከው ይታያሉ። እነዚህ ቢሮዎች ጉዳት ቢደርስባቸውም ለወታደሮች በጊዜያዊ ማረፊያነት ከማገልገል ወደ ኋላ አላሉም።
ከእነዚህ ጽህፈት ቤቶች አቅራቢያ በሚገኘው ቀበሌ 15 የከባድ መሳሪያ አረር ያደረሰባቸው ጉዳት በጉልህ የሚታይ፤ መጠጥ ቤቶች እና መዝናኛዎች አሉ። “ኤደን ሃውስ” የሚል ስያሜ ያለው መጠጥ ቤት ግድግዳ እና በሮች በከባድ መሳሪያ ፍንጥርጣሪዎች ተበሳስቷል። ከመጠጥ ቤቱ ጎን እና ትይዩ ያሉ ቤቶች ላይ የሚታየው ጉዳትም ተመሳሳይ ነው።
ከመጠጥ ቤቶቹ በአንዱ በአስተናጋጅነት ይሰራ የነበረ እና የከባድ መሳሪያ ጥቃቱ ሲፈጸም በቦታው የነበረ ወጣት አፈላልገን አገኘን። ጥቃቱ ከተፈጸመ አንድ ወር ሊሞላው በዋዜማው ላይ ብንሆንም ወጣቱ ግን ልክ ትላንት እንደሆነ ሁሉ በስሜት ተውጦ ነው የሚተርክልን። በዕለቱ ከምሽቱ 12 ሰዓት አካባቢ “የተወንጫፊ መሳሪያ” ድምጽ መስማቱን የሚናገረው ወጣት፤ የደረሰውን ጉዳት ለማጣራት በመሻት ከመጠጥ ቤቱ ጣሪያ ላይ መውጣቱን መለስ ብሎ ያስታውሳል።
ወጣቱ ከጣሪያው ላይ ሆኖ ባሻገር ካለፈው አስፋልት፣ ታክሲ መቆሚያ አጠገብ የደረሰውን ጉዳት እየተመለከተ እያለ፤ ወደ እርሱ አቅጣጫ የሚምዘገዘግ “ተወንጫፊ” መሳሪያ ድምጽ ሲሰማ አጠገቡ ባለው “ሮቶ” የውሃ ማጠራቀሚያ ጀርባ መሸሸጉን ይገልጻል። ያንን ተከትሎ ከፍተኛ የፍንዳታ ድምጽ መሰማቱን እና እርሱም በፍጥነት ወደታች መውረዱንም ያስረዳል። ጎረቤታቸው በሚገኝ ድራፍት ቤት እና ግሮሰሪ ውስጥ ሲጠጡ የነበሩ ሰዎች በፍንጥርጣሪው ተመትተው መውደቃቸውን ከተመለከተ በኋላ ነፍሱን ለማትረፍ በሩጫ አካባቢውን ለቅቆ መፈትለኩን ይናገራል።
“ብዙ ሰው የሞተ አለ። የሞቱ ሰዎች አይተህ፤ ድጋሚ ተወንጫፊ ይመጣል ብለህ ረግጠኸው ታልፋለህ” ይላል ወጣቱ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ሲያስታውስ። ነገሮች ከተረጋጉ በኋላ ወደ ስፍራው የተመለሰው ይህ ወጣት፤ በአካባቢው ባረፉ አራት የተለያዩ “ተወንጫፊ” ከባድ መሳሪያዎች ምክንያት 19 ሰዎች እንደሞቱ መረዳቱን ይገልጻል። በዚሁ ጥቃት ከቆሰሉ የአካባቢያው ሰዎች መካከል አንዲት ሴት ሁለት እግሮቿ ተቆርጠው በሆስፒታል መተኛቷንም ያክላል። እኛን ከማግኘቱ ከአንድ ቀን በፊት ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ተጎጂዋን በሆስፒታል እንዳለች መጎብኘታቸውን፤ የተኛችበትን ክፍል በማጣቀስ ጭምር ያብራራል።
በዚህ የከባድ መሳሪያ ጥቃት 21 ሰዎች መሞታቸውን አስቀድሜ ሰምቼ ስለነበር፤ የቁጥሩን መለያየት ከምን የመነጨ እንደሆነ ለማረጋገጥ ተጨማሪ ጥያቄ ለወጣቱ አቀረብኩ። በእርግጥም ሁለት ተጨማሪ ሰዎች በዚሁ ምክንያት መሞታቸውን ነገር ግን ቦታው እነርሱ ከነበሩበት ራቅ ብሎ፣ ትምህርት ቢሮ ያለበት አካባቢ እንደሆነ ምላሽ ሰጠኝ። ከእነዚህ በተጨማሪ በከባድ መሳሪያ እና በአየር ድብደባ በአንድ ትምህርት ቤት እና በሰዎች መኖሪያ ቤቶች ላይ ጉዳት መድረሱን ያገኘኋቸው ሰዎች ነግረውኛል። ትምህርት ቤቱን ለነገ ለመመልከት ቀጠሮ ይዤ ወደ ማደሪያዬ ተመለስኩ።
ከምሽቱ አንድ ሰዓት ጀምሮ ወደ ውጭ ውልፊት ማለት አይቻልምና ረጅሙን ምሽት ለመግፋት በሆቴል ክፍሌ ውስጥ ካለው ቴሌቪዥን ፊት ተጣድኩ። የምሽት ሁለት ሰዓት ዜና እስኪደርስ ከአንደኛው የቴሌቪዥን ጣቢያ ወደ ሌላው እያቀያየርኩ እመለከታለሁ። በዚህ መካከል ነበር ትላንት ምሽት በቴሌቪዥን መተላለፉን የተነገረኝና “አመለጠኝ” ብዬ ስቆጭበት የነበረው የመቐለ ነዋሪዎች ውይይት በድጋሚ ሲተላለፍ ያጋጠመኝ።
ውይይቱ የተካሄደው እኔ መቐለ ከመግባቴ ሁለት ቀናት አስቀድሞ ነበር። ከዚህ ቀደም የህወሓትም ሆነ የትግራይ ክልል መንግስት ስብሰባዎች ይደረጉበት በነበረው የሃውልቲ አዳራሽ በተካሄደው በዚሁ ስብሰባ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ሙሉ ነጋ፣ የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር ዶ/ር አብርሃም በላይ፣ የመቐለ ከተማን በከንቲባነት እንዲመሩ በቅርቡ የተሾሙት አቶ አታኽልቲ ኃይለስላሴ እንዲሁም የመከላከያ ሰራዊት የሰሜን ዕዝ አዛዥ ሜጀር ጄነራል በላይ ስዩም ተገኝተዋል።
በዚህ ስብሰባ የተነሱ አንኳር ጉዳዮች በዜና መልክ ተጨምቀው ሲቀርቡ ተመልክቼ ስለነበር፤ በመጀመሪያው እና ሁለተኛው ቀን ውሎዬ ያገኘኋቸውን ሰዎች ስለ ስብሰባው ሁኔታ ጠይቄያቸው ነበር። ያነጋገርኳቸው ሰዎች በቴሌቪዥን የተመለከቱትን የወደዱት አይመስልም። አንዳንዶቹ “ለስብሰባው የተጠሩት አብዛኞቹ ሰዎች የአንድ አካባቢ ሰዎች እና ከድሮም ጀምሮ በህወሓት ላይ ቂም የነበራቸው ናቸው” የሚል አመለካከት አላቸው። ጥቂቶች “የአንድ ሃይማኖት ተከታይ ሰዎች በዝተዋል” ሲሉ፤ ሌሎች ደግሞ “የተነሱት ሃሳቦች የህብረተሰቡን ዋነኛ ስሜቶች ያስተጋቡ አይደሉም” ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል።
ሆኖም የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለትግርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች በመደበው “ቮይስ ኦፍ ትግራይ” ቻናል ሲተላለፍ በተመለከትኩት ሙሉ ውይይት የተነሱ ሀሳቦች፤ በከተማይቱ ስዘዋወር ካደመጥኳቸው እምብዛም የራቁ አልነበሩም። አንዳንዶቹ የውይይቱ ተሳታፊዎች የከተማው ነዋሪ በየኮፊ ሃውሱ እና መጠጥ ቤቶች ድምጹን ቀንሶ የሚያወራውን፤ በባለስልጣናቱ እና በወታደራዊ አዛዡ ፊት በድፍረት አንስተዋል። ምናልባት ለከተማይቱ ነዋሪዎች ቅሬታ መፈጠር አንዱ ምክንያት የሆነው ውይይቱ ከተካሄደ በኋላ በመንግስት መገናኛ ብዙሃን የተዘገበበት መንፈስ ሳይሆን አይቀርም።
ብሔራዊው የቴሌቪዥን ጣቢያ የውይይቱን ጨመቅ በዜና መልክ ሲያቀርብ የተጠቀመው ርዕስ “የትግራይ ህዝብን ከሕወሓት ጁንታ ነፃ ስላወጣው፤ ‘የመከላከያ ሰራዊትን እናመሰግናለን’ ሲሉ የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ” የሚል ነበር። ሌላኛው የቴሌቪዥን ጣቢያም በዜናው መክፈቻ አንቀጽ ላይ “የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከመቐለ ከተማ ነዋሪዎች ጋር ባደረገው ውይይት፤ ህዝቡ ከህወሓት ጁንታ ነጻ በመውጣቱ የተሰማውን ስሜት አንጸባርቋል” የሚል አረፍተ ነገር ተጠቅሟል። የውይይቱ ሙሉ ክፍል ከቀናት በኋላ ሲተላለፍ ግን የህዝቡ አንገብጋቢ ጥያቄዎችም በተሳታፊዎች መነሳታቸው ታይቷል።
ከስብሰባው ተሳታፊዎች መካከል ጠንከር ያሉ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች የሰነዘሩት “የህዝብ ተወካይ መሆናቸውን” የገለጹ አንድ አባት ናቸው። አዛውንቱ “በትግራይ ክልል የተከሰቱ እና መፍትሄ የሚያሻቸው” ያሏቸውን ችግሮች አንድ በአንድ ዘርዝረዋል። በጦርነቱ ምክንያት በትግራይ ህዝብ ላይ ደረሰ ያሉትን ጉስቁልና፣ ያለ ምንም ከልካይ ስለሚካሄዱ ዝርፊያዎች፣ ስለ ጸጥታ ችግር፣ ስለ አስተዳደር መዋቅር መፈራረስ እንዲሁም ስለ ኢትዮጵያ ሉዓላዊነት መደፈር ሲናገሩ የስብሰባው ተሳታፊዎች ለንግግራቸው ያላቸውን ድጋፍ በተደጋጋሚ ጭብጨባ ሲገልጹ ተደምጠዋል።
አዛውንቱ የትግራይ ህዝብ አሁን ያለበትን ሁኔታ የገለጹት “ህዝቡ ተጎሳቆሏል። ኑሮው፣ ጸጥታው፣ ስነ ልቦናው በጭንቀት ላይ ነው” በማለት ነበር። የትግራይ ህዝብ በቱርኮች፣ ግብጾች፣ ማህዲስቶች እና ጣሊያኖች ጦርነት እንደተከፈተበት ያስታወሱት አዛውንቱ፤ “ህዝቡ ጦርነት አይፈልግም። ሰልችቶታል” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል። በክልሉ ጦርነቱ ካስከተለው ጉዳት ባሻገር የመንግስት መዋቅር መፈራረሱ ህዝቡን ለባሰ ችግር እንዳጋለጠውም ጠቁመዋል። ለመዋቅሩ መፈራረስ ዋነኛው ምክንያት “ሁሉም በፖለቲከኛ ድርጅት በመካተቱ” እንደሆነ አመልክተዋል።
“በአሁኑ ወቅት የክልሉ መንግስት መዋቅር በሙሉ ፈርሷል። ሌባ ቢያዝ የት ይዳኛል? ንብረቴን ተዘረፍኩ ብሎ ‘ኡኡ’ የሚል ነጋዴ ማን ጋር ሄዶ አቤት ይበል። ባዶ እጁን ነው፤ መሳሪያ የለው፤ አይከላከል…ባዶ እጁን ሆኖ ንብረቱን እየተዘረፈ ነው። ከእስር ቤት የተለቀቁ ወንጀለኞች መጫወቻ ሆኗል ህዝቡ። ልዕልናው፣ ክብሩ፣ ስነ ልቦናው ተሰልቧል። አቅም የለውማ! ምን ያድርግ?” ብለዋል አዛውንቱ።
እኚሁ የህዝብ ተወካይ በመድረኩ ለተሰየሙ ባለስልጣናት “መንግስታዊ መዋቅር በአስቸኳይ እንዲያቋቁሙ” ያሳሰቡ ሲሆን ቀደም ሲል የነበሩ እንደ ፖሊስ እና ሚሊሺያ ያሉ የጸጥታ ሃይሎችም “ሰላማዊ መሆናቸው ተገምግሞ” ወደ ስራ እንዲገቡ ጥያቄ አቅርበዋል። ከዚህ በተጨማሪም የክልሉን እና የሀገሪቱን ጸጥታ በማስከበር ረገድ የመከላከያ ሰራዊት “ሊያደርግ ይገባው ነበር” ያሉትን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ “ሉዓላዊት ሀገር” መሆኗን የገለጹት አዛውንቱ፤ “ማንም ሊደፍራት አይገባም” ሲሉ ጣታቸውን እያወዛወዙ የቁጭት ስሜታቸውን አጋርተዋል። በተሳታፊዎች ጭብጨባ የታጀበው የህዝብ ተወካዩ ንግግር፤ መቐለ ከገባሁ ጀምሮ በተደጋጋሚ የምሰማው የኤርትራ ወታደሮችን ጉዳይ በገደምዳሜ ያነሳ ነበር።
“መለስተኛ ሀብት እና ንብረት ያላቸው ሰዎች ተዘርፈዋል። ይሄ ለምን ይሆናል? የሀገራቸው ወታደር ዲስፕሊንድ ነው። አሁንም ከእኛ ጋር ነው ያለው። ምንም የሰራው ነገር የለም። ለምን? ይሄ ለምን ይሆናል? ይሄ ህዝብ እኮ ታላቅ ህዝብ ተብሎ፤ ኢትዮጵያ የምትባለውን ሀገር፤ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር አብሮ የገነባ ህዝብ ነው። ይሄ እንዲታረመልን፤ እንዲስተካከልልን ህዝቡ ይፈልጋል” ብለዋል አዛውንቱ።
ለዚህ ችግር፤ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ማስፋፋት እና የንግድ ልውውጥ ማካሄድን በመፍትሄ ሀሳብነት የጠቆሙት አዛውንቱ፤ “ይሄ ሁሉ ለሀገሪቷ ዕድገት እንጂ፤ ለተወሰኑ የትግራይ ህዝቦች ሰዎች ፍላጎት ማሟያ አይደለም” ሲሉ ሀሳባቸውን አጋርተዋል። “ህዝብን ህዝብ የሚያሰኘው የሰው ቁጥር አይደለም፤ ህዝብ ራሱ ነው” በማለትም ጉዳዩ ለሚመለከታቸው መልዕክታቸውን አድርሰዋል።
* * *
በመቐለ ሶስተኛ ቀኔን ይዤያለሁ። ዕለቱ ሰኞ ነው፤ የስራ መጀመሪያ ቀን። ቅዳሜ እና እሁድ ተፋዝዛ ያየኋት መቐለ ዛሬ የተለየ እንቅስቃሴ ታሳይ እንደሁ ለመታዘብ በከተማዋ ለመዘዋወር አቅጃለሁ። የመከላከያ ሰራዊት ከተማይቱን ከተቆጣጠረ ዛሬ ድፍን አንድ ወሩ መሆኑ ደግሞ ለትዝብቴ ወሳኝ የጊዜ ምዕራፍ ሆኖልኛል። አንድ ወሩ እንዴት እንዳለፈ ከተወሰኑ የከተማይቱ ነዋሪዎች እና ለጊዜያዊ አስተዳደሩ ቅርብ ከሆኑ ሰው ጋር ለመወያየት ቀጠሮ ይዤያለሁ። ከሁሉ አስቀድሞ ግን በጠዋቱ መከወን ያለባቸው ሁለት ጉዳዩች አሉኝ።
የመጀመሪያው ጉዳይ በሆቴሌ አቅራቢያ ወዳለው የገብርኤል ቤተክርስቲያን መሄድ ነበር። በዚያ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በዓመት ሁለቴ በድምቀት የሚከበረው የቅዱስ ገብርኤል የንግስ በዓል ይካሄዳል። የበዓል አከባበሩ፤ ከተማይቱ ወደ መደበኛ ህይወቷ እየተመለሰች ስለመሆኑ እና ስለ ህዝቡ ስሜት የሚጠቁመው ነገር ይኖራል በሚል ነበር ወደዚያ ለመሄድ መነሳቴ። ዛሬም አስጎብኚዬ ወጣት ከአጠገቤ አለ።
ወደ ቤተክርስቲያኑ የሚወስደው ባለ ሁለት መስመር መንገድ ዳር እና ዳር በሰዎች ተሞልቷል። በተሳፋሪዎች ጢም ብለው የሞሉ ሚኒባሶች ማቆሚያ ቦታ እስኪቸገሩ ድረስ አካባቢውን አጨናንቀውታል። ሰዓቱ ወደ ሁለት ሰዓት እየተጠጋ ነው። ወደ ቤተክርስቲያኑ የሚተመውን ሰው ብዛት ያህል፤ ጸሎት አድርሰውና ተሳልመው ወደ ቤታቸው የሚመለሱም ብዙ ነበሩ። በርከት ያሉ ነጠላ ያጣፉ ምዕመናን በቤተክርስቲያኑ አቅራቢያ ከሚገኘው የትግራይ ታጋዮች እና አርበኞች መካነ መቃብር አጠገብ ባለ ቦታ ተሰባስበው አንድ ነገር ሲመለከቱ አይቼ ወደዚያው ተጠጋሁ።
በዚህ ቦታ ጣሪያ የተሰራላቸው፣ ግድግዳ አልባ፣ ሶስት አነስተኛ ቤት መሳይ ነገሮች ይታያሉ። የሶስቱም ስሪት ቢለያይም የሚያመሳስላቸው አንድ ነገር አለ። ሶስቱም በተመሳሳይ ዓመት ህይወታቸውን ላጡ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች መታሰቢያ የተገነቡ ናቸው። ሁለቱ በአንድ ቀን፣ በአንድ ቦታ የተገደሉ ጄነራሎች ናቸው – ጄነራል ሰዓረ መኮንን እና ሜጀር ጄነራል ገዛኢ አበራ። ሌላኛው የትግራይ ልዩ ሃይል አባላትን በማሰልጠን ከፍተኛ ሚና እንደነበራቸው የሚነገርላቸው ጄነራል አብርሃ ወልደማርያም (ኳርተር) ናቸው።
ምዕመናኑ በመስታወት በታጠረው የጄነራል ሰዓረ መታሰቢያ እና በሰንሰለት መከለያ በተበጀለት የሜጀር ጄነራል ገዛኢ ሃውልት ፊት ለደቂቃዎች ከቆሙ በኋላ ቦታውን ለተረኞች ይለቅቃሉ። ሶስተኛው መታሰቢያ እንደ ሁለቱ በቅጡ ያልተሰራ እና ገላጭ ጹሁፍ የሌለው በመሆኑ ይመስላል የአብዛኞቹን ተመልካቾች ትኩረት እምብዛም አልሳበም። ቤተክርስቲያን ተሳልመው ከሚመለሱት ውስጥ ለተወሰኑቱ ሌላ ቀልባቸውን የሚገዙ ነገሮች ነበሩ።
እስከ ቤተክርስቲያኑ መዳረሻ ድረስ በተዘረጋው አስፋልት ዳር፤ ከሰሞኑ ከገበያ ጠፍተው የሰነበቱ ሸቀጦች ይቸበቸባሉ። አንደኛው ቸርቻሪ ክብሪት ከምሮ ይሸጣል። ሌላኛው የልጆች ልብስ በ30 ብር ብቻ እንደሚሸጥ ጮክ ብሎ ያስተዋውቃል። ቄጤማ፣ ጧፍ፣ ሻማ፣ የሃይማኖት መጽሐፍት በሽ ናቸው። ከቲማቲም እስከ ሰላጣ ለምግብ የሚውሉ ግብዓቶችን በብዛት ያቀረቡም ነበሩ። የቤት ዕቃዎችን በብዛት ከምረው የሚሸጡም አልጠፉም።
ይህ ሁሉ የሚከናወነው በጥብቅ የጸጥታ ቁጥጥር ስር ተሁኖ ነው። በአካባቢው ከተሰማሩ መሳሪያ ከታጠቁ የፌደራል ፖሊስ አባላት ሌላ በፒክ አፕ መኪና ተጭነው አካባቢውን የሚቃኙ ወታደሮች አሁንም አሁንም መለስ ቀለስ ይላሉ። ከህዝቡ መካከል ቢሆኑም በታጠቁ የፌደራል ፖሊስ አባላት ዙሪያቸውን በተጠንቀቅ እየተጠበቁ ነው የሚጓዙት። ከህዝቡ መካከል ቢሆኑም በታጠቁ የፌደራል አባላት ዙሪያቸውን በተጠንቀቅ እየተጠበቁ ነው የሚጓዙት።
ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ስንጠጋ፤ ከርቀት ተመልክቼ ከገመትኩት በላይ ዙሪያ ገባው ነጭ ነጠላ እና ጋቢ በደረቡ በዓል አክባሪዎች ተጥለቅልቋል። በከተማው ካለው የህዝብ መጓጓዣ እጥረት እና ባለፉት ቀናት ካየሁት የተፋዘዘ እንቅስቃሴ በመነሳት ይህን ያህል ሰው በበዓሉ ላይ ይገኛል ብዬ አልጠበቅሁም ነበር። የበዓል አክባሪው ቁጥር ወትሮ ከነበረው እንደውም መጨመሩን አስጎብኚዬ ገለጸልኝ። ለዚህ ምክንያቱ ብዙ ሰው እንደቀድሞው ወደ ስራ ወይም ትምህርት ስለማይገባ እንደሆነ ግምቱን አጋራኝ። በቤተክርስቲያኑ ዙሪያ እየተዘዋወርኩ ጥቂት ደቂቃዎች ቆየሁ።
ከዚህ በላይ ቆይቼ፤ እናቶች ለእግዚያብሔር የሚያቀርቡትን ምህላ መከታተል ፈልጌ ነበር። በትግራይ ያሉ እናቶች፤ በአካባቢያቸው ችግር እና መከራ በመጣ ቁጥር፣ እንዲህ ባሉ የቤተክርስቲያን መርሃ ግብሮች ማጠናቀቂያ ላይ ተሰብስበው በዜማ የታጀበ፣ አንጀት የሚበላ ምህላ እንደሚያቀርቡ ከዚህ በፊት በቪዲዮ ተመልክቼያለሁ። ለቤተክርስቲያን ገቢ ለማሰባሰብ በምዕመናን መካከል ከሚዞሩ እናቶች ውስጥ አንደኛዋ፤ ምህላው ዛሬም እንዳለ ቢነግሩኝም፤ መርሃ ግብሩ እስኪጠናቀቅ መጠበቅ አልቻልኩም። ሳይረፍድ ከተማ መሃል ወደሚገኘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የትኬት መሸጫ ቢሮ መሄድ ነበረብኝ። የመመለሻ የአውሮፕላን ትኬት በጊዜ ለመቁረጥ በማሰብ ነበር በቶሎ ለመሄድ የተነሳሁት።
ከበዓል የሚመለሱ ሰዎችን እየተመለከተን ወደ ሆቴሌ ስንመለስ ያልጠበቅሁት ነገር ከአይኔ ገባ። ተጠራጥሬ አስጎብኚዬን ጠየቅሁት። ያየሁትን አረጋገጠልኝ። ፖሊሶች ናቸው። የመደበኛ ፖሊስ የደንብ ልብስ የለበሱ ሶስት ፖሊሶች። በከተማይቱ ነዋሪዎች ተደጋግሞ ከሚጠየቀው ጉዳይ አንዱ የሆነው “ፖሊሶች ስራ ይጀምሩልን” ጥያቄ በትንሹም ቢሆን መመለስ መጀመሩን ያየሁበት አጋጣሚ ነበር። ወደ ሆቴሌ ስቃረብ ሌላው የነዋሪዎች ጥያቄ የሆነው የባንክ አገልግሎት እንዲሁ ሊጀመር ነው መባሉን ሰማሁ።
ጥቂት ሰዎች ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዲ ሃቂ ቅርንጫፍ በር ላይ ተሰባስበው የወሬውን እውነተኛነት ለማረጋገጥ ይሞክራሉ። በእርግጥም አገልግሎቱ ዛሬ እንደሚጀመር የሚያበስር ማስታወቂያ ተለጥፏል። ሆኖም አገልግሎቱ የሚሰጠው በመቐለ ከተማ የባንክ ደብተር ላወጡ ደንበኞች ብቻ መሆኑን በማስታወቂያው ላይ ተመልክቷል። ማስታወቂያው እንደሚለው አንድ ሰው በወር ውስጥ ማውጣት የሚችለው የገንዘብ መጠንም 25 ሺህ ብር ብቻ ነው። ይህ ገደብ ወደፊት የገንዘብ አቅርቦቱ እየታየ እንደሚስተካከል በማስታወቂያው ተገልጿል። ከአንድ ግለሰብ የባንክ ሂሳብ ወደ ሌላ ግለሰብ የሚደረግ ማንኛውም የገንዘብ ዝውውር ለጊዜው እንደማይፈቀድ በማስታወቂያው የጠቆመው መንግስታዊው ባንክ፤ ማንኛውንም የክልሉን መስሪያ ቤቶች ቼኮች ተቀብሎ ክፍያ እንደማይከፍልም አስታውቋል።
በአካባቢው ያሉ ሌሎች የግል ባንኮች ስራ ጀምረው አሊያም ተመሳሳይ ማስታወቂያ ለጥፈው እንደሁ ተመለከትኩ። ምንም የተለየ እንቅስቃሴ አይታይባቸውም። ወደ ከተማ ስወጣም ከንግድ ባንክ ቅርንጫፎች ሌላ በሌሎች ባንኮች የተለየ ነገር አይስተዋልም። በንግድ ባንክ ቅርንጫፎች ግን የከተማይቱ ነዋሪ ገና ካሁኑ ረጃጅም ሰልፍ ሰርቶ የሚሆነውን እየጠበቀ ነው። በከተማው መሃል የሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና ቅርንጫፍ መስሪያ ቤትም ሸብ ረቡ በዝቷል። በአካባቢው በርካታ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ቆመው ይታያሉ።
ከባንኩ ትይዩ ወደሚገኘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቢሮ አመራሁ። አስራ አንድ ሰዎች ቀድመውኛል። ወረፋ ለመጠበቅ በተዘጋጁት ወንበሮች ላይ አረፍ አልኩ። በትኬት ሽያጭ ቢሮ ውስጥ አገልግሎት እየሰጡ ያሉት አንዲት ሴት ብቻ ናቸው። የጠባቂው ሰው እየጨመረ መምጣቱን የታዘቡት እኚሁ ሴት፤ ከመቐለ ወደ አዲስ አበባ ለመጓዝ ቦታ ያለው፤ ከ12 ቀን በኋላ እንደሆነ አረዱን። ትኬት ለመቁረጥ የሚጠበቀውን ክፍያም እዚህ እንደማይቀበሉ እና ክፍያው አዲስ አበባ ባለ ሰው መፈጸም እንዳለበት ነገሩን። እዚያው ቆይቶ ጊዜ ከመፍጀት ይልቅ ሌሎች አማራጮች ለመፈለግ ተንቀሳቀስኩ። በአላማጣ በኩል በመኪና ወደ አዲስ አበባ መጓዝ እንደሚቻል ሰምቼ ስለነበር እርሱን ለመጣራት ወደ መናኸሪያ አመራሁ።
አስጎብኚዬ የሚያውቀው የመኪና ደላላ፤ ያሉትን አማራጮች ዘረዘርልኝ። ከመቐለ አዲስ አበባ በቀጥታ የሚጓዙ፣ እንደ “ሰላም ባስ” አይነቶቹ አውቶብሶች ስራ ጀምረው እንደሁ ጠየቅኩ። በትግራይ ውጊያ ሲጀመር በመቐለ ለመቆየት ተገድደው የነበሩት የተወሰኑ እንደዚህ አይነት አውቶብሶች፤ መንገዱ ክፍት ሲደረግ የተወሰኑ ሰዎችን ጭነው ከመሄዳቸው ውጭ አገልግሎት አለመጀመራቸውን ነገረኝ። አሁን በስፋት ሰው የሚጠቀምበት አማራጭ ከመቐለ አላማጣ በሚኒባስ መጓዝ እንደሆነ እና ከዚያ በኋላ አውቶብሶችም ሆኑ ሌሎች መጓጓዣዎች ቀላል መሆኑን አብራራልኝ።
ከመቐለ የሚነሱ እንደ ላንድክሩዘር ያሉ መኪኖች እስከ አላማጣ ድረስ በ700 ብር እንደሚጭኑ ጥቆማ ሰጠኝ። ዕድለኛ ከሆንኩም ሶስት ሺህ ብር በሚያስከፍሉ ላንድክሩዘሮች በቀጥታ አዲስ አበባ ድረስ መጓዝ እንደምችልም አነሳልኝ። ሶስት ሺህ ብር ከተከፈለ በወታደራዊ አንቶኖቭ አውሮፕላን ወደ አዲስ አበባ መጓዝ እንደሚቻል በከተማው ሲወራ መስማቴን ገለጽኩለት። ስለዚህ አሰራር ብዙም እውቀት እንደሌለው ጠንቀቅ ባለ መንፈስ ምላሽ ሰጠኝ።
አጋጣሚውን ካገኘሁ በሚል፤ ለደላላው ወደ ውቅሮ እና አዲግራት ስለሚጓዙ መኪኖች ሌላ ጥያቄ አቀረብኩ። ጠዋት ብመጣ ወደ ቦታዎቹ የሚጓዙ ሚኒባሶች መናኻሪያ አካባቢ እንደማገኝ አስረዳኝ። “እዚህ ድረስ መጥቼ ከሁለቱ ከተሞች ቢያንስ አንዱን ሳላይ አልመለስም” ብዬ ለራሴ ደጋግሜ ብነግርም፤ እቅዴን ያካፈልኳቸው ሰዎች በአካባቢዎቹ የስልክ አገልግሎት እስካሁንም አለመስራቱን እና የጸጥታ ስጋት እንዳለ በማንሳት ተጨንቀው አስጨንቀውኛል። “ቢያንስ በቋንቋ ማስተርጎም ይረዱኛል” በሚል አብረውኝ እንዲጓዙ የጠየቅኋቸው ሰዎችም፤ ለደህነንታቸው እንደሚሰጉ በመግለጽ ወደ ከተሞቹ ለመሄድ አሻፈረኝ ብለዋል።
ከእነዚህ መካከል አንዷ የሆነችው ወጣት ቤተሰቦቿ የሚኖሩት በአዲግራት ነው። ላለፉት ሁለት ወራት ድምጻቸውን ባለመስማቷ ተጨንቃለች። በአካባቢው በነበረው ውጊያ ጉዳት ይድረስባቸው፤ ወይም ይትረፉ የምታውቀው ነገር የለም። ይህንኑ ጭንቀቷን ለጓደኞቿ ጭምር በየጊዜው አካፍላለች። ወደ ከተማይቱ የሚጓዙ መኪኖች እንዳሉና ሰው ደርሶ መመለስ መጀመሩን ሲነገራት ግን ወደ ቦታው ለመሄድ እንደማትፈልግ ለመናገር አላቅማማችም። ምንልባት የገንዝብ ችግር ኖሮባት እንደሁ በሚል ወጪዋን ለመሸፈን ብስማማም፤ “አይሆንም” አለች። ምክንያቷን ስትጠየቅ “የኤርትራ ወታደሮች በከተማይቱ አሉ። ይገድሉኛል” የሚል ሆነ።
ይህን ከሰዎች ጋር ባወራሁ ቁጥር በየጊዜው ብቅ የሚለው የኤርትራ ወታደሮችን ጉዳይ፤ ያን ዕለት ከሰዓት በነበሩኝ ሁለት ቀጠሮዎች ላይ አንስቼ ነገሩን ከስረ መሰረቱ ማጣራት እንዳለብኝ ወስኜያለሁ። ከቀጠሮዎቼ በፊት ግን ትላንት ለመመልከት አስቤ፤ በጊዜ እጥረት ለዛሬ ያሳደርኩት የትምህርት ቤት ጉብኝትን መከወን አለብኝ። ወደ ትምህርት ቤቱ እየሄድኩ መቐለን በድጋሚ ተመለከትኳት።
መቐለ ከቅዳሜ እና እሁዱ የተሻለ እንቅስቃሴ ቢታይባትም፤ ወደ ቀደመ ድምቀቷ ግን አልተመለሰችም። አሁንም በርካታ የንግድ መደብሮቿ እና አገልግሎት መስጪያዎቿ ዝግ ናቸው። የመንግስት ስራ በቅጡ አልተጀመረም። በምግብ ቤቶች እና በኮፊ ሀውስ በረንዳዎች፣ በመንገድ ዳር ባሉ “የጀበና ቡና” መሸጫ ቦታዎች በርካታ ሰዎች ያለ ስራ ተቀምጠው ሲውሉ መመልከትም የተለመደ ሆኗል። ሰው ከዛሬ ይልቅ መጪውን ጊዜ በትዕግስት የሚጠብቅ ይመስላል።
በከተማይቱ የተለያዩ አካባቢዎች ያሉትን እኒህን መሰል ሁኔታዎች እየታዘብኩ ትምህርት ቤቱ ወደሚገኝበት አካባቢ ደረስኩ። የትግራይ ክልል ባንዲራ የተሳለበት የብሎኬት አጥር ጋር ስንደርስ ግቢው የትምህርት ቤቱ መሆኑን ገመትኩ። ግምቴን ያረጋገጠልኝ ግን ከላይ እስከታች ትልቅ ቀዳዳ ያበጀው የአጥሩ ክፍል ነው። የትምህርት ቤቱ አጥር በከባድ መሳሪያ ተመትቶ ጉዳት እንደደረሰበት አስቀድሜ ሰምቼ ነበር። ጉዳቱ ወደ መማሪያ ክፍሎቹ መሻገሩ ተገልጾልኛል። የተነገረኝን በአይኔ ተመልክቼ ለማረጋገጥ ወደ ቅጽር ግቢው ዘለቅሁ።
ከውጭ ሲገባ በመጀመሪያ የሚታየው የመማሪያ ክፍል ግድግዳ ላይ፤ ስለ ትምህርት ቤቱ ዝርዝር መረጃዎች የሚገልጽ ትልቅ ጹሁፍ ተለጥፏል። የትምህርት ቤቱ ስም ዓዲ ሽምድሑን ይሰኛል። የመጀመሪያ ደረጃ የመንግስት ትምህርት ቤት ነው። ከ1995 ዓ.ም. ጀምሮ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ በጽሁፉ ተጠቅሷል። በጸጥታ በተዋጠው ትምህርት ቤት ግቢ መሃል የእግር ኳስ መጫወቻ ሜዳ ይታያል። ከሜዳው ባሻገር አስር የመማሪያ ክፍሎችን የያዘ፣ ባለ አንድ ፎቅ ቢጫ ህንጻ በዛፎች ተከልሎ ቆሟል። ጉዳት የደረሰባቸው የመማሪያ ክፍሎች በዚህ ፎቅ ውስጥ እንደሚገኙ ተነግሮኝ ወደዚያው ተራመድኩ።
ከፍ ያለ ሽንቁር ያለበት የትምህርት ቤቱ አጥር፤ ከቢጫው ፎቅ የእርምጃዎች ርቀት ያህል ላይ እንደሚገኝ ተመለከትኩ። ለአጥሩ የሚቀርበው የፎቁ ግድግዳ እና የመጀመሪያው የመማሪያ ክፍል በከባድ መሳሪያ ፍንጥርጣሪዎች ተበሳስተዋል። በፎቁ የታችኛው ክፍል ያለው በረንዳ ከመስኮቶች በወረደ መስታወት ስብርባሪ ተሞልቷል። የመጀመሪያው ክፍል የተዘጋበትን መቀርቀሪያ አስከፍቼ ወደ ውስጥ ገባሁ። ከበር ጀምሮ ወለሉ በስብርባሪ ተሸፍኗል። በመስኮት ጥግ የሚገኙ ዴስኮችም እንዲሁ ስብርባሪው አርፎባቸዋል።
በአንደኛው ክፍል ያየሁት ይህ ትዕይንት መጠኑ የበዛ እና ያነሰ እንደሁ እንጂ፤ በአስሩም ክፍሎች የሚታይ ነው። ትምህርት ቤቱ ጉዳቱ በደረሰበት ቀን አገልግሎት እየሰጠ ቢሆን ኖሮ በተማሪዎች ላይ ይደርስ የነበረው ጉዳት ከፍተኛ ይሆን ነበር። በትምህርት ቤቱ ላይ የከባድ መሳሪያ አረሩ ያረፈው የመከላከያ ሰራዊት መቐለን በተቆጣጠረበት ቀን እንደነበር አንድ የትምህርት ቤቱ ሰራተኛ ነግረውኛል። በመቐለ ሰማይ ላይ ጄቶች ማንዣበብ ከጀምሮ አንስቶ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዳይመጡ በመነገሩ ምክንያት ጉዳቱ በደረሰበት ዕለት ተማሪዎች በቦታው እንዳልነበሩም አብራርተውልኛል።
የከባድ መሳሪያ ጥቃቱ በትምህርት ቤቱ ብቻ ሳይሆን በአቅራቢያው ባሉ መኖሪያ ቤቶች ላይ ጭምርም ማረፉን የነገሩኝ እኚህ የአይን ምስክር፤ በዚህም ሳቢያ አምስት ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል ብለዋል። በዚህ አካባቢ በአንድ መኖሪያ ቤት የደረሰውን ጉዳት የሚያሳይ ቪዲዮ እና ፎቶዎች ተመልክቻለሁ። የቤቱ ባለቤቶች ሁኔታውን ለእንግዳ ሰው ለማሳየት እምብዛም ደስተኛ እንዳልሆኑ ስለተነገረኝ ግን በአይኔ ሳልመለከተው ብቀርም ጥቃቱ ከፍ ያለ ጉዳት ያደረሰ እንደሆነ ከምስሎቹ ተረድቻለሁ።
* * *
የሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን አጋማሽ በመቐለ የተለያዩ ቦታዎች ስዞር ተገባድዷል። ለከሰዓት ሁለት ቀጠሮዎች ይዤያለሁ። በእነዚህ ቀጠሮዎቼ ስለ ኤርትራ ወታደሮች ተጨማሪ መረጃ ለማሰባሰብ አቅጃለሁ። የመጀመሪያው ቀጠሮዬ የነበረው “ኤሊት” ከሚባሉ፤ ከተማሩ የከተማይቱ ወጣቶች ጋር ነበር። ወጣቶቹ የኤርትራን ወታደሮች እንዴት እንደለዩዋቸው በምሳሌዎች ሊያስረዱኝ ጣሩ። ወጣቶቹ የኤርትራ ወታደሮችን በቀላሉ በአለባበሳቸው እና ጫማቸው መለየት ይቻላል ባይ ናቸው። በትግርኛ ቋንቋ ሲነጋገሩ የሚጠቀሟቸው ቃላት እና ዘዬአቸውም ሌላው ወታደሮቹን የሚለዩባቸው ባህሪያት እንደሆኑም ይናገራሉ።
የኤርትራ ወታደሮች የሚጫሟቸው፤ በተለምዶ “የታጋዮች” ተብለው የሚታወቁትን የኮንጎ ላስቲክ ጫማዎችን ነው። በኤርትራ “ሽዳ” ተብሎ የሚጠራው ይሄ ጫማ፤ ሀገሪቱ ለነጻነት ባደረገችው ትግል ህይወታቸውን ላጡ ታጋዮች ተምሳሌትነት፤ በሃውልት መልክ ተሰርቶ በአስመራ ከተማ አደባባይ ላይ ጭምር ቆሞ ነበር።
የኤርትራ ወታደሮች እንደ ሽረ፣ ሽራሮ፣ ዛላምበሳ አካባቢ ባሉ ቦታዎች የራሳቸውን የደንብ ልብስ ጭምር ለብሰው እንደሚንቀሳቀሱ፤ ከአካባቢው የመጡ የዓይን እማኞችን ጠቅሰው ወጣቶቹ ያስረዳሉ። የደንብ ልብሳቸውን በማያደርጉባቸው ጊዜ የሚጠቀሟቸው የተዘበራረቁ አለባበሶች ሌላ መለያቸው እንደሆኑም ያብራራሉ።
ከወጣቶቹ ውስጥ ሁለቱ፤ ከላይ የኢትዮጵያን የመከላከያ ሰራዊት የደንብ ልብስ የለበሱ፤ ሱሪያቸው ደግሞ የኤርትራ መከላከያ ሰራዊት የሆነ ወታደሮች በመቐለ ከተማ መመልከታቸውን ነግረውኛል። የኤርትራ ወታደሮች በከተማይቱ ይታዩ የነበሩት፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት መቐለ ከተማን ከተቆጣጠረ በኋላ በነበረው የመጀመሪያ ሳምንት እንደነበርም ገልጸውልኛል።
ወታደሮቹ አላፊ አግዳሚውን መታወቂያ ሲጠይቁ የሚጠቀሙበት “ቲሴራ” የሚል ቃል በኤርትራ እንጂ ፤ በትግራይ እምብዛም ጥቅም ላይ እንደማይውል በምሳሌነት የሚያነሱት ወጣቶቹ፤ እነዚህን መሰል የቋንቋ ልዩነቶች ከሌሎች ምልክቶች ጋር ተደማምረው የወታደሮቹን ማንነት ቁልጭ አድርገው እንደሚያሳዩ ይሞግታሉ። “ቲሴራ” የጣሊያንኛ ቃል ሲሆን ቀጥተኛ ትርጉም “ካርድ” የሚል ነው። በኢትዮጵያ ቃሉ ጥቅም ላይ ሲውል የሚደመጠው የእግር ኳስ ተጨዋቾች መታወቂያን ለመግለጽ ነው። ተጨዋቾቹ መታወቂያውን የሚያገኙት ከእግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ነው።
የኤርትራ ወታደሮችን በፍተሻ ወቅትም ሆነ በሌሎች አጋጣሚዎች አግኝተው ያነጋገሩ ሰዎች ሌሎች ነገሮች መታዘባቸውንም ወጣቶቹ ይናገራሉ። የግድያ፣ ሴቶችን የመድፈር፣ የደረሰ እህል የማቃጠል እና ሌሎች መሰል ዘግናኝ ድርጊቶችን በአብዛኛው የሚፈጽሙት ከኤርትራ ቆላማው ስፍራ የመጡ ወታደሮች መሆናቸውን ያስረዳሉ። ፊታቸው ላይ ባሉ ምልክቶች፣ እርስ በእርስ በሚነጋገሩባቸው ቋንቋዎች ይለያሉ የተባሉት እነዚህ ወታደሮች የራሺዳ፣ ሳሆ፣ ብሌን፣ ቤኒ አሚር ተወላጆች ናቸው ባይ ናቸው። ከደጋው የኤርትራ አካባቢ የመጡት ወታደሮች በአብዛኛው በዘረፋ ላይ እንደሚሰማሩ መስማታቸውን የሚናገሩት ወጣቶቹ፤ አንዳንዴም የሚፈጸሙ ዘግናኝ ድርጊቶችን ለማስቆም እንደሚሞክሩ ይጠቁማሉ።
ከዚህ ቀደም በትግራይ በነበሩኝ ቆይታዎች፤ የኤርትራ እና የትግራይ ህዝብ እንዴት በቤተሰብ ደረጃ የተሳሰረ እንደሆነ ሲተነተን እሰማ ለነበርኩት ሰው፤ ከውጊያ ተሳትፎ ባሻገር በሀገሪቱ ወታደሮች ተፈጸሙ የተባሉ ነገሮች ግር የሚያሰኙ ሆነውብኛል። ኤርትራ እና ኢትዮጵያ በይፋ ሰላም ከማውረዳቸው በፊት በነበሩት ዓመታት፤ እንደ አዲግራት ያሉ ከተሞች በድንበር መዘጋት ምክንያት እንዴት እንደተጎዱ ይቆጩ የነበሩ የትግራይ ሰዎች በርካቶች ነበሩ። ያኔ በቤተሰቦቻቸው የሰርግ እና የቀብር ስነርዓቶች ላይ ለመገኘት፤ በሁለቱ ሀገራት ወታደሮች ከታጠረው ድንበር መሹለኪያ ተፈልጎ ሰዎች ይገናኙ እንዳልነበር፤ ዛሬ እኒህን መሳይ ድርጊቶች እንዴት በኤርትራ ወታደሮች ሊፈጸም ቻለ?
ወጣቶቹ ለዚህ ጥያቄዬም እየተቀባበሉ ምላሽ ሰጥተውኛል። “ኤርትራ አሁን ላለችበት ደካማ የኢኮኖሚ ሁኔታ እና ድህነት ትልቁ ምክንያት በመለስ ዜናዊ እና በህወሓት አማካኝነት የተከፈተባት ጦርነት እንደሆነ” ለወታደሮቹም ሆነ ለቀረው ህዝብ በኤርትራ ባለስልጣናት ሲነገረው መቆየቱን ወጣቶቹ ያስታውሳሉ። የኢትዮ-ኤርትራ ድንበር በተከፈተ ወቅት ወደ ትግራይ መጥተው የህዝቡን እና የአኗኗሩን ሁኔታ የተመለከቱ የኤርትራ ዜጎች በእርግጥም እነርሱ ያሉበት ሁኔታ የቆረቆዘ እንደሆነ ከተነገራቸውም በላይ በዓይናቸው አይተው ማረጋገጣቸውን ይጠቅሳሉ። ይህን በልባቸው ይዘው የቆዩ ኤርትራውያን ወታደሮች ጊዜ ጠብቀው “የብቀላ እርምጃ ወስደዋል” ይላሉ።
በመቐለ ያገኘኋቸው አብዛኞቹ ሰዎች የነገሩኝ እና ወጣቶቹም በሙሉ ሀሳብ የሚስማሙበት አንድ ጉዳይ አለ- “የኤርትራ ወታደሮች የሚፈጽሟቸውን ግድያዎችንም ሆነ ዘረፋዎች የኢትዮጵያ መንግስትም ለማስቆም አልቻለም” የሚል። ይህ ጉዳይ ለብዙዎች “የእግር እሳት” እንደሆነባቸው በስሜት ተውጠው ከሚያቀርቧቸው ገለጻቸው ተረድቻለሁ። በቀረው የኢትዮጵያ ክፍል ያለው ህዝብም፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ድምጹን አምርሮ ባለማሰማቱ ጥልቅ የመከፋት ስሜት እንዳለ ተመልክቻለሁ። “ህዝብ ማለት መሬቱ ብቻ አይደለም። ሰውም ጭምር ነው” የምትለው አንድ ወጣት “ኢትዮጵያውያን የሚፈልጉት መሬቱን እንጂ እኛን አይደለም” ስትል እንባ በሚተናነቀው ድምጽ ነግራኛለች።
የኤርትራ ወታደሮች ጉዳይ፤ በወጣቶቹ እንዲህ ቢብራራልኝም የበለጠ ማረጋገጫ ለማግኘት ሌላ አካል መፈለግ ነበረብኝ። ለዚህ ደግሞ ሁነኛው ሰው፤ ከዚህ ቀደም የማውቀቸውና አሁን ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር በቅርበት የሚሰሩ ሰውን ነው። በቀጠሮዬ መሰረት ሳገኛቸው ከጉዳዩ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎቼን አዥጎደጎድሁ። የኤርትራ ወታደሮች በእርግጥም በትግራይ ክልል ውጊያ ተሳትፈው እንደሆነ፣ ፈጽመዋቸዋል ስለሚባሉ ግድያዎች እና ዝርፊያዎች፣ አሁንም በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች እየተንቀሳቀሱ ስለመሆኑ ጠየቅሁ። ለሁሉም ጥያቄዎቼ ያገኘሁት ምላሽ “አዎ” የሚል ነበር።
እኚሁ ምንጭ እስካነጋገርኳቸው ቀን ድረስ በደህንነት ስጋት ምክንያት ከመቐለ ከተማ ውጪ ወዳሉ አካባቢዎች መጓዝ ባይችሉም፤ በተለያዩ የክልሉ አካባቢ ያሉ ሰዎች ወደ ዋና ከተማይቱ በሚመጡበት ጊዜ ያለውን ሁኔታ ከአንደበታቸው ለመረዳት ዕድል አግኝተዋል። በገጠር ያሉ ቤተሰቦቻቸው ከባዱን ጊዜ እንዴት እንደተወጡትም ከዚያ መልዕክት ይዘው የመጡ ሰዎች አጫውተዋቸዋል። ከዚህ ሁሉ በላይ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ባለስልጣናት የሚያገኙት አስተማማኝ መረጃ አለ። በዚህ መልክ ያሰባሰቧቸውን መረጃዎች፤ ራሳቸው በዓይን እማኛነት ከተመለከቱት ጋር በማቀናጀት ነበር የሆነውን ሁሉ የሚዘረዝሩልኝ።
እንደ እርሳቸው ገለጻ ከሆነ፤ የኤርትራ ወታደሮች በባድመ- ሽራሮ-ሽረ-አክሱም እንዲሁም በዛላምበሳ- አዲግራት ግንባር በኩል ወደ መቐለ ሲገሰግስ ከነበረው የመከላከያ ሰራዊት ጋር አብረው በውጊያ ተሳትፈዋል። በአላማጣ-ኮረም እና በመኾኒ- ጨርጨር ግንባር በኩል የነበረው ግን ሙሉ በመሉ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትን ብቻ ያሳተፈ መሆኑን፤ እኚሁ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የቅርብ ምንጭ አስረድተውኛል። የኤርትራ ወታደሮች አሁንም በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች እንደሚገኙ እና ድንበር አቅራቢያ ባሉ ቦታዎች ላይም ባንዲራቸውን ጭምር እንደተከሉ ከተለያዩ ሰዎች የሰማሁትን መረጃ አረጋግጠውልኛል።
ኤርትራውያን ወታደሮች በተለያዩ አካባቢዎች በጅምላ ሰዎችን መግደላቸውን የሚጠቅሱት የጊዜያዊ አስተዳደሩ ምንጭ፤ በአክሱም፣ በውቅሮ እና ዕዳጋ ሐሙስ ይህን መሰል ድርጊት እንደተፈጸመ ይዘረዝራሉ። አዲግራት አቅራቢያ በምትገኘው ዕዳጋ ሐሙስ 86 ሰዎች መገደላቸውን ወደ ቦታው ከተጓዘ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ሰው መስማታቸውን ያክላሉ። በዚያ ቦታ ተገደሉ የተባሉ ሰዎች ብዛትን በተመለከተ የተለያዩ ሰዎች የተለያዩ ቁጥር ሲጠቅሱ ሰምቻለሁ። አንዳንዶች የሟቾቹን ቁጥር “120 ነው” ሲሉ፤ ሌሎች ደግሞ “150 ይደርሳል” ይላሉ። እንደ ልብ ተንቀሳቅሶ፣ በርካታ የዓይን እማኞች አነጋግሮ፣ ሌሎች አጋዥ መረጃዎችን አሰባስቦ፤ መረጃዎችን ለማጣራት በማይቻልበት ይህን መሰሉ ሁኔታ፤ በእንዲህ አይነት የተራራቁ አሃዞች መወዛገብ አይቀሬ ነው።
የጊዜያዊ አስተዳደሩ ምንጭ፤ ቤተሰቦቻቸው የሚገኙበት የእርሳቸው የትውልድ ስፍራ፤ የከፋ ዘረፋ ከተፈጸመባቸው ቦታዎች አንዱ እንደሆነ ያስረዳሉ። ወደ እርሳቸው እህት ቤት የገቡ የኤርትራ ወታደሮች ዱቄት ሳይቀር ዘርፈው መውሰዳቸውን መስማታቸውን ይናገራሉ። በግለሰብ ቤቶች፣ በንግድ ተቋማት እና በተሽከርካሪዎች ላይ ከደረሰው ዘረፋ ባሻገር ፋብሪካዎች ላይም ተመሳሳይ ድርጊት መፈጸሙን ይገልጻሉ። “እኔ ከሁሉ የሚገርመኝ ነገር በር እየገነጠሉ የሚወስዱት ነገር ነው። ኤርትራውያን ወታደሮች እና በር ያላቸው ቁርኝት መጠናት አለበት” ሲሉም ስላቅ የቀላቀለ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ከወጣቶቹ እና ከመረጃ ምንጬ ጋር የነበረኝን ቆይታ ሳጠናቅቅ፤ በቀጣዩ ቀን ቢያንስ እስከ ውቅሮ ድረስ እንኳ ተጉዤ የተባሉትን ነገሮች በአይኔ ለመመልከት ከውሳኔ ላይ ደረስኩ። ውቅሮ አቅራቢያ አሁንም ድረስ ውጊያ እንዳለ ሰምቻለሁ። ከውቅሮ ታጥፎ ወደ ገጠር በሚወስደው መንገድ ያለው አጽቢ ወንበርታ የተባለው አካባቢ በትግራይ ሚሊሺያ ቁጥጥር ስር እንዳለና ቦታውም “ሃራ መሬት” መሆኑ በመቐለ ይወራል። ህወሓት ከደርግ ጋር በትጥቅ ትግል ላይ በነበረበት ወቅት፤ ከወታደራዊው አገዛዝ የሚያስለቅቃቸውን ቦታዎች “ሃራ መሬት” በሚል ይጠራቸው እንደነበር ከመጽሐፍት ላይ አንብቤያለሁ። ትርጉሙ “ነጻ መሬት” ማለት እንደሆነም ተነግሮኛል። በመንገድ ላይ አለ የሚባለው የጸጥታ ሁኔታ ምንም አስጊ ቢሆን ግን ወደ ውቅሮ እና አካባቢው ነገ ለመሄድ ቆርጬያለሁ።
ክፍል ሶስትን ለማንበብ ይህን ሊንክ ይጫኑ https://ethiopiainsider.com/2021/2461/
የዚህን ልዩ ዘገባ ቀዳሚ እና የመጨረሻ ክፍሎች ለማንበብ ተከታዩቹን ሊንኮች ይጫኑ፦
ክፍል አንድ – https://ethiopiainsider.com/2021/2374/
የመጨረሻ ክፍል – https://ethiopiainsider.com/2021/2514/