– የአዲግራት የሁለት ሰዓታት ቆይታ
– የትግራይ ተጓዦች በአዲስ አበባ ፖሊስ ጣቢያ ምን ገጠማቸው?
በተስፋለም ወልደየስ
ዕኩለ ቀን ሆኗል። ቢጫና ነጭ ቀለም የተቀቡት እና በዋናው መንገድ መሃል ባለው አካፋይ ላይ በተርታ የተተከሉት የአዲግራት የመንገድ መብራቶች አይን ይስባሉ። በመንገዱ ላይ የሚታዩት መኪኖች ቁጥር አነስተኛ ነው። በመንገድ ዳር ቆመው ተሳፋሪ የሚጠብቁ ባጃጆች አለፍ አለፍ ብለው ይታያሉ። በከተማይቱ ዳርቻ ያለውን ይሄን መሰሉን ነገር እያስተዋልኩ እያለ መኪናችን ድንገት ቆመ። ከእኛ ጋር በስተኋላ ተቀምጣ የነበረችውና ከዕዳጋ ሐሙስ በኋላ ወደ ጋቢና የተዛወረችው ወጣቷ ተሳፋሪ ነበረች መኪናውን ያስቆመችው። ለሹፌሩ የቤተሰቦቿን ቤት አቅጣጫ ከጠቆመችው በኋላ ከዋናው መንገድ ታጥፈን ወደ ውስጥ ገባን።
ዝምተኛዋን ወጣት ተጓዥ አውርደን ወደ ዋናው መንገድ ተመለስን። ብዙም ሳንሄድ አጠገቤ የተቀመጠው የጋራዥ ሰራተኛ “ተመልከት የኤርትራ ወታደሮች” አለኝ። አይኖቼ የመንገዱን ግራ እና ቀኝ በፍጥነት አሰሱ። በቀላሉ ልለያቸው አልቻልኩም። “እነዚያውልህ” ብሎ ወጣቱ ከመኪናችን በተቃራኒ አቅጣጫ ወደ እኛ ፊታቸውን አድርገው የሚጓዙ ሁለት ሰዎች አሳየኝ። ከመቅጽበት እጄ ላይ የነበረውን ሞባይሌን ወደ እነርሱ አቅጣጫ ለመደገን ሳነሳ፤ አጠገቤ የተቀመጠችው ተለቅ ያለችው ሴት እጄን አፈፍ አድርጋ ይዛ ከመቀመጫው ጋር ጠፍንጋ ያዘችው። “ስታነሳ ቢያዩህ ይገሉናል” በማለት በአይኖቿ ጭምር ፎቶ እንዳላነሳ ለመነችኝ። የሰው ህይወት አደጋ ላይ ከማጋለጥ ቢቀርብኝ ይሻላል ብዬ በእሺታ አንገቴን አወዛወዝኩላት።
በዚህ ምክንያት ፎቷቸውን ማንሳት ባልችልም፤ በነጻነት ዘና ብለው በመንገድ ዳር እያወጉ የሚጓዙትን ሁለት ወታደሮች ግን አተኩሬ ነገረ ስራቸውን ከመመልከት የከለከለኝ አልነበረም። ሁለቱም አረንጓዴ ወታደራዊ ልብስ ለብሰው፤ ጠመንጃቸውን በትከሻቸው አንግበዋል። ወታደራዊ የደንብ ልብስ አለባበሳቸው እንደነገሩ ነው። ከወታደር ይልቅ ታጣቂ ይመስላሉ። የተጫሙት ያው ከመቐለ ጀምሮ ስሰማው የነበረው፤ በተለምዶ የታጋዮች ጫማ የሚባለው የኮንጎ ላስቲክ ጫማ ነው። መኪናችን አልፋቸው እስክትሄድ ድረስ ስመለከታቸው ቆየሁ።
ሹፌራችን ወደ ከተማ መሃል በመንዳት ፈንታ፤ ዋናውን መንገድ ተከትሎ በቀጥታ ወደ ተዘረጋው ኮብል ስቶን ሲያመራ ቀልቤን ሰብስቤ ቀጣዩን ነገር መከታተል ቀጠልኩ። አጠገቤ የተቀመጠችው ሴት ለሹፌሩ አቅጣጫ እያመላከተቸው ወደ ቤተሰቦቿ ቤት አቀናን። በመንገዳችን ላይ በነበረን ጨዋታ፤ ሴትዮዋ የቤተሰቦቿ ሁኔታ በጣም እንዳሳሰባት ተረድቻለሁ። በትግራይ ውጊያ ተጀምሮ የስልክ አገልግሎት ከተቋረጠ አንስቶ የቤተሰቦቿን ደህንነት ማወቅ ባለመቻሏ ተጨንቃለች። መኪናችን ቤታቸው ደጃፍ ደርሶ ሲቆም፤ ውቅሮ ላይ ለቤተሰቦቿ በፌስታል የገዛችውን ቆሎ አንጠልጥላ እመር ብላ ወረደችና የውጭውን በር አንኳኳች።
መንገድ ዳር ቆመው የነበሩ ጎረቤቶቿ የሆኑ አራት እናቶች፤ እርሷን ሲመለከቱ የተገረሙ መሰሉ። የናፍቆቷን ያህል እያንዳንዳቸውን እያገላበጠች ሳመቻቸው። በር እንድትከፍት የተላከች ታዳጊ ልጅ ከእኛ ጋር የመጣችውን ሴት ስትመለከት፤ ስሟን እያነሳች፣ መምጣቷን በሚያበስር ከፍ ያለ ድምጽ ቤተሰቦቿን መጣራት ጀመረች። የሴትዮዋ እህት የሰሙትን ባለማመን ተንደርድረው ወደ በር ወጡ። ከዚያ በኋላ ለደቂቃዎች ተቃቅፎ መላቀስ ሆነ። በሁሉም ፊት ላይ የናፍቆት እና የስጋት ሰቀቀን ይነበባል።
ሰላምታው እና “እንዴት ነሽ” መባባሉ ጋብ ሲል፤ “መቐለ እንዴት ነች? እናንተ እንዴት ናችሁ” የሚል ጥያቄ ተከተለ። አብራን የተጓዘችው ሴት ለቤተሰቧ ስትሰጋ እንደከረመችው ሁሉ፤ እነርሱም የእርሷ ነገር ሲያስጨንቃቸው ነው ጊዜውን የፈጁት። የትግራይ ሰው የራሱን አካባቢ አስጨናቂ ነገር ወደ ጎን አድርጎ፤ የሌላውን ደህንነት የሚያጠያይቀው ነገር በተለያየ ቦታ ገጥሞኛል። ራሳቸው ያሉበትን ሁኔታ በአንጻራዊነት እንደተሻለ የሚወስዱት የየከተሞቹ ነዋሪዎች፤ ሀሳባቸው የጸጥታም ሆነ ሌሎች ችግሮች ጸንቶባቸዋል ብለው ለሚያስቧቸው ቦታዎች ነው። ለሴትዮዋ ቤተሰቦች በመቐለ ሁሉም ነገር ሰላም መሆኑ ከተነገራቸው በኋላ፤ “ምሳ ብሉ፤ ቡና ጠጡ” ሲሉ ጋበዙን። “ከተማ ጉዳይ አለን” በሚል ሰበብ ተሰናብተን ወደ መሃል ከተማ ሄድን።
በከተማ መሃልም ሆነ ከዚያ በኋላ ባሉ መንገዶች ስንዘዋወር ያስተዋልኩት ነገር፤ ከመቐለ ጀምሮ ባሉ ከተሞች ላይ የሚታየው መፋዘዝ በአዲግራት ላይ ጎልቶ እንደሚታይ ነው። በርካታ መኪኖችን የሚያስተናግዱት መንገዶቿ ላይ የሚታዩት ተሽከርካሪዎች በቁጥር አነስተኛ ናቸው። በትግራይ ክልል የነበረው ውጊያ መጠናቀቁ በይፋ ከተነገረ ከወር በኋላም በርካታ አገልግሎት መስጪያዎች እና የንግድ መደብሮች በራቸውን እንደጠረቀሙ ናቸው። ጭርታው ብርቱ ነው።
በአዲግራት በመንገዴ ላይ እንዳየኋቸው ከተማዎች የውጊያው ጉልህ ምልክቶች አይታዩም። የተቃጠሉ ወይም የተጎዱ ተሽከርካሪዎችም አልተመለከትኩትም። ምናልባት እኔ ከመድረሴ በፊት በነበሩት ጊዜያት ተነስተው እንደው አላውቅም። በመጀመሪያ አፍታ፤ በጨረፍታ የቃኘኋቸው በከተማይቱ ያሉ ህንጻዎች የመስታወት መሰባበር ቢያጋጥማቸውም በአንጻራዊነት በደህና ሁኔታ ላይ ያሉ ይመስላሉ።
አዲግራትን ከምሳ በኋላ ይበልጥ ተዟዙሮ ለመመልከት እቅድ ይዤ፤ ሹፌሩን እና የጋራዥ ሰራተኛው “ጥሩ ምግብ አለበት” ወዳሉበት ቦታ አብሬያቸው ሄድኩ። ወደ ምግብ ቤቱ የሚወስደው፤ የኮብል ስቶን መንገድ በመሃል ከተማ ካየሁት ይልቅ በተሻለ እንቅስቃሴ ያለበት ነው። በርከት ያሉ ባጃጆች በመንገዱ ላይ ይመላለሳሉ።
ከመንገዱ ግራና ቀኝ ባሉ እና በተዘጉ የንግድ መደብሮች ደጃፍ፤ አልባሳት እና ሌሎች ሸቀጦችን የደረደሩ ነጋዴዎች በቁጥር በርከት ብለው ይታያሉ። ዘንቢል እና ፌስታል ያንጠለጠሉ ሸማቾች ቁጥርም የሚናቅ አይደለም። ቦታው የከተማይቱ ዋና የመገበያያ ቦታ እንደሆነ የጋራዥ ሰራተኛው ነገረኝ። እኛ ወደ ቦታው ከመሄዳችን ከሁለት ሳምንት በፊት ግን ይሄም አካባቢ በጭርታ የተዋጠ እንደነበር አከለልኝ።
ገበያው ጎን ካለው፤ ለምሳ ከተመረጠው ምግብ ቤት ደጃፍ መኪናችንን ስናቆም፤ አንድ ሸበቶ አባት ወደ መኪናችን ተጠጉና ከሹፌራችን ጋር በትግርኛ ወግ ጀመሩ። ከሹፌራችን ጋር ለደቂቃዎች ሲጠያይቁ ቆይተው፤ አንድ ነገር ለማሳየት ከደረት ኪሳቸው የማስታወሻ ደብተራቸውን መዘዙ። ለካንስ እንደምንጓዝባት መኪና አይነት ተሽከርካሪያቸው በኤርትራውያን ወታደሮ ተወስዶባቸው፤ በመንገድ ላይ አይተናት እንደሆነ እየጠየቁ ነው። ማስታወሻ ደብተራቸው ደግሞ የመኪናቸው የታርጋ ቁጥር ተመዝግቦ የተያዘባት በመሆኗ፤ ከዚያ ላይ እያነበቡ ለእኛ ለማስገልበጥ ነበር አወጣጣቸው። በአዲግራት የስልክ አገልግሎት ባይኖርም፤ ድንገት በቀጣይ ቀናት ከተከፈተ ያየነውን እንድንነግራቸው ስልክ ቁጥራቸውን አጻፉን።
ብርማ ቀለም እንዳለው የነገሩን መኪናቸው፤ በኤርትራውያን ወታደሮች ከተወሰደ በኋላ እስከ ዕዳጋ ሐሙስ ባለው መንገድ ሲመላለስ እንደከረመ ያዩ ሰዎች ነግረዋቸዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን መኪናውን አየሁ የሚል በመጥፋቱ፤ እንደ እኛ መኪና ሹፌር አይነት ሰው ሲያገኙ እያቆሙ ይጠይቃሉ – “መኪናዬን በመንገድ አይታችኋታል?” እያሉ።
ኤርትራውያን ወስደዋቸዋል ስለሚባሉ መኪናዎች ጉዳይ ብዙ ሰምቻለሁ። ወደ አዲግራት እየመጣን እያለ፤ ሹፌራችን እና የጋራዥ ሰራተኛው አንድ ሲኖትራክ መኪና በመንገድ አይተው እንዴት በመደነቅ ሲነጋገሩ እንደነበር አይቻለሁ። ምን እንዳስገረማቸው ብጠይቃቸው፤ ወደ ኤርትራ ከመወሰድ የተረፈ ሲኖትራክ በማየታቸው እንደሆነ ነግረውኝ ነበር። ሸበቶውን አባት ተሰናበተን ከምግብ ቤት አረፍ እንዳልን ሹፌሩ እና የጋራዥ ሰራተኛው የእነርሱም መኪና ከመወሰድ የተረፈችው በሰዎች ጥረት እንደሆነ እየተቀባበሉ ያጫውቱኝ ገቡ።
ውጊያው የተጀመረ ሰሞን በአዲግራት የነበረው ሹፌራችን፤ ለክፉም ለደጉም በሚል መኪናውን ቤተክርስቲያን አቁሟት ወደ መቐለ ይጓዛል። ዝርፊያም ሆነ ሌላ ነገር ቢፈጠር ድርጊቱን የሚፈጽሙ ሰዎች “ቤተክርስቲያንን አይደፍሩም” በሚል እሳቤ ነበር ይህንን ማድረጉ። ውጊያው አብቅቶ፣ መንገድ ሲከፈት፤ መኪናውን ፍለጋ ከጋራዥ ሰራተኛው ጋር ወደ አዲግራት ተመልሶ ይመጣል። መኪናውን ጠብቀው ያቆዩለት የሃይማኖት አባቶች፤ የኤርትራ ወታደሮች ከአንድም ሶስት ጊዜ መኪናዋን ሊወስዱ መምጣታቸውን እና በስንት እግዚኦታና ልመና ድርጊቱን ሳይፈጽሙት መቅረታቸውን እንደነገሩት አጫውቶኛል።
በአዲግራት ከተማ እንደልብ የሚንቀሳቀሱ መኪናዎች፤ ኤርትራውያን ከየሰው ላይ የወሰዱት እንደሆነ ሁለቱም አስረድተውኛል። ከምሳ በኋላ ከተማዋን ለማየት ዞር ዞር ባልንበት ጊዜም፤ የከተማይቱ ነዋሪዎች መኪናችንን በጥርጣሬ ሲመለከቱ አስተውያለሁ። በዚህ ሁኔታ መገረሜን ያየው ሹፌራችን፤ በውስጥ ለውስጥ ባሉ መንገዶች መኪናዋን አቁሞ ወጪ ወራጁን ሲያነጋግር፤ የሚያሳዩትን ገጽታ እንድመለከት ጋበዘኝ። ሹፌራችን የትግርኛ ቃላት ሲወረውር፤ በእርግጥም በመኪናዋ ውስጥ ያለነው ሰዎች ኤርትራውያን መስለናቸው ሲደነብሩ አይቻለሁ። እንዲህ ውስጥ ለውስጥ እያሳበረን ወደ አዲግራት ዩኒቨርስቲ የሚወስደው የኮብል ስቶን መንገድ ላይ ወጣን።
ዩኒቨርስቲው በከተማይቱ በኤርትራውያን ወታደሮች ከፍተኛ ዘረፋ ከተፈጸመባቸው ቦታዎች አንዱ እንደሆነ ተነግሮኛል። ወታደሮቹ ፍራሽ ሳይቀር ከዩኒቨርስቲው ዘርፈው መውሰዳቸውን ከሶስት የተለያዩ ሰዎች ሰምቻለሁ። በአዲግራት ሆቴሎችን ጨምሮ በርካታ የንግድ ተቋማት መዘረፋቸውን ብሰማም፤ ባለው የጸጥታ ሁኔታ እና በነበረኝ የጊዜ እጥረት ምክንያት በአይኔ ተመልክቼ ያረጋገጥሁት ጥቂቶቹን ብቻ ነው። ከዋና መንገዶች አቅራቢያ ባሉ ቦታዎች፤ ውስጥ ለውስጥ በተዘዋወርኩባቸው አፍታዎች እንደ ሞባይል ቤት ያሉ ዘረፋ የተፈጸመባቸው የንግድ መደብሮች አይቻለሁ።
ወደ አዲግራት ዩኒቨርስቲ ቅጽር ግቢ ከሚያስገቡ በሮች ወደ አንደኛው ስንጠጋ በጥበቃ ላይ ያለ የመከላከያ ሰራዊት አባል ተመለከትኩ። በአካባቢው ብዙም እንቅስቃሴ የለም። ህንጻዎቹን አሻግሬ ተመለከትኩ። ሁሉም ነገር ጸጥ ብሏል። ከዩኒቨርስቲው በር ትይዩ ያለው የወጋገን ባንክ የወልዋሎ ቅርንጫፍ የማስታወቂያ ሰሌዳ፤ ከተሰቀለበት ተገንጥሎ ወርዶ የበረንዳውን መሬት ነክቷል።
ሌሎች የከተማይቱን ክፍሎች ለመመልከት ከዩኒቨርስቲው ደጃፍ ተንቀሳቀስን። ከአክሱም አቅጣጫ ወደ ከተማይቱ የሚያስገባውን መንገድ ተከትለን ዙሪያ ገባውን መቃኘት ቀጠልን። እስከ ከተማይቱ መሃል የተዘረጋውን መንገድ በብቸኝነት የተቆጣጠሩት ባጃጆች ናቸው። የእነርሱም ቁጥር ቢሆን ከዚህ ቀደም ከነበረው ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ የሚባል ነው። በዚህኛው የመንገድ ክፍል ዳር ያሉ የንግድ መደብሮች፣ ባንኮች እና ሌሎች ቤቶች ሙሉ ለሙሉ እንደተዘጉ ናቸው።
ጠንካራውን ጸሀይ ተቋቁመው በእግራቸው የሚጓዙ የከተማይቱን ነዋሪዎች እየተመለከትን ወደ መሃል ከተማ በመመለስ ላይ ሳለን፤ አራት የፌደራል ፖሊስ የደንብ ልብስ የለበሱ ፖሊሶችን ከአንድ ህንጻ ስር አየሁ። እስካሁን በዞርኩባቸው የከተማይቱ ክፍል ያየኋቸው ወታደሮች እና ፖሊሶች ከአምስት አለመብለጣቸው አስገርሞኛል። ይህ ገረሜታዬ አብሮኝ የቆየው ግን ተጨማሪ አራት የኤርትራ ወታደሮችን እስከተመለከትኩበት አፍታ ድረስ ነው። ወታደሮቹን በአንድ ላይ የመመልከት ዕድል ያገኘሁት ባልተጠበቀ አጋጣሚ ነው።
ሹፌራችን ወደ መቐለ የሚሄዱ ተጨማሪ ተጓዦች ለማግኘት በመፈለግ ወደ ከተማይቱ መናኸሪያ የሚወስደውን መንገድ ደጋግሞ ይዞረዋል። መዞሩ ሲታክተው፤ መናኸሪያው አቅራቢያ ካለ እና ከፍ ብሎ የተሰራ በረንዳ ካለው ካፌ አጠገብ ሄዶ ያቆማል። የመኪናውን መሪ እንደያዘ፤ በመስኮት ጭንቅላቱን አውጥቶ ከወጣት የመኪና ደላላዎች ጋር ይነጋገራል፤ ተጓዥ የመሰሉትን አልፎ ሂያጆችንም ያግባባል። ከተማውን እንደልብ ለመመልከት በሚል ከጋቢና ከተቀመጥሁ ቆይቻለሁ። ከጋቢናው ውስጥ ሆኜ ፊት ለፊታችን ካለው በረንዳ ላይ የተቀመጡትን ሰዎች አስተውላለሁ።
“ ‘የኤርትራ ወታደሮች ናቸው እንዴ?’ ብዬ ራሴን ጠይቄ ሳልጨርስ፤ ካፌ በረንዳ ላይ ተቀምጠው የነበሩት ሁለቱ ሰዎች ሲነሱ ጫማቸው ታየኝ። ሚሊሺያ የመሰለኝም፤ የሲቪል ልብስ የለበሰውም የተጫሙት የኮንጎ ላስቲክ ጫማ ነው። ክላሺንኮቭ መሳሪያቸውን ከጎናቸው አንስተው ከጓዶቻቸው ጋር ሰላም ተባባሉ”
አንደኛው ሰው የለበሰው ሱሪ የቀድሞውን የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የደንብ ልብስ የመሰለ ነው። ሚሊሺያዎች እንዲህ ይለብሱ እንደነበር ከዚህ ቀደም በነበሩኝ ጉዞዎቼ ተመልክቼ ስለነበር፤ “በዚህ ጊዜ እንዴት ሚሊሺያዎች እንዲህ ደፍረው ሊንቀሳቀሱ ቻሉ?” እያልኩ እገረማለሁ። በዚያ ላይ የደንብ ልብሱን የለበሰው ሰው አጠገቡ ከተቀመጠው እና ሰው ጋር በመዝናናት መንፈስ ነው የሚያወራው። ሁኔታቸው አስገርሞኝ አተኩሬ እያያኋቸሁ እያለ፤ ሁለት ክላሺንኮቭ መሳሪያ የያዙ ሰዎች ወደ ካፌው በረንዳ አቅጣጫ መጡ። ሁለቱም ታጣቂዎች፤ ሚሊሺያ የመሰለኝ ሰው ያደረገውን አይነት ወታደራዊ የደንብ ልብስ አድርገዋል።
“የኤርትራ ወታደሮች ናቸው እንዴ?” ብዬ ራሴን ጠይቄ ሳልጨርስ፤ ካፌ በረንዳ ላይ ተቀምጠው የነበሩት ሁለቱ ሰዎች ሲነሱ ጫማቸው ታየኝ። ሚሊሺያ የመሰለኝም፤ የሲቪል ልብስ የለበሰውም የተጫሙት የኮንጎ ላስቲክ ጫማ ነው። ሁለቱም እስካሁን ዕይታዬ ውስጥ ሳይገባ የቆዩ፤ ክላሺንኮቭ መሳሪያቸውን ከጎናቸው አንስተው ከጓዶቻቸው ጋር ሰላም ተባባሉ። ጓዶቻቸውም ያደረጉት የላስቲክ ጫማ መሆኑን አስተዋልኩ።
በመሳሪያ አንጋቾቹ ሁኔታ ተመስጬ ሁኔታቸውን ስከታተል፤ ከአዲስ መጤዎቹ ውስጥ ጎልማሳ የሆነው ሰው መኪናችንን ተመለከታትና ተቆጣ። ወዲያው ትዕዛዝ እና ቁጣ በቀላቀለ መልኩ የሆነ ነገር በትግርኛ ተናገረ። ከሁኔታው ከፊታቸው ዞር እንድንል እንደፈለገ ገባኝ። የገመትኩት ልክ ነበር። ከኋላ የተቀመጠው የጋራዡ ሰራተኛ መሳሪያ አንጋቹ “መኪናችንን በፍጥነት ከአካባቢው እንድናነሳ” ትዕዛዝ እንደሰጠ ገለጸልኝ። አከታትሎም “የኤርትራ ወታደሮች ናቸው” ሲል የጠረጠርኩትን አረጋገጠልኝ።
የጋራዡ ሰራተኛ የተባለውን ለሹፌሩ ቢነግረውም፤ በወሬ የተጠመደው ሹፌር በቅጡ አልሰማውም። ጎልማሳው የኤርትራ ወታደር ጣቱን እያወዛወዘ በቁጣ በድጋሚ ትዕዛዝ ሲሰጥ፤ እኔም የጋራዡ ሰራተኛም ሹፌሩ ላይ ጮኽንበት። እየተነጫነጨ መኪናዋን አቅራቢያው ወዳለው የከተማው መሃል ወሰዳት።
ሹፌሩ የሆነውን በዝርዝር እስክንነግረው ድረስ ነገሩ አልገባውም፤ ኤርትራውያኑን ወታደሮችም አላያቸውም። የጋራዥ ሰራተኛው፤ ጎልማሳው የኤርትራ ወታደር የተጠቀማቸውን ቃላቶች ለሹፌሩ በትግርኛ ደገመለት። በትግራይ ያሉ ነዋሪዎች፤ ኤርትራውያን ወታደሮቹን ለመለየት የቃላት አጠቃቀም እና ዘያቸውን ነገሬ ብለው እንደሚከታተሉ አስቀድሜ ስለሰማሁ የሹፌሩ እና የጋራዥ ሰራተኛው ምልልስ አልገረመኝም። አምስት ደቂቃ ባማይሞላ ጊዜ ግን ሹፌሩ የራሱን ማረጋገጫ አገኘ።
ካፌ በረንዳ ላይ አስቀድመው ያየናቸው ሁለቱ ወታደሮች፤ መኪናችን ከቆመችበት ባሻገር ያለው የመንገድ አቅጣጫ በመከተል ወደ ከተማ መሃል ሲሄዱ አየን እና አሳየነው። ሹፌር ከቦታው ያስነሳነው ለረዥም ጊዜ አንድ አካባቢ ላይ በመቆማችን ተሰላተችተን መስሎት ነበር። ያየውን ካየ በኋላ ግን አመነ።
መኪናችን ተጨማሪ ተጓዦችን ለመፈለግ ለመጨረሻ ጊዜ ወደ መናኸሪያ አቅጣጫ ስታቀና አይኖቼን ወደ ካፌዋ በረንዳ ላኩ። ሁለቱ አዲስ መጤ ወታደሮች በረንዳው ላይ ተቀምጠው ዙሪያ ገባውን በተጠንቀቅ ይቃኛሉ። የቀድሞዎቹም ሆኑ አዲሶቹ ወታደሮች አካባቢውን በመጠበቅ አሊያም በመቃኘት ስራ ላይ የተሰማሩ ሳይሆኑ አይቀርም። መኪናችንን በረንዳው አጠገብ አቁመን የነበርንበት ሰዓትም፤ ወታደሮቹ ፈረቃ የሚቀያየሩበት ሰዓት እንደነበር ከሁኔታው ተነስቼ ገመትኩ።
የእኔ እና የኤርትራውያን ወታደሮች ጉዳይ በዚህ አላበቃም። ሹፌራችን ሁለት ተጓዦችን ከመናኸሪያ ጭኖ፤ ከመቐለ አብረውን የመጡትን ሁለት ሴቶች ከየቤታቸው ለማምጣት እየተጓዘ ነው። ዋናውን መንገድ ለቅቆ ወደ አዲግራት ማዘጋጃ ቤት ወደሚወስደው የውስጥ ለውስጥ መንገድ ሲታጠፍ ከሌሎች የኤርትራ ወታደሮች ጋር ተገጣጠምኩ። አንድ በቆርቆሮ የታጠረ መስሪያ ቤት የመሰለ ግቢ ደጃፍ ላይ አራት ወታደሮች ተቀምጠዋል። መሳሪያ ባይታጠቁም፤ የደንብ ልብሳቸውና ጫማቸው ግን ቀደም ሲል እንዳየኋቸው ወታደሮች ነው። መኪናችን በዝግታ በአጠገባቸው ስታልፍ ወታደሮቹ በጥርጣሬ አተኩረው ተመለከቷት።
ያየኋቸው ኤርትራውያን ወታደሮች አንዳቸውም የሀገራቸውን የመከላከያ ሰራዊት የደንብ ልብስ አልለበሱም። ወደ ዛላምበሳ እና ሌሎች የድንበር ከተሞች ብሄድ፤ የራሳቸውን የደንብ ልብስ እንደለበሱ እንደልብ መመልከት እንደምችል አዲግራት ያሉ ሰዎች ነግረውኛል። ይሄንን እንዴት እንዳወቁ ስጠይቅ፤ ወደ አካባቢው ደርሰው ከተመለሱ የአዲግራት ነዋሪዎች መስማታቸውን አብራርተውልኛል።
መናኸሪያ አካባቢ በቆየንባቸው ደቂቃዎች፤ በእግርጥም ወደ ዛላምበሳ የሚሄድ መኪና እንዳለ አጠያይቄ ነበር። ከወጣት መኪና ደላላዎች አንዱ እንደልብ ባይሆንም አልፎ አልፎ ሚኒባሶች እንደሚሄዱ ነገሩን። ሚኒባሶቹ የሚጠይቁትን ከፍ ያለ ዋጋ መክፈል የምችል ከሆነ ወደ ዛላምበሳ ብቻ ሳይሆን አድዋ እና ሽረም የሚሄዱ ሚኒባሶች ማግኘት እንደሚቻል ጨመረልኝ። ዋጋውን ጠየቅሁ። ለመሄጃ ብቻ አንድ ሺህ ብር መሆኑ ተነገረኝ።
የእውነትም ወደ አካባቢው መሄድ የምፈልግ የመሰላቸው ሹፌሩ እና የጋራዥ ሰራተኛው ነገርየውን እንዳልሞክረው ተከላከሉኝ። በዛላምበሳ መንገድ እና አካባቢው ያለው የጸጥታ ሁኔታ አስጊ መሆኑን አንስተው፤ መኪና ቢኖርም አደጋው ከፍ ያለ መሆኑን ገለጹልኝ። ወደ አድዋ እና ሽረ የሚሄዱ መኪናዎች፤ አዲግራት መውጪያ ላይ ካለ ኬላ በኋላ ማለፍ እንደማይችሉና የሚፈቀድላቸውም ካሉ የመንግስት ተሽከርካሪዎች ብቻ እንደሆኑ ጠቆሙኝ። ወጣቱ ደላላ ግን የሁለቱን ሀሳብ ችላ ብሎ፤ ወደ ቦታው የሚጓዙ መኪናዎች እንዳሉ ሊያሳምነኝ ጣረ። የሁለቱንም ወገን ማብራሪያዎች ከሰማሁ በኋላ ወደ መቐለ እንደምመለስ አሳውቄ የተጨማሪ ጉዞ ውይይቱን በዚሁ ቋጨሁት።
ወጣቱ ደላላ ከእኔ ጉዞ “ሽቀላ” ባለማግኘቱ የተከፋ ይመስላል። እንደቀድሞ ጊዜ ስራ በሽ ባለመሆኑ መቸገሩ በግልጽ ያስታውቃል። ወጣቱ ኑሮው የተመሰረተው ቀነ ተቀን በሚያገኘው ገቢ ላይ ነው። ከጠዋት ጀምሮ ምንም ስራ አለመስራቱንና እስከ ቀኑ ሰባት ሰዓት ድረስ እህል በአፉ አለመዞሩን ለሹፌሩ ሲነግረው ሰማሁ። ከውቅሮ ጀምሮ ስንሻምደው ከነበረው አንድ ኪሎ የገብስ ቆሎ ላይ የተረፈንን ሰጠሁት። የቆሎ አዘጋገኑ መራቡን ያስታውቃል። ጥቂት የብር ኖቶች “ለምሳ ትሁንህ” ብዬ ጨመርኩለት። ፊቱ በደስታ በራ።
የቀዘቀዘችውን እና በሮቿን የዘጋጋችውን አዲግራት ለተመለከተ፤ እንደ ወጣቱ ደላላ አይነት የተቸገሩ ሰዎች በየቦታው ሊኖሩ እንደሚችሉ ማገናዘብ አይሳነውም። በአዲግራት በእግር ከተዘዋወርኩባቸው ጥቂት ቦታዎች በአንዱ፤ የከተማይቱ ነዋሪዎች በእህል አቅርቦት ብቻ ሳይሆን፤ በመድኃኒት እጥረት ሊቸገሩ እንደሚችሉ በማሳያነት ሊጠቀስ የሚችል ነገር አይቻለሁ።
ነገሩ ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር፤ የትግራይ ክልል ምስራቅ ዞን ቅርንጫፍ ጋር የተያያዘ ነው። እኔ በተመለከትኩበት ወቅት በቅርንጫፉ ስር ያለው የአዲግራት መድኃኒት ቤት ከአገልግሎት ውጪ ሆኗል። በቀጫጭን የብረት ርብራቦች ከተሸፈኑት መስኮቶች መታወታቸው ተሰባብሯል። ከበሩ አጠገብ ያለው አንደኛው መስኮት እንደውም የብረት ርብራቦቹ ላይ የመገንጠል ሙከራ እንደተደረገ በግልጽ ይታያል።
ለዝርፊያ በሚመስል መልኩ የተሰበሩ መስኮቶችን በአዲግራት ባሉ የባንኮች ቅርንጫፎች ላይም ተመልክቻለሁ። የወጋገን፣ አንበሳ እና ቡና ባንኮች ቅርንጫፎች ለዚህ በምሳሌነት ሊጠቀሱ ይችላሉ። በአዲግራት በነበርኩበት ሰዓት ሁሉም የባንክ ቅርንጫፎች ዝግ ነበሩ። ከህዝብ አገልግሎት መስጪያዎች ቢያንስ የቅጽር ግቢው ተከፍቶ የተመለከትሁት የአዲግራት ማዘጋጃ ቤት ነው። በማዘጋጁ ቤቱ አገልግሎት ተጀምሮ እንደው ግን ወደ ውስጥ ዘልቄ አላረጋገጥኩም።
አዲግራትን የተሰናበትናት ከቀኑ ስምንት ሰዓት ገደማ ነበር። መቐለ ከሰዓት እላፊ በፊት በቶሎ ለመድረስ በሚል ነበር በጊዜ ከከተማይቱ ለመውጣት ውሳኔ ላይ የተደረሰው። አብረውኝ ከመቐለ የመጡ ሁለቱን ሴት ተጓዦች አሳፍረን ወደ የመልስ ጉዞ ጀመርን። በመልስ ጉዟችን እንደገና በወፍ በረረ የተመለከትኳቸውን ከተሞች ከአዲግራት ሁኔታ ጋር ለማነጻጸር ሞከርኩ።
እንደ እነ እኔ ዕይታ አዲግራት፤ በጉዳት እና ውድመት ረገድ ከዕዳጋ ሐሙስ እና ውቅሮ ከተሞች በተሻለ ሁኔታ ላይ ያለች ነች። ይህን ጉዳይ ያነሳሁባቸው አብረውኝ የሚጓዙ የከተማይቱ ተወላጆች፤ “በየቦታው እየገባህ ዘረፋውን እና ጉዳቱን ስላላየኸው ነው” የሚል ምላሽ ሰጥተውኛል። የተወሰነ እውነት አላቸው። ብዙ ዘረፋ እና ውድመት እንደደረሰበት የሰማሁትን የአዲግራት መድኃኒት ፋብሪካን እንኳ፤ በነበረኝ የጠበበ ጊዜ እና የጉዞዬ ሁኔታ ምክንያት በአይኔ ተመልክቼ ማረጋገጥ አልቻልኩም።
ወደ አዲግራት ስንጓዝም ሆነ ስንመለስ በመንገድ ያስተዋልኩት ሌላው ጉዳይ፤ ከገጠር የመጡ የሚመስሉ ነዋሪዎችን ነገር ነው። በማዳበሪያ ከረጢት የተሞላ ነገር ተሸክመው እና በአህያ ጭነው የሚጓዙ በርከት ያሉ ሰዎች ተመልክቼያለሁ። የተወሰኑቱ ወፍጮ ቤት እየተጓዙ ሳይሆን እንደማይቀር ጠርጥሬያለሁ። ለጥርጣሬዬ መነሻ የሆነኝ መንገድ ዳር ባሉ እና በሰዎች በተጨናነቁ ወፍጮ ቤቶች ተመሳሳይ ሰዎችን በመመልከቴ ነው። መብራት ጠፍቶ በመክረሙ ሳይሆን አይቀርም ወፍጮ ቤቶቹ ስራ የበዛባቸው ይመስላል። በጥቂት ቦታዎች አርሶ አደሮች የደረሰ እህላቸውን ሲያበራዩ አይቻለሁ። አልፎ አልፎም ቢሆን በየሜዳው የተሰማሩ ከብቶች እና እነርሱን የሚያግዱ ህጻናትም ከዕይታዬ ገብተዋል።
መቐለ ከመግባታቸን በፊት አጉላዕ ከተሰኘችው ከተማ መውጪያ ላይ ካለ የነዳጅ ማደያ ላይ መኪናችን ቆማ ነበር። ወደ አዲግራት ስንሄድም በዚሁ ማደያ ቆመን ነዳጅ መቅዳታችንን አይቼ ስለነበር፤ ሹፌራችንን ለምን እንደ እርሱ እንዳደረገ ጥያቄ ጠየቅሁት። ምንም እንኳ የነዳጅ ዋጋው ቢወደድም፤ በአካባቢው እምብዛም ተጠቃሚ ስለሌለ፣ ከመቐለ በተሻለ ነዳጅ የሚገኝበት ቦታ በመሆኑ ነው ይህንን ማደያ መምረጡን ነገረኝ። የሹፌራችን ምርጫ፤ ጣጣ አስከትሎብን እንደነበር ግን ያን ጊዜ ማናችንም አላወቅንም። በስተኋላ ላይ ከአካባቢው የመጡ ሰዎች የተሰማው መረጃ ግን የሚያስደንግጥ ነበር። ለካንስ እኛ ቦታውን ከለቀቅን ከግማሽ ሰዓት በኋላ በአጉላዕ አካባቢ ቅልጥ ያለ ተኩስ ተከፍቶ ኖሯል። ለ30 ደቂቃ ብንዘገይ ኖሮ….
* * *
ታህሳስ 23፤ 2013 ዓ.ም.። ለአምስት ቀናት ከግማሽ የቆየሁባትን መቐለን ልሰናበታት ነው። ወደ አዲስ አበባ የሚጓዝ የአውሮፕላን ቦታ ማግኘት ቢያንስ አንድ ሳምንት የሚያስጠብቅ በመሆኑ፤ ሌሎች አማራጮችን ሳፈላልግ ነበር የቆየሁት። ወደ መዲናይቱ የሚጓዝ አውቶብስ እንዳለ ስሰማ፤ የተጠየቅሁትን ለመክፈል አላቅማማሁም። ከ500 ብር በታች ይከፈልበት የነበረው የአውቶብስ ጉዞ፤ ሁለት ሺህ ብር የሚጠይቅበት ሆኗል። እርሱም ቢሆን ቀድሞ በደላላ የሚገዙት ካልጨረሱት ነው። በዚያም አለ በዚህ “ግዮን ባስ” ከተሰኘ የህዝብ ማመለሻ አገልግሎት ሰጪ፤ ለዛሬ ጉዞ የሚሆን ትኬቴን ቆርጬ ተዘጋጅቻለሁ።
የአውቶብሱ የትኬት ቢሮ ከሚገኘበት ቦታ ጠዋት አስራ ሁለት ሰዓት ተኩል እንድንገኝ በተገረን መሰረት፤ በተባለው ጊዜ ተገኝቻለሁ። አንድ ሰዓት ይንቀሳቀሳል የተባለው አውቶብስ ሌሎች መንገደኞችን እስኪያስተናግድ ራቅ ብዬ ሁኔታውን አስተውላለሁ። ከመንገደኞቹ በተሻለ ማልደው በቦታው የተገኙት ግን በአቅራቢያው በሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወረፋ ለመጠበቅ የተሰለፉ የከተማይቱ ነዋሪዎች ናቸው። እየተንጠባጠቡ በመጡ ተጓዞች ምክንያት 50 ደቂቃ ዘግይተን መቐለን ለቀን ወጣን። ጉዟችን በአላማጣ አቅጣጫ ነው።
ከመቐለ 15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ያለው አሸጎዳ ሳንደርስ፤ ሶስት ጊዜ ለፍተሻ እንድንወርድ ስንደረግ ነው፤ ጉዟችን የኤሊ ሊሆን እንደሚችል የገመትኩት። የፈራሁትም አልቀረ፤ በየ30 ደቂቃ ለፍተሻ መቆም ሆነ ስራችን። አንዳንዴ ከአውቶብስ ሳንወርድ በዚያው በተቀመጠንበት መታወቂያችን እያወለበለብን እንድናሳይ እንደረጋለን። ሌላ ጊዜ ሁለት ፈታሾች ወደ አውቶብስ ውስጥ ይገቡና ግማሽ ግማሽ ተካፍለው የሁሉንም መንገደኞች መታወቂያ በጥንቃቄ እየተመለከቱ ማንነታችንን ያረጋግጣሉ። እንደ ከተሞች መግቢያ እና መውጪያ ባሉ ቦታዎች ደግሞ ከአውቶብስ ወርደን መታወቂያችንም፤ አካላታችንም፤ አውቶብሳችንም ይፈተሻል።
በእንዲህ አይነት ሁኔታ ተጉዘን አላማጣ የገባነው እኩለ ቀን ገደማ ነው። ለምሳ ካሰብነው ጊዜ በላይ ስንወስድ፤ ረዳቱን ዛሬውኑ አዲስ አበባ እንገባ እንደሁ ጠየቅኩት። ፍተሻው እንዲሁ የሚቀጥል ከሆነ መተሐራ ላይ ልናድር እንደምንችል ነገረኝ። ከአላማጣ በኋላ በደሴ መስመር እንደምንጓዝ ገምቼ ስለነበር ለምን በአፋር በኩል እንደምንዞር በድጋሚ ጥያቄ አቀረብሁ። “የአፋሩ መንገድ ብዙም የትራፊክ ጭንቅንቅ ስለሌለው ነው” የሚል ምላሽ ተሰጠኝ። ረዳቱ እንደገመተውም በሃራ መገንጠያ አድርገን ወደ አፋር ክልል እስክንገባ ድረስ ተደጋጋሚ ፍተሻዎች ቀጥለው ነበር።
በአፋር ያለው ፍተሻ እንደ ትግራይ እና አማራ ክልል አይነቶቹ ጥብቅ ባይሆንም፤ ለመተሐራ የሚሆን ጊዜ አላተረፈልንም። ገዋኔ ከተማ ስንደርስ አስራ ሁለት ሰዓት በማለፉ ማደሪያችን እዚያው እንደሚሆን ሹፌሩ ውሳኔ አሳለፈ። በከባድ መኪናዎች እና የነዳጅ መጫኚያ ቦቴ አሽከርካሪዎች ዘንድ የምትዘወተረው አነስተኛይቱ ገዋኔ ብዙም የሆቴል አማራጭ የላትም። የተገኘው ቦታ ፈላልገን ለሊቱን አሳለፍን።
አርብ ጠዋት ከመቐለ ለጉዞ የተነሳን ቅዳሜንም በተመሳሳይ መልኩ መንገዱን ተያይዘነዋል። መተሐራ ላይ አፋችንን በቁርስ ካሟሸን በኋላ ጉዟችንን ያለ እክል ቀጠልን። እኩለ ቀን ሲሆን አዳማ ከተማ መግቢያ ደረስን። የአውቶብሱ ረዳት፤ አዳማ ወራጆች ካሉ እንዲዘጋጁ ሲናገር፤ ከፊት ለፊታችን ካለው ወንበር ከተቀመጡት ጀምሮ ብዙ መንገደኞች ለመውረድ መሰናዳት ጀመሩ። አንዴ ወደ ፈጣን የክፍያ መንገድ ከተገባ እስከ ቱሉ ዲምቱ ማቆም ስለማይቻል፤ ትክክለኛው መውረጃ ቦታ አዳማ መሆኑን ወራጆች ይነጋገራሉ።
ስለ ቱሉ ዲምቱ መቐለ እያለሁ ሰምቻለሁ። ወሬው “ከትግራይ የሚሄዱ ወጣቶች፤ አዲስ አበባ ሊገቡ ሲሉ ቱሉ ዲምቱ ላይ ተይዘው ይታሰራሉ” የሚል ነበር። “አፍንጫችን ስር አዲስ አበባ፤ ይህ ድርጊት ተፈጽሞ ከሆነ መስማት ነበረብኝ” በሚል ችላ ብዬው የቆየሁት ወሬ፤ በአውቶብሱ መንገደኞች ዘንድ ተደጋግሞ ሲነሳ “ምናልባት እውነትነት ሊኖረው ይችላል” አስብሎኛል። ሆኖም ይሄን ያህል ሰው በስሚ ስሚ ባገኘው ወሬ ተሸብሮ አውቶብሱን ጥሎ ይወርዳል ብዬ አልገመትኩም። ወራጆቹ “ከመታሰር፤ አዳማ ወርዶ በሌላ መኪና ወደ አዲስ አበባ እያሰበሩ መሄድ ይሻላል” የሚል አቋም ይዘዋል።
ከወረዱት ውስጥ አብዛኞቹ ኤርትራውያን ስደተኞች መሆናቸውን ከኋላ የተቀመጠ የመቐለ ሰው ሲነግረኝ፤ በዚያ ሁሉ ፍተሻ እንዴት አልፈው እንደመጡ ገረመኝ። በፍተሻ ወቅት የኤርትራ ፖስፖርት ይዛ የተመለከትኳት ተለቅ ያለች ሴት ከእነ ልጇ አሁንም አውቶብስ ውስጥ እንዳለች ስመለከት ደግሞ ግር አለኝ። የወረዱት ወርደው አውቶብሳችን ሲንቀሳቀስ በውስጡ የቀረነው ሃያ ገደማ መንገደኞች ነን። “ቱሉ ዲምቱ የሚያጋጥመን ያው ፍተሻ ነው። እንደተለመደው መታወቂያችንን አሳይተን ማለፋችን አይቀር” ያልን ሰዎች ነበር በአውቶብሱ የቀረነው።
እንደገመትነውም የፍጥነት የክፍያ መንገድ ማብቂያ ከሆነው ቱሉ ዲምቱ ስንደርስ ለፍተሻ እንድወርድ ተደረገ። የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የደንብ ልብስ የለበሰ ፖሊስ፤ ሴቶች እና ወንዶቹን በተለያየ መስመር ለፍተሻ አሰለፈን። ከዚያም የሁላችንንም መታወቂያ እና ፓስፖርት ከተቀበለ በኋላ ባለንበት እንድቆም ነገረን። ለደቂቃዎች በከራራው ጸሀይ ላይ ቆመን ጠበቅን። ፖሊሱ መታወቂያዎቹን በእጁ ይዞ ስልክ ይደውላል። ጥቂት ቆይቶ ደግሞ በአካባቢው ካሉ ሌሎች ፖሊሶች ጋር መታወቂያውን እያሳየ ይነጋገራል።
ጸሐዩ የበረታብን መንገደኞች ጥላ ፍለጋ መንገዱ ዳር ወዳለው ጉብታ ወጥተን ተቀመጥን። በዚያ እንደተቀመጥን ከተለያዩ ቦታዎች የሚመጡ በርካታ የህዝብ ማመላሻ ሚኒባሶች እና አውቶብሶች እንደነገሩ ተፈትሸው ሲያልፉ ስንታዘብ ቆየን። የእኛን መታወቂያ የያዘው ፖሊስ እና ሌሎች፤ ከአውቶብሳችን ፊት ቆሞ በሮቹ በተከፋፈተ ዘመናዊ የቤት መኪና እና መንገደኞቹ ላይ አተኩረዋል። ስለ ጉዟችን ህጋዊነት ፖሊሶቹን ለማስረዳት ሞክረው የሰለቻቸው ሹፌራችን እና ረዳቱ፤ አሁንም አሁንም ስልክ ይደውላሉ። ጠብ ያለ ነገር ሳይኖር ግማሽ ሰዓት አለፈ።
በአውቶብሱ ኋለኛ ክፍል ተቀምጠን የነበረን መንገደኞች፤ “አዳማ የወረዱት ተጓዦች ያሉት ነገር እውነት ይሆን እንዴ?” በሚል መንፈስ እንነጋገራለን። አንዳንድ መንገደኞች ላይ ጭንቀት ይነበባል። “የበላይ አለቆች ሲፈቅዱ ጉዟችንን እንቀጥላለን” የሚለው እምነቴ አሁንም ባይሟጠጥም፤ ያንን ሁሉ መንገድ ተጉዘን መጉላላታችንን ግን አልወደድኩትም። ከዚያ በኋላ የተከሰተው ግን እኔንም ስጋት ውስጥ የጨመረኝ ነበር።
ከጸሐይ ከተጠለልንበት ተጠርተን፤ ወደ አውቶብሱ እንድንሳፈር ከተደረገ በኋላ በቀጥታ ወደ ቱሉ ዲምቱ ፖሊስ ጣቢያ ተወስደን። ፖሊስ ጣቢያው አጠገብ፤ ከመቐለ የተነሳ ሌላ አውቶብስ ስመለከት ልቤ ዝቅ አለ። በኖህ ትራንስፖርት ባለቤትነት ስር ያለው ይህ አውቶብስ ከእኛ በኋላ ዘግይቶ ከመቐለ እንደተነሳው ሁሉ ማደሪያችን በነበረው ገዋኔም የደረሰው አምሽቶ ነው። ወደ አዲስ አበባ በነበረው ጉዞ ግን መዘግየቱን ለማካካስ ያሰበ በሚመስል መልኩ፤ ቀድሞን ነበር ከገዋኔ ጥሎን የሄደው። ይህን አውቶብስ ነው እንግዲህ ፖሊስ ጣቢያው ላይ ቆሞ ያገኘንው።
ወደ ቱሉ ዲምቱ ፖሊስ ጣቢያ ቅጽር ግቢ በሰልፍ ስንገባ፤ በስተቀኝ ባለው ክፍት ቦታ ላይ በርከት ያሉ ሰዎች ተሰብስበው አየሁ። በኖህ አውቶብስ ከመቐለ የመጡ መንገደኞች መሆናቸውን አልተጠራጠርኩም። ከመካከላቸው አንዳንዶቹን ገዋኔ ላይ ልብ ብዬ አይቼያቸዋለሁ። ፖሊስ ጣቢያው እንደ በረንዳ በሚጠቀምበት ቦታ ላይ ወረቀቶች የያዘ ፖሊስ እና ሌሎቹ ባልደረቦቹ ይታያሉ። ወረቀቶቹን የያዘው ፖሊስ አለቃ ነገር ይመስላል። ከዚያ በኋላ የቀረቡልንን አብዛኞቹን ጥያቄዎች የሚጠይቀው እርሱ ነበር።
ይሄው ፖሊስ ከመካከላችን የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እንዳሉ ጠየቀ። ሰባት ገደማ የሚሆኑት በአዎንታ ምላሽ ሰጡ። አብዛኞቹየአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ (AASTU) ተማሪዎች ናቸው። ተማሪዎቹ ቤተሰቦቻቸው ዘንድ መክረማቸውን፤ ወደ ዩኒቨርስቲ እንዲገቡ የተላለፈውን ጥሪ ሰምተው መምጣታቸውን እና የዚህ ዓመት ተመራቂዎች መሆናቸውን ተናገሩ። አለቃ ከሚመስለው ፖሊስ ኋላ የቆመው ወጣት ፖሊስ ለተማሪዎቹ አንድ ሁለት ጥያቄ እንደ ቀልድ ወርወር አደረገ። ጥያቄዎቹ በትክክል ተማሪዎች መሆናቸውን ለማረጋገጥ የተደረጉ ይመስላሉ።
ወጣቱ ፖሊስ ከአጠያየቁ፤ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት አጠገብ የሚገኘውን የተማሪዎቹን ዩኒቨርስቲ የሚያውቅ ይመስላል። ዩኒቨርስቲው ስንት መግቢያ እንዳለው፣ መግቢያዎቹ በየት አቅጣጫ እንደሚገኙ፣ ተማሪዎች ብዙውን ጊዜ “የሚፎርፉት” በየትኛው በር በኩል እንደሆነ፣ ተማሪዎቹ ፎርፈው ያውቁ እንደሆነ ተማሪዎቹን ቀልድ እያስመሰለ ይጠይቃቸዋል። በዚህ መሃል አለቃ መሳዩ ፖሊስ የተዘጋጀ ፎርም አምጥቶ የተማሪዎቹን ስም እና ዝርዝር መረጃ መመዝገብ ጀምሯል።
ተማሪዎቹ የቀረበላቸውን ጥያቄዎች ቢመልሱም፤ ወጣቱ ፖሊስ አለቀቃቸውም። ድንገት ያልተጠበቀ ጥያቄ ጠየቃቸው። “ባለፈው ዓመት እናንተ ግቢ ራሱን ያጠፋው ልጅ የስንተኛ ዓመት ተማሪ ነው? የየት አካባቢ ልጅ ነው?” ሲል ጠየቀ ወጣቱ ፖሊስ፤ አቃቤ ህግ ተከሳሽን በመስቀለኛ ጥያቄ በሚያፋጥጥበት ድምጸት። ብዙውን ጊዜ ምላሽ የሚሰጠው ተማሪ፤ በጥያቄው ግር ቢሰኝም ሁለቱንም ጥያቄዎች መለሰ። አሁን ወጣቱ ፖሊስ በምላሹ የረካ መሰለ። “ትክክል ነው” አለ ወደ ባልደረቦቹ ዞሮ። ያንን ምላሽ እስኪሰማ ድረስ ተማሪዎቹን ተጠራጥሯቸው እንደነበርም ተናገረ።
አለቃ መሳዩ ፖሊስ፤ የተማሪዎቹን ምዝገባ ሲጨረስ ከመንገደኞቹ መካከል የትግራይ መታወቂያ የያዙ ነዋሪዎች በአንድ ወገን እንዲሆን አደረገ። ከመካከላችን የአዲስ አበባ ነዋሪ እንዳለ ሲጠይቅ የተወሰነው እጃችንን አወጣን። እኛን በሌላ ወገን እንድንሰበሰብ አመለከተን። አለቃ መሳዩ ፖሊስ የትግራይ ነዋሪዎችን ዝርዝር መረጃ መመዝገብ ሲቀጥል፤ ወጣቱ ፖሊስ ተመሳሳዩን ለማድረግ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን አሰለፈ። ሁሉን ነገር ለማየት ከሰልፉ በስተመጨረሻ ቆምኩ። ተራዬ ሲደርስ ስሜን፣ የመኖሪያ አድራሻዬን፣ የጉዞዬን ምክንያት እና ስልክ ቁጥሬን አስመዘገብኩ።
የሁላችንም ምዝገባ ሲጠናቀቅ ከእኛ ቀድመው ከመጡት ከኖህ ባስ መንገደኞች ጋር እንድንቀላቀል ተደረገ። አርባ ገደማ የምንሆን የመቐለ ተጓዦች በጠባቧ የፖሊስ ጣቢያ ግቢ ውስጥ ተከማችተን ደቂቃዎች መቁጠር ጀመርን። በግቢው ውስጥ የነበረን ቆይታ አንድ ሰዓት ሲሻገር፤ “አጣርተው ይለቁናል” የሚለው ተስፋችን እየተመናመነ መጣ። በዚያ ላይ ፖሊሶቹ “ጠብቁ” ከማለት ውጪ የሚሰጡት ተጨማሪ መረጃ የለም። ለድብርታችን ትንሽ ማስታገሻ የሆነን ከፖሊስ ጣቢያው ውጪ ቡና ከምትሸጥ ሴት፤ የጀበና ቡና ያገኘን ጊዜ ነው። በእርግጥ የአውቶብሳችን ረዳትም የታሸገ ውሃ አምጥቶ አከፋፍሎናል።
ፖሊስ ጣቢያ ከገባን ሁለተኛ ሰዓት ሲቆጠር ነገርየው እንደመረረ ተረዳን። በአንድ አውቶብስ ውስጥ የነበረውን ተጓዦች እንለዋወጠው የነበረው የቢሆናል ግምት፤ “ምሽቱን በእስር ማሳለፍ” የሚለውን ጨመርንበት። ሰዓቱ ወደ አስር ሲጠጋ፤ በሁለቱም አውቶብሶች የነበሩ ተማሪዎች ወደ ፖሊሶቹ ዘንድ ተጠሩ። ለግማሽ ሰዓት ገደማ ድምጻቸው ከጠፋ በኋላ፤ ከተማሪዎቹ መካከል የተወሰኑት የራሳቸውንና የሌሎች መታወቂያች ከግቢ ውጪ ፎቶ ኮፒ አድርገው እንዲያመጡ ተላኩ። የታዘዙትን ፈጽመው ተመለሱ። ከሃያ ምናምን ደቂቃዎች በኋላ፤ ተማሪዎቹ አንድ በአንድ ከግቢ ሲወጡ እየተቁለጨለጨን በአይናችን ሸኘናቸው።
ከአስር ሰዓት በኋላ ባለው ጊዜ እስር ቤትን የሚያስታውሱ ነገሮችን የተመለከትኩበት ነበር። መንገደኞች በፖሊሶች አጀብ ሽንት ቤት ሲመላለሱ እና ከቤተሰብ የመጣላቸውን ምግብ ተቀብለው ከበው ሲመገቡ ማየቴ ነበር የእስር ቤት ጊዜ ትውስታዬን የቀሰቀሰው። መንገደኞች በፖሊስ ጣቢያ እንዲቆዩ መደረጋቸውን በስልክ የሰማ ቤተሰብ፤ ምግብ እና ውሃ ይዞ ከመምጣት ባሻገር ከፖሊሶች ጋር እሰጥ እገባ ሲገባ አስተውያለሁ። ሰዓቱ ወደ አስራ አንድ ሰዓት ሲጠጋ፤ ሁለት ከፍ ያለ ሹመት ያላቸው ፖሊሶች ወደ ግቢው መሃል መጡ።
ሁለቱ ፖሊሶች የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የሆኑ ሰዎች እንዲሰለፉ ጠይቁ። በእጃቸው ይዘውት የነበረውን የስም ዝርዝር ከመታወቂያ እና ፖስፖርት ጋራ እያመሳከሩ ወደ በረንዳው እንድሄድ አደረጉ። አካሄዱ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን ሁኔታ የተከተለ ስለነበር፤ ከፖሊስ ጣቢያው የመለቀቃችንን ተስፋ አለመለመው። የእኛን ተለይቶ መቆም ተከትሎ፤ ቀሪዎቹ መንገደኞች ዕጣ ፈንታቸውን ወደ ሁለቱ ፖሊሶች ተጠግተው ጥያቄ ያከታተሉ ጀምር። አንደኛው ፖሊስ “ጠብቁ” የሚል ምላሽ ሰጥቶ ሄደ። መንገደኞቹ ቀሪውን ፖሊስ ከብበው ማብራሪያ መጠየቃቸውን ቀጠሉ። ፖሊሱ በጫጫታ መሃል “እኔም እንደናንተው ነኝ። የማውቀው ነገር የለም” ሲላቸው ሰማሁ።
ከደቂቃዎች በኋላ የአዲስ አበባ መንገደኞች ስማችን እና መታወቂያችን በድጋሚ ታይቶ ከተረጋገጠ በኋላ ከግቢው እንድንወጣ ተደረገ። ወደ ኋላ የቀሩ፣ አብረውኝ የተጓዙ መንገደኞችን እጄን እያወዛወዝኩ ስሰናበት በሀዘን ስሜት ውስጥ ተዘፍቄ ነበር። ላደርግላቸው የምችለው ነገር አለመኖሩም አስከፍቶኛል። ከፖሊስ ጣቢያ ወጥቼ፤ አውቶብሱ ውስጥ የነበረኝን ሻንጣ ካወረድኩ በኋላ የረዳቱን ስልክ ተቀበልኩ። የቀሪዎቹን መንገደኞች ሁኔታ ለመከታተል በሚል ነበር ስልኩን መቀበሌ።
አውቶብሱ አጠገብ ቆሞ የነበረ ላዳ ታክሲ ውስጥ ስገባ አስራ አንድ ሰዓት አልፏል። በሁኔታው ማዘኔን ያየው የታክሲ ሹፌር፤ ሊያጫውተኝ ሞከረ። ባለፉት ሁለት ቀናት ከመቐለ የተነሱ አውቶብሶች ከነመንገደኞቻቸው በተመሳሳይ ሁኔታ ወደዚህ ፖሊስ ጣቢያ እንዲመጡ መደረጋቸውን ነገረኝ። የተወሰኑት ሲለቀቁ፤ የተወሰኑት ወደ ሌላ ሰፋ ወዳለ ፖሊስ ጣቢያ መወሰዳቸውን ጨመረልኝ። በዚህ አይነት የቀሩት መንገደኞች “በፖሊስ ጣቢያ ማደራቸው አይቀርም” በሚል ይበልጥ ተከዝኩ።
በእኛ አውቶብስ ውስጥ ከነበሩ መንገደኞች አንድ ሰው ሲቀር ሊሎቹ የዚያኑ ቀን ምሽት አንድ ሰዓት ላይ መለቀቃቸውን የአውቶብሱ ረዳት በስተኋላ በስልክ ነገረኝ። የኖህ ባስ መንገደኞች ግን እንደ እኛዎቹ ዕድለኞች እንዳልነበሩም አከለልኝ። ይህን ስሰማ አዳማ ላይ የወረዱት መንገደኞች ትዝ አሉኝ። ማንኛችን ነን ትክክል? እነርሱ ወይስ እኛ? ህግን ያመንነው – እኛ ወይስ ከሌሎች መከራ የተማሩት – እነርሱ?። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
የዚህን ልዩ ዘገባ ቀደምት ክፍሎች ለማንበብ ተከታዩቹን ሊንኮች ይጫኑ፦
ክፍል አንድ – https://ethiopiainsider.com/2021/2374/
ክፍል ሁለት – https://ethiopiainsider.com/2021/2398/
ክፍል ሶስት – https://ethiopiainsider.com/2021/2461/