በተስፋለም ወልደየስ
ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል የሚገኙ ሁለት የኤርትራውያን ስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎችን ልትዘጋ ነው። እንዲዘጉ ውሳኔ የተላለፈባቸው የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች፤ ሽመልባ እና ህጻጽ የተሰኙት እንደሆኑ የስደት እና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ ዛሬ አስታውቋል።
ሽመልባ የተመሰረተበት ቦታ ከኢትዮ-ኤርትራ ድንበር በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኝ በመሆኑ ለመዘጋቱ በምክንያትነት ተጠቅሷል። በደደቢት በረሃ የሚገኘው ለኑሮም ሆነ ለስደተኞች መጠለያነት አመቺ ባለመሆኑ በተመሳሳይ መልኩ ከአገልግሎት ውጪ እንዲሆን መወሰኑን የስደት እና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ ተናግረዋል።
“ሽመልባ ያው የመጀመሪያ ካምፕ ነው። ግን ከኢትዮ- ኤርትራ ድንበር 20 ኪሎ ሜትር ብቻ ነው የሚርቀው። በUNHCR ህግ መሰረት አንድ የስደተኛ ጣቢያ ከድንበር ቢያንስ 50 ኪሎ ሜትር መራቅ አለበት ይላል። ምክንያቱም [ስደተኞች] ለክፉም ለደጉም ኢላማ (target) እንዳይሆኑ እና ደህንነታቸው መረጋገጥ ስላለበት ማለት ነው” ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ።
በ1996 ዓ.ም. የተመሰረተው የሽመልባ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ፤ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በቁርሾ ላይ በነበሩባቸው ዓመታት እንኳ ስድስት ሺህ ገደማ ስደተኞችን ሲያስተናግድ የቆየ ነበር። በኢትዮጵያ ያሉ ስደተኞችን ጉዳይ በቀጥታ የሚመለከተውን መስሪያ ቤት የመምራት ኃላፊነት ከሁለት ወራት በፊት የተረከቡት አቶ ተስፋሁን፤ የስደተኞች ጣቢያው ዓለም አቀፉን ህግ በተቃረነ መልኩ መጀመሪያውኑ “እንዴት እንደተመሰረተ አላውቅም” ብለዋል።
“እንደ መንግስት ይመለከተናል ግን እኛ አልነበርንም። ዞሮ ዞሮ አሁን ከUNHCR ጋር ተነጋግረን ‘ይሄ መጀመሪያውኑ ልክ አልነበረም። አሁንም የሚቀጥልበት አግባብ የለም’ በሚለው ተነጋግረን ሽመልባ ላይ ያሉ ስደተኞችን ወይ ወደ ሌሎች ካምፖች በመውሰድ ወይ ከካምፕ ውጪ እንዲኖሩ መብት በመስጠት ወይም ከማህበረሰቡ ጋር በመቀላቀል ያንን ካምፕ መዝጋት በሚቻልበት መንገድ ላይ ተነጋግረን፣ ተሰማምተናል” ሲሉም በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት አብራርተዋል።
በትግራይ ክልል ከሚገኙት 92 ሺህ ገደማ ኤርትራውያን ስደተኞች ውስጥ፤ ግማሽ ያህሉ በክልሉ ባሉ አራት የስደተኞች ጣቢያዎች የሚኖሩ እንደነበር ይፋዊ መረጃዎች ያመለክታሉ። ከሽመልባ እና ህጻጽ ውጪ ያሉት የስደተኛ መጠለያዎች አዲ ሃሩሽ እና ማይ አይኒ በሚል መጠሪያ የሚታወቁ ናቸው።
በክልሉ ውጊያ ከመቀስቀሱ አስቀድሞ በነበረው ጊዜ በሽመልባ ይኖሩ የነበሩ ስደተኞች ብዛት 8,400 እንደነበር የስደተኞችን ጉዳይ የሚከታተለው የኢትዮጵያ መንግስት መስሪያ ቤት አስታውቋል። እንደ ሽመልባ የመዘጋት ዕጣ ፈንታ ከፊቱ በተደቀነው በህጻጽ የስደተኞች ጣቢያ፤ 11,800 ኤርትራውያን ይኖሩ እንደነበርም መስሪያ ቤቱ ጨምሮ ገልጿል።

የህጻጽ የስደተኞች መጠለያ “በረሃ ውስጥ ያለ ካምፕ” መሆኑን የሚናገሩት የስደት እና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር፤ “ብዙ ጊዜ ስደተኞች እዚያ ካምፕ ላይ ይመዘገቡና፣ አንዴ መታወቂያ ካወጡ በኋላ ጥለውት ነው የሚወጡት” ይላሉ። ስደተኞች ይህን የሚያደርጉት በአካባቢ ያለው ሁኔታ “ለኑሮ የማይመች” በመሆኑ ምክንያት እንደሆነም ያስረዳሉ።
የኢትዮጵያ መንግስት በ2005 ዓ.ም የተመሰረተውን የህጻጽ የስደተኞች መጠለያን እንደሚዘጋ ሲያስታውቅ የአሁኑ የመጀመሪያው አይደለም። የፌደራል መንግስት ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ በመጠለያ ጣቢያዎች ለሚኖሩ 12 ሺህ ስደተኞች የከተማ መታወቂያ ሰጥቷቸው እንደነበር አቶ ተስፋሁን አስታውሰዋል።
“[መንግስት] ያንን ካምፕ ለመዝጋት ብዙ ጥረት ቢያደርግም በወቅቱ የነበረው አመራር ህወሓት እና አንዳንድ አካላት እንቅፋት ፈጥረው ያንን እንቅስቃሴ አስተጓጉለውታል። ከዚያም በኋላ ኮቪድ ገባ። በኮሮና ጊዜ ብዙ ሰው ማንቀሳቀስ የሚመከር ስላልነበር ቆመ። በእሱ ምክንያት ነው ይሄ የሆነው እንጂ መጀመሪያውኑ ራሱ መዘጋት የነበረበትና ለመዝጋትም ብዙ ስራዎች የተሰሩበት ካምፕ ነው የነበረው” ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ የነበረውን ሂደት አብራርተዋል።
የሽመልባ እና ህጻጽ የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች እንዲዘጉ ቢወሰንም፤ መቼ የሚለውን በእርግጠኝነት መናገር እንደሚያስቸግር አቶ ተስፋሁን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በአካባቢ ካለው የጸጥታ ሁኔታ ባሻገር በመጠለያ ጣቢያዎቹ ግንባታዎችን ያከናወኑ ሌሎች ተቋማት በቦታው ተገኝተው የሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ጊዜውን እንደሚወስኑ አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)