እስካሁን የተመዘገቡ ዕጩዎች ቁጥር አነስተኛ መሆኑን ምርጫ ቦርድ ገለጸ

በአራት ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተሞች ለመጪው ምርጫ የሚወዳደሩ ዕጩዎች ምዝገባ ሊጠናቀቅ ስድስት ቀናት ቢቀሩትም፤ እስካሁን የተመዘገቡ ዕጩዎች ቁጥር አነስተኛ እንደሆነ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ገለጸ። ዕጩዎቻቸውን በብዛት ካላስመዘገቡት ውስጥ ገዢው የብልጽግና ፓርቲ ጭምር እንደሚገኝበት ቦርዱ አስታውቋል። 

ምርጫ ቦርድ ይህን የገለጸው ዛሬ ማክሰኞ የካቲት 16፤ 2013 ከፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ጋር በአዲስ አበባ ባካሄደው ስብሰባ ነው። በዚሁ ውይይት ላይ መዲናይቱ አዲስ አበባን ጨምሮ በኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ሐረሪ እና ጋምቤላ ክልሎች ስለተከናወኑ የዕጩዎች ምዝገባዎች በቁጥሮች የተደገፈ ገለጻ ቀርቧል። 

ቦርዱ በአራቱ ክልሎች እና በሁለቱ የከተማ መስተዳደሮች  የምርጫ ክልል ጽህፈት ቤቶችን ከፍቶ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ለስብሰባው ታዳሚዎች አብራርቷል። ጽህፈት ቤቶቹ ከተከፈቱባቸው አካባቢዎች መካከል የጸጥታ ችግር የነበረባቸው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ስፍራዎች እንደሚገኙበት ጠቁሟል።

እነዚህ ስፍራዎች፤ ባለፉት ወራት በተደጋጋሚ በተፈጸመ ጥቃት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በተገደሉበት የመተከል ዞን ስር የሚገኙ ናቸው። በፌደራል መንግስት በተቋቋመ ኮማንድ ፖስት ስር በሚገኘው የመተከል ዞን የተከፈቱት የምርጫ ክልል ጽህፈት ቤቶች በሰባት ወረዳዎች እና በአንድ ልዩ ዞን ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን ቦርዱ ገልጿል። 

የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ለተሰብሳቢዎቹ እንደተናገሩት፤ ጽህፈት ቤቶቹን ለመክፈት የተቻለው የፌደራል እና የክልሉ ፖሊስ እንዲሁም የመከላከያ ሰራዊት ባደረጉት የተቀናጀ እገዛ ነው። “ብቸኛው እዚያ ላይ ያጋጠመን ችግር፤ የጸጥታ ሁኔታው ከተማው ላይ ጥሩ ቢሆንም ከአሶሳ ወደ መተከል የወረዳ ከተሞች ወይም የምርጫ ክልልሎች የሚደረገው ሂደት በጥንቃቄ፣ በብዙ እጀባ መደረግ ስለነበረበት ሶስት፣ አራት ቀናት ወስዷል” ብለዋል። 

ቦርዱ ጽህፈት ቤቶቹን ከከፈተም በኋላ ችግሮች አጋጥመውት እንደነበር ሰብሳቢዋ አንስተዋል። “አንዳንድ ወረዳዎች ላይ የአስተዳደር መሸጋሸግ ወይም መለዋወጥ ስለነበረ፤ አዲሶቹ አስተዳዳሪዎች ቢሮው የቱ ጋር መሆኑን አለማወቅ፣ በቋሚነት የፖሊስ ምደባ አለማድረግ እና እንደዚህ የመሳሰሉ ችግሮች ገጥመውን ነበር” ያሉት ብርቱካን፤ ይህም ቢሆን ግን በስተመጨረሻ መፈታቱን አስረድተዋል። 

ምርጫ ቦርድ በሁለተኛው ዙር ባካተታቸው አምስት ክልሎች፤ ከዛሬ ማክሰኞ የካቲት 16 ጀምሮ የዕጩዎች ምዝገባ እንደሚጀምር በስብሰባው ላይ ተጠቅሷል። አምስቱ ክልሎች በዕጩዎች ምዝገባ ቀድመው መሳተፍ ያልቻሉት  ቦርዱ የሚጠበቅባቸውን የትብብር ግዴታዎች ዘግይተው በማሟላቸው መሆኑም ተብራርቷል። በአማራ፣ ደቡብ፣ ሲዳማ፣ አፋር እና ሶማሌ ክልሎች ከዛሬ ጀምሮ የሚከናወነው የዕጩዎች ምዝገባ የሚጠናቀቀው የካቲት 26 እንደሆነም ተጠቁሟል። (በተስፋለም ወልደየስ – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)