ኦብነግ በገዢው ፓርቲ “ጥቃት እየተፈጸመብኝ ነው” አለ

በተስፋለም ወልደየስ

የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) የሶማሌ ክልልን ከሚያስተዳድረው ገዢ ፓርቲ “ብዙ ጥቃቶች እየተፈጸሙብኝ ነው” አለ። ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ ከ50 በላይ የኦብነግ አባላት መታሰራቸውን አንድ የግንባሩ አመራር ተናግረዋል። 

የኦብነግ የስራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት አቶ አህመድ መሐመድ፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በጠራው ስብሰባ ላይ ዛሬ ማክሰኞ የካቲት 16 እንደገለጹት፤ በሶማሌ ክልል በዶሎ፣ ቸረር፣ ሸበሌ እና ቆራሔይ ዞኖች በሚገኙ የድርጅታቸው አባላት ላይ የእስራት እና ሌሎችም ጥቃቶች ደርሶባቸዋል። ከታሰሩት አባላቶቻቸው ውስጥ ለመጪው ምርጫ ግንባሩን ወክለው የሚወዳደሩ ዕጩዎች እንዲያዘጋጁ የተላኩ ልዑካን እንደሚገኙበት አስረድተዋል። 

“በዶሎ ዞን በዋርዴር የእኛ ቢሮ ተዘግቷል። ዕጩዎች እንዲያዘጋጁ የላክናቸው ሰዎች ደግሞ ከዞኑ ወደ ጅግጅጋ አምጥተዋቸው፤ ሰሞኑን ጅግጅጋ ታስረው ነው የነበሩት” ብለዋል። በቀድሞው የድርጅቱ ሊቀመንበር የተመራና ወደ ደገሐቡር የተጓዘ ልዑክም ወደ ከተማይቱ እንዳይገባ መከልከሉንም አክለዋል። 

አንድ ድርጅት “መንቀሳቀስም ሆነ ዕጩ ማዘጋጀት ካልቻለ”፤ ምርጫ ላይ ለመሳተፍ እንደሚቸገር የስራ አስፈጻሚ አባሉ ገልጸዋል። ኦብነግ በምርጫው ለመሳተፍም ሆነ ላለመሳተፍ ገና ውሳኔ ላይ እንዳልደረሰም በንግግራቸው ጠቁመዋል።  

“አሁን ሀገሪቱ ባለችበት ሁኔታ እኛ ምርጫውን ለመሳተፍ መገምገም አለብን። ሜዳው ነጻ አይደለም” ያሉት አቶ አህመድ፤ “አሁን ባለው ሁኔታ ሂዱና [ምርጫ] ተወዳደሩ ማለት፤ ሂዱና ተጣሉ ማለት ነው” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል። 

“እኛ በእጃችን ምንም የለም። አንድ ነገር ካልተደረገ፣ መፍትሔ ካልተገኘ ‘ሂዱና ተጣሉ’ ማለት፤ ‘ሂዱና ሙቱ’ ማለት ነው። ይሄን ከመቀበል፣ ምርጫውን ባንሳተፍ እና ‘እሺ፣ ሂዱና ውሰዱ’ ብንል ይሻላል የሚል [ሀሳብ] አለን” ሲሉ ምርጫውን በተመለከተ በኦብነግ አመራሮች ዘንድ ያለውን አመለካከት ለተሰብሳቢው አጋርተዋል።    

ለአቶ አህመድ አቤቱታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ እና የብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪል ማህበራት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አለሙ ስሜ ምላሾችን ሰጥተዋል። ኦብነግ ያቀረባቸው በርካታ አቤቱታዎች እንደደረሳቸው የተናገሩት ብርቱካን፤ ለችግሮቹ መፍትሄ ለመስጠት ከሶማሌ ክልል መንግስት የስራ ኃላፊዎች ጋር “በአጭር ጊዜ ውስጥ” ስብሰባ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል። 

በስብሰባው ላይ ገዢውን ፓርቲ ወክለው የተገኙት አቶ አለሙ በበኩላቸው እንደ ኦብነግ ያሉ ፓርቲዎች “ከክልል መንግስታት ጋር መነጋገር አይፈልጉም” ሲሉ ተችተዋል። “ኦብነግ ብዙ ጊዜ እኛ ዋናው መስሪያ ቤት ይመጣና የሶማሌ ክልል አመራርን ይከሰሳል። የሶማሌ ክልል አመራርን ስንጠይቅ ደግሞ ጅግጅጋ ሄደው ከእነርሱ ጋር መነጋገር አይፈልጉም” ብለዋል። 

“አደረጃጀታችን ፌደራላዊ አወቃቀር ነው። ከማዕከል፣ ከፌደራል መንግስት ሁሉ ነገር ከዚህ የሚዘወርበት ሁኔታ ስለሌለ፤ ብዙ ጊዜ ከክልል መንግስት ጋር እንዲነጋገሩ በተለይ ከኦብነግ ሊቀመንበር ጋር እንነጋገራለን ግን አያደርጉትም። ከእኛ ጋር መነጋገር ይፈልጋሉ፤ ታች ግን የክልል መንግስትን ያለማክበር አዝማሚያዎች አሉ” ሲሉ ኦብነግ ይከተለዋል ያሉትን አካሄድ ነቅፈዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)