በተስፋለም ወልደየስ
በእስር ቤት ያሉ ፖለቲከኞች ለምርጫ በዕጩነት መቅረብ እንደማይችሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ። ቦርዱ ይህን የገለጸው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) በእስር ላይ ያሉ አባላቱ በመጪው ምርጫ ዕጩ ሆነው መቅረብ ይችሉ እንደው ጥያቄ ማቅረቡን ተከትሎ ነው።
ጥያቄው የቀረበው ቦርዱ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ማክሰኞ የካቲት 16 ባደረገው ስብሰባ ላይ ነበር።በዳውድ ኢብሳ የሚመራው ኦነግ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ በቴ ኡርጌሳ፤ የፍርድ ውሳኔ ሳይተላለፍባቸው፤ በፖሊስ ጣቢያ እና በእስር ቤት ያሉ አባሎቻቸው የምርጫ ተሳትፎ የተመለከተ ጉዳይ አንስተዋል።
“በህግ ወይም በፍርድ ቤት ውሳኔ፤ የመመረጥ ወይም የመምረጥ መብቱ ያልተገፈፈ ሰው፤ በዕጩነት መቅረብ እንደሚችል ህጉ ይደነግጋል። በየፖሊስ ጣቢያው የታሰሩና ምንም በህግ አግባብ እየተጠየቁ ያልሆኑ፤ ፍርድ ቤት በነጻ ያሰናበታቸውን አካላት ዕጩ አድርገን ማቅረብ እንችላለን?” ሲሉ አቶ በቴ ጠይቀዋል።
የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢዋ ብርቱካን ሚደቅሳ ለጥያቄው በሰጡት ምላሽ፤ “እስር ቤት ያሉ ሰዎች በዕጩነት መቅረብ አይችሉም” ብለዋል። ለዚህ አይነት ጥያቄ “በሩ ከተከፈተ”፤ የኦነግ አባላት ብቻ ሳይሆኑ “በነፍስ ግድያ ተከሰስው ጉዳያቸውን በእስር ላይ ሆነው የሚከታተሉ ጭምር” በዕጩነት ለመሳተፍ ጥያቄ ሊያቀርቡ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
በአንዳንድ ሀገራት ይህም ቢሆን እንደሚፈቀድ የጠቀሱት የቦርድ ሰብሳቢዋ፤ “የኢትዮጵያ ህግ ግን ይህን እንደማያዝ” አብራርተዋል። ህጉ “ለምን አላዘዝም ወይም ለምን አልፈቀደም ወደሚለው መሄድ አልችልም” ያሉት ሰብሳቢዋ፤ ነገር ግን “እስር ላይ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት በዕጩነት ይቀርባሉ የሚባልበት የህግ አግባብ የለም” ብለዋል።
ይህ ማለት ግን በእስር ላይ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ጭርሱኑ በምርጫ መሳተፍ አይችሉም ማለት እንዳልሆነም አብራርተዋል። “እስር ቤት ቆይተው ፍርድ ቤት ነጻ እስካላቸው፤ በከባድ ወንጀል እስካልተፈረደባቸው ወይም ፍርድብ ቤቱ መብታቸውን እስካልገደበባቸው በዕጩነት ለመመዝገብም ሆነ ለመወዳደር ይችላሉ” ሲሉ ለተሰብሳቢዎቹ አስረድተዋል።
ኦነግ አሁን በእስር ላይ የሚገኙ አመራሮቹን በዕጩነት የማቅረብ ዕቅድ እንደነበረው አቶ በቴ በስብሰባው ላይ ተናግረዋል። አመራሮቹ የታሰሩት “የህግ የበላይነትን ለማስከበር ነው” በሚል በገዢው ፓርቲ የሚቀርበውን ምክንያት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው ውድቅ አድርገዋል።
“እኛ በግልጽ እየተናገርን ያለነው በኦሮሚያ አሁን ወደ 50 ሺህ እስረኞች አሉ። ከእነዚያ ውስጥ እኛ ለየት አድርገን ያቀረብነው፤ ፍርድ ቤት ጉዳዮቻቸውን ዘግቶ በነጻ እንዲለቀቁ ከአንዴም እስከ አምስት፣ ስድስት ጊዜ የጻፈላቸው፤ አቃቤ ህግ ‘እነዚህ ሰዎች ላይ ክስ የለኝም’ ብሎ ከመጀመሪያው ፋይላቸውን የዘጋውን አመራሮችን ነው” ብለዋል።
ከአመራሮቹ በተጨማሪ፤ “ፍርድ ቤት ቀርበው ክስ ያልተመሰረተባቸው” በሺህ የሚቆጠሩ የኦነግ አባላቶች በተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎች እንደሚገኙ አቶ በቴ ተናግረዋል። እነዚህ እስረኞችን በተመለከተ ምርጫ ቦርድም ሆነ ገዢው ፓርቲ መፍትሔ እንዲሰጡ ጥያቄ ቢቀርብላቸውም ከሁለቱም አጥጋቢ ምላሽ አለማግኘታቸውን ገልጸዋል። “ብልጽግና ያንን ለማድረግ ፍቃደኛ አይደለም” ሲሉም ወንጅለዋል።
በፍርድ ቤት ያልተያዙ፤ ምንም አይነት ቀጠሮ የሌላቸው የኦነግ አመራሮችን በተመለከተ፤ ምርጫ ቦርድ ከሚመለከተው የመንግስት አካል ጋር እየተነጋገረ እንደሆነ በቦርዱ ኃላፊ ምላሽ ተሰጥቷል። “ቀጠሮ እስከሌላቸው ድረስ በእስር የሚቆዩበት ምክንያት ምንም የለም። ቀጠሮ ያለበትም እንግዲህ ‘በራሱ አግባብ የሚታይ ነው’ ብለን ነው እዚያም ውስጥ የማንገባው። ይሄንን ለይተን ከሚመለከታቸው፤ በተለይ በኦሮሚያ መንግስት ቁጥጥር ስር ስላሉ፣ ከእነርሱ ጋር እየተነጋገርን ነው። እየተከታተልን ነው” ብለዋል።
የብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪል ማህበራት ዘርፍ ኃላፊ የሆኑት አቶ አለሙ ስሜ ግን በኦነግ የቀረበውን ስሞታ አጣጥለዋል። ኦነግ “በአመራሮቹ መካከል የተፈጠረውን ችግር ወደ ብልጽግና ለማላከክ” እንዳይሞክር ያሳሰቡት አቶ አለሙ፤ ግንባሩ “የራሱን ችግር ሳይፈታ እና ህግ ሳይከብር ብልጽግናን መክሰሱን” ተችተዋል።
አቶ በቴ ያሉበት የኦነግ ክንፍ “የሽግግር መንግስት አቋቋሜያለሁ ብሎ አውጇል” በማለት የወነጀሉት አቶ አለሙ፤ “የትኛው ነው የምርጫ ቦርድን ህግ ያከበረው?” ሲሉ ጠይቀዋል። ምርጫ ቦርድ “ሽግግር መንግስት አቋቁሙ” ሳይሆን፤ “ችግራችሁን በጉባኤ ፍቱ” የሚል ውሳኔ ማሳለፉን የብልጽግና ፓርቲው አመራር አስታውሰዋል። ቦርዱ “የሀገሪቱን ህግ የማይከብሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በህግ አግባብ” እንዲሰሩ እንዲያደርግም አሳስበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)