በየምርጫ ክልሎቹ የሚወዳደሩ ዕጩዎች ማንነት ይፋ ተደረገ

የፎቶ ዘገባ፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአዲስ አበባ ከተማ ፓርቲያቸውን ወክለው አሊያም በግል በየምርጫ ክልሎቹ የሚወዳደሩ ዕጩዎችን ማንነት ዛሬ ይፋ አድርጓል። በዕጩዎች መመዝገቢያ ጽህፈት ቤቶች ፊት ለፊት በተለጠፉት የቦርዱ የማሳወቂያ ቅጾች፤ የምርጫ ተወዳዳሪዎችን ሙሉ ስም፣ የመወዳደሪያ ምልክታቸውን፣ ማንን ወክለው በዕጩነት እንደቀረቡ፣ ዕድሜያቸውን፣ የተሰማሩበትን የስራ ዘርፍ እንዲሁም የትምህርት ደረጃቸውን ዝርዝር መረጃ ይዘዋል።

በአዲስ አበባ ካዛንቺስ አካባቢ የሚወዳደሩ ዕጩዎችን ማንነት ለማወቅ በአካባቢው የሚተላለፉ ሰዎች ለአፍታ ቆም ብለው ቅጾቹን ሲያስተውሉ የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ ተመልክቷል። የፓርላማ መቀመጫ ለማግኘት ገዢውን የብልጽግና ፓርቲ ወክለው በአካባቢው የሚወዳደሩት የትምህርት ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌታሁን መኩሪያ ናቸው።

ተቃዋሚው የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) ዶ/ር ንጋት አስፋውን በዕጩነት ሲያቀርብ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በበኩሉ በቅርቡ ከአሜሪካ የተመለሱትን ዶ/ር በላይ እጅጉን ለውድድር አጭቷል። ከእነዚህ በተጨማሪ ኅብር ኢትዮጵያ፣ ኢህአፓ፥ ነጻነትና እኩልነት፣ እናት እና ኅዳሴ ፓርቲዎች በዚሁ በምርጫ ክልል 15 ዕጩዎቻቸውን ያወዳድራሉ። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)