ኦነግ በመጪው ምርጫ እንደማይሳተፍ አስታወቀ

በተስፋለም ወልደየስ 

በዳውድ ኢብሳ የሚመራው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) በመጪው ግንቦት ወር መጨረሻ በሚደረገው ጠቅላላ ምርጫ እንደማይሳተፍ አስታወቀ። መጪውን ምርጫ “ውጤቱ አስቀድሞ የታወቀ” ሲል የጠራው ኦነግ፤ “በምርጫ መሳተፍ አለመቻሌን ስገልጽ ሀዘን ይሰማኛል” ብሏል።  

ኦነግ ሰኞ የካቲት 29 ለሊት በይፋዊ የፌስ ቡክ ገጹ  ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ግንባሩ ከዚህ ውሳኔ ላይ ሊደርስ የቻለው ገዢው ፓርቲ “ነጻ እና ፍትሃዊ ምርጫ” ለማካሄድ የሚያስፈልጉ መስፈርቶችን ለማሟላት ፍቃደኛ ባለመሆኑ ነው።  የብልጽግና ፓርቲ ይህን ያደረገው “ለራሱ እና ለአጋሮቹ በምርጫ ውስጥ የማይገባቸውን ጥቅም ለማግኘት ነው” ሲል ግንባሩ ወንጅሏል።

መጪውን ምርጫ “በፍትሃዊነት፣ በገለልተኛነት እና ተአማኒነት” ለማካሄድ ያለው “እድል ያነሰ” መሆኑን በመግለጫው የጠቀሰው ኦነግ፤  በስልጣን ላይ ያለው መንግስት “ነጻ እና ፍትሃዊ ምርጫ ማካሄድ የሚያስፈልጉ ዝቅተኛ መስፈርቶችን ማሟላት የማይችል ነው” በማለት ተችቷል። አሁን ያለው መንግስት “ነጻ ባልሆኑ ሀገራት የሚታዩ ዝቅተኛ የዲሞክራሲ ደረጃዎችን እንኳን አያሟላም” ሲል አክሏል። 

“ገዢው ቡድን ይህንን ምርጫ ለማካሄድ የወሰነበት ብቸኛ  ምክንያት በምርጫ ተመርጦ ስልጣን ላይ የወጣ መንግስት ለማስመሰል ብቻ ነው” የሚለው ኦነግ፤ “ከዚህ ውጪ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቹ ለሚራቡበት ድሃ ሃገር፤ ይህን አይነቱን፣ በለጋሾች እና ባለሃብቶች ልገሳ የሚካሄድ ውድ ምርጫ ለማካሄድ ምንም ምክንያት የለም” ሲል የምርጫውን መደረግ ነቅፏል።  

“ነጻ እና ፍትሃዊ ባልሆነ ሁኔታ” የሚደረግ ምርጫ ውጤት “በሁሉም የባለድርሻ አካላት ውክልና እና ተቀባይነት የሌለው ይሆናል” ሲልም ኦነግ በመግለጫው አስጠንቅቋል። ምርጫው ቢደረግም፤ በኢትዮጵያ አሁን ላለው ችግር መፍትሄ እንደማያመጣ አጽንኦት ሰጥቷል።

“ምርጫው ከተካሄደም፤ የአገሪቷን ዋና ዋና የፖለቲካ ችግሮች እና የግጭት ምንጮች የሆኑትን ችግሮች በመፍታት ረገድ፤ ይህ ነው የተባለ፣ ምንም አይነት ልዩነት አያመጣም” ሲል ኦነግ በመግለጫው አትቷል።  

በአሁኑ ወቅት ምርጫ ከማካሄድ ይልቅ “ለአገሪቱ የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የሚያግዙ መስፈርቶችን ተግባራዊ ማድረግ ይጠቅማል” የሚል እምነቱን ያንጸባረቀው ኦነግ፤ መደረግ አለባቸውን ያላቸውን ጉዳዩች በአምስት ነጥቦች ከፋፍሎ አስቀምጧል። 

ግንባሩ በቀዳሚነት ያስቀመጠው መስፈርት “ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መልቀቅ” የሚል ሲሆን፤ በተከታይነት ደግሞ “የተዘጉ ወይም በቁጥጥር ስር ያሉ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጽህፈት ቤቶች ተመልሰው እንዲከፈቱ” ጠይቋል። 

በሀገሪቱ በሁሉም ክፍሎች “ጦርነቶች እንደሚስተዋሉ” በሶስተኛ ነጥብነት የጠቀሰው ኦነግ፤ “ሁሉንም ጦርነቶች በማቆም ሁሉን ያካተተ ድርድር እንዲደረግ” እንደሚሻ ገልጿል። “ቁልፍ የሆኑ የመንግስት ተቋማትን ገለልተኝነት እና ከአድሎ የጸዱ መሆናቸውን ማረጋገጥ” የሚለው ግንባሩ በአራተኛነት ያስቀመጠው መስፈርት ነው።  

ከተቋሟት መካከል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ  በመግለጫው በቀጥታ ስሙ ተነስቶ ተጠቅሷል። ከምርጫ ቦርድ ባሻገር ከህግ ጋር የተያያዙ ተቋማት በኦነግ መግለጫ ቢነሱም በደፈናው “የህግ አስፈጻሚ አካል እና የዳኝነት ስርዓት”  በሚል ነው የቀረቡት። 

ኦነግ በሶስት ቋንቋዎች ያወጣውን ጋዜጣዊ መግለጫ ያጠቃለለው አምስተኛ መስፈርቱን በማስተዋወቅ ነው። የግንባሩ የመጨረሻ መስፈርት “ወሳኝ የሆነ የፖለቲካ ውይይት ሂደት ማስጀመርን” ይጠይቃል። ውይይቱ “የፖለቲካ ልዩነቶችን ለመፍታት ያለመ” መሆን እንዳለበት የጠቆመው ኦነግ፤ ለዚህም “ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት” መሆን እንደሚገባው አሳስቧል።  (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)