በመጪው ምርጫ ለመወዳደር ከስምንት ሺህ በላይ ዕጩዎች መመዝገባቸውን ምርጫ ቦርድ አስታወቀ

በግንቦት ወር መጨረሻ ለሚደረገው ሀገር አቀፍ ምርጫ በፖለቲካ ፓርቲዎች የቀረቡ 8,209 ዕጩዎች መመዝገባቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ አደረገ። ቦርዱ ዛሬ ሐሙስ መጋቢት 2 በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው 125 የግል ተወዳዳሪዎችም በምርጫው ለመወዳደር በዕጩነት ተመዝግበዋል።  

የምርጫ መወዳደሪያ ምልክቶች ከወሰዱ 49 ፓርቲዎች መካከል 47ቱ ዕጩዎችን ማስመዝገባቸውን ቦርዱ በመግለጫው ጠቅሷል። አራት ፓርቲዎች ለክልል ምክር ቤት ብቻ የሚወዳደሩ ሲሆን ሁለት ፓርቲዎች ደግሞ ለተወካዮች ምክር ቤት ብቻ ዕጩዎችን ያቀረቡ ናቸው ተብሏል። 

በምርጫው ከሚሳተፉ 47 ፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ከፍተኛውን ዕጩ ያስመዘገበው ገዢው ብልጽግና ፓርቲ ነው። ብልጽግና 2,432 ዕጩዎች ለውድድር አቅርቧል። በሁለተኛ ደረጃ ከፍተኛ የዕጩዎች ቁጥር ያቀረበው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ ደግሞ 1,385 ዕጩዎችን አስመዝግቧል። እናት ፓርቲ 573 ዕጩዎችን በማስመዘገብ በሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ለምርጫው የተመዘገቡ ዕጩዎች ቁጥር አሁን ይፋ ከተደረገው ሊቀንስም ሆነ ሊጨምር እንደሚችል የገለጸው ምርጫ ቦርድ፤ የዛሬው አሃዝ “ጊዜያዊ” መሆኑን አስገንዝቧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)