የምርጫ ክርክር ለማዘጋጀት 11 ተቋማት የምርጫ ቦርድን ይሁንታ አገኙ

በተስፋለም ወልደየስ 

የምርጫ ክርክር ለማዘጋጀት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፍላጎታቸውን በጹሁፍ ካቀረቡ ተቋማት መካከል አስራ አንዱ የቦርዱን ይሁንታ አገኙ። ምርጫ ቦርድ ዛሬ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ግምገማ ካቀረባቸው ከእነዚህ ተቋማት መካከል የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ የባለሙያዎች ማህበራት እና የብዙሃን መገናኛዎች ይገኙበታል። 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዩች ኃላፊ ሶልያና ሽመልስ እንደተናገሩት 23 ድርጅቶች የምርጫ ክርክር ለማዘጋጀት ለመስሪያ ቤታቸው የፍላጎት መግለጫ አስገብተዋል። “[ድርጅቶቹ] መስፈርቱን ሙሉ ለሙሉ ያሟሉ ላይሆኑ ይችላሉ ግን 23 የሚሆኑ  ድርጅቶች በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ የምርጫ ክርክር ማካሄድ እንፈልጋልን ብለዋል” ሲሉ ዛሬ ቦርዱ ለውይይት ለጠራቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች አስረድተዋል። 

የቦርዱን ይሁንታ ካገኙና በመብቶች ላይ ከሚሰሩ ተቋማት መካከል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ)፣ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ህብረት እና ሴታዊት ሙቭመንት ይጠቀሳሉ። በሙያ ዘርፋቸው የሚያጠነጥኑ ክርከሮችን ለማዘጋጀት ያቀዱት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን እና የኢትዮጵያ መሬት አስተዳደር ባለሙያዎች ማህበር በአስራ አንዱ ተቋማት ዝርዝር ተካትተዋል።   

በ1997 ምርጫ ወቅት አይረሴ የሆኑ የምርጫ ክርክሮችን ያዘጋጀው ኢንተር አፍሪካ ግሩፕ በዘንድሮው ምርጫ ተመሳሳይ ሙግቶችን ለማዘጋጀት መሰናዳቱን ምርጫ ቦርድ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ባሰራጨው ሰነድ ላይ ተገልጿል። ኢንተር አፍሪካ ግሩፕ “በተመረጡ ዋና ዋና የፖለቲካ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ሶስት የክርክር መድረኮችን ለማዘጋጀት ማቀዱም ተብራርቷል። ተቋሙ ክርክሮቹን ለማካሄድ የመረጣቸው ከተሞች በደብረ ብርሃን፣ አርባ ምንጭ እና ጅግጅጋ ናቸው። 

በብዙሃን መገናኛ ረገድ አምስት ድርጅቶች የምርጫ ክርክሮችን የማዘጋጀት እቅዳቸውን ለምርጫ ቦርድ ቢያቀርቡም፤ ተቀባይነት አግኝተው ከአስራ አንዱ ተቋማት ዝርዝር ውስጥ የገቡት ሶስት ብቻ ናቸው። ከብዙሃን መገናኛ ድርጅቶቹ መካከል ከፍተኛውን ቁጥር ያቀረበው የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ (OBN) ነው።

OBN በስቱዲዮ ውስጥ የሚካሄዱ 55 ክርክሮችን ለማዘጋጀት ማቀዱ በምርጫ ቦርድ ሰነድ ላይ ተመልክቷል። ሃያ አምስቱ ክርክሮች በኦሮምኛ ቋንቋ የሚደረጉ ሲሆን ቀሪዎቹ በሶማሊኛ፣ አፋርኛ እና አማርኛ የሚካሄዱ ናቸው። ሁሉም ክርክሮች ከተቀረጹ በኋላ “በOBN ኤዲቶሪያል ፖሊሲ መሰረት አርትኦት ተደርጎባቸው” እንደሚተላለፉ ተጠቁሟል።  

በመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ ክርክሮችን ለመቅረጽ የተሰናዳው ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት፤ 13 ክርክሮችን እንደሚያዘጋጅ በምርጫ ቦርድ ሰነድ ላይ ተቀምጧል። ፋና በሀገር አቀፍ ደረጃ አራት ክርክሮች ለማዘጋጀት ያቀደ ሲሆን በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ሶማሊ እና አፋር ክልሎች ደግሞ በእያንዳንዳቸው ሁለት የክርክር መድረኮች እንደሚኖሩት ተገልጿል። ድርጅቱ በሀዋሳ ከተማ የሚካሄዱ ሁለት ክርክሮችም እንደሚኖሩትም ተጠቅሷል።  

የምርጫ ቦርድ ይሁንታ ከተሰጣቸው የመገናኛ ብዙሃን ድርጅቶች ውስጥ የግል ቴሌቪዝን ጣቢያ የሆነው አሃዱ ይገኝበታል።  ሌላኛው ነው። አሃዱ ቴሌቪዝን በአማርኛ ቋንቋ ከሚያደርጋቸው ክርክሮች ውስጥ አራቱ በቀጥታ የሚተላለፉ ናቸው ተብሏል። የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በእነዚህ ክርክሮች ላይ የሚሳተፉት “በራሳቸው ምርጫ እና ፍቃደኝነት ላይ ተመስርተው” መሆኑን ምርጫ ቦርድ አስታውቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)