በአማሮ ልዩ ወረዳ በቀጠለው ጥቃት ሶስት አርሶ አደሮች ተገደሉ

በተስፋለም ወልደየስ 

በደቡብ ክልል በአማሮ ልዩ ወረዳ ትናንት እና ከትናንት በስቲያ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ሶስት አርሶ አደሮች መገደላቸውን የልዩ ወረዳው የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዩች ጽህፈት ቤት አስታወቀ። የልዩ ወረዳውን ከኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ጋር በሚያዋስኑ አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች “ተመሳሳይ ጥቃት ይፈጸማል” በሚል በስጋት ላይ መሆናቸውም ተገልጿል።

በአማሮ ልዩ ወረዳ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የሚዲያ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት አስተባባሪ የሆኑት አቶ አማረ አክሊሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደተናገሩት በትላንትናው ዕለት ጥቃት በተፈጸመበት የከሬዳ ቀበሌ አቶ አስረስ አሻግሬ የተባሉ አርሶ አደር ተገድለዋል። ሟቹ በጥይት የተገደሉት፤ ከቀኑ 11 ሰዓት ከ40 ገደማ በራሳቸው የእርሻ ማሳ ላይ ባሉበት እንደሆነም ገልጸዋል።

በተመሳሳይ ሁኔታ በልዩ ወረዳው ከትላንት በስቲያ ረቡዕ በተሰነዘረ ጥቃት፤ ሁለት ሰዎች ሲገደሉ አንድ የአካባቢው ነዋሪ ላይ “ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል” ብለዋል። የረቡዕው ጥቃት ያነጣጠረው በሻሮ እና ቡኑቲ ቀበሌዎች ላይ እንደነበር የሚያስረዱት አስተባባሪው፤ በዚህም አቶ አለሙ ጭርቆሳ እና አቶ መሰለ አዳነ የተባሉ በሁለቱ አካባቢዎች የሚኖሩ አርሶ አደሮች በጥይት ተመትተው መሞታቸውን አብራርተዋል። የሶስቱም አርሶ አደሮች ቀብር በዛሬው ዕለት አርብ በአካባቢያቸው መፈጸሙንም አክለዋል። 

በአካባቢው በተደጋጋሚ እየተከሰተ ያለውን ግድያዎች በመፈጸም ላይ ያሉት “ከምዕራብ ጉጂ፤ ገላና ወረዳ የሚነሱ ታጣቂዎች ናቸው” ሲሉ የሚዲያ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት አስተባባሪው ወንጅለዋል

በአካባቢው በተደጋጋሚ እየተከሰተ ያለውን ግድያዎች በመፈጸም ላይ ያሉት “ከምዕራብ ጉጂ፤ ገላና ወረዳ የሚነሱ ታጣቂዎች ናቸው” ሲሉ የሚዲያ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት አስተባባሪው ወንጅለዋል። “የታጠቁ ሚሊሺያዎች ናቸው ይህን ጥቃት ያደረሱት። ዘመናዊ ክላሺንኮቭ እና መትረየስ እንዲሁም በርከት ያለ ጥይት ነው የሚይዙት። የሚንቀሳቀሱት ከ50 እና ከ60 በላይ በቡድን ሆነው ነው” ብለዋል። 

ከዚህ ቀደም እንደዚህ አይነት ድርጊት የሚፈጽሙት በአካባቢው የሚንቀሳቀሱት “የኦነግ- ሸኔ ታጣቂዎች ናቸው” የሚል መረጃ ይወጣ እንደነበር ያስታወሱት አስተባባሪው፤ እውነታው ግን ከዚህ የተለየ ነው ባይ ናቸው። በአካባቢው ከፍተኛ “የታጣቂዎች ክምችት” እንዳለ ከነዋሪዎች መስማታቸውንና ይህንኑም ዛሬ ወደ አካባቢው የተንቀሳቀሰው የደቡብ ክልል ልዩ ኃይል እና የፌደራል ፖሊስ አባላት ማረጋገጣቸውን ይጠቅሳሉ። 

“አሁንም ከፍተኛ ስጋት አለ። ዛሬ የፌደራል ፖሊስ እና የደቡብ ክልል ልዩ ኃይል አባላት ጥቆማ ደርሷቸው ወደ ከሬዳ እና ዶርቤዶ ቀበሌዎች ሄደዋል። ታጣቂዎቹ ሁለቱም ቦታ ላይ ተከማችተው ስለነበር ወደዚያ መቅረብ አልፈለጉም። ሁኔታው ‘ከአቅማችን በላይ ነው’ ብለዋል” ሲሉ የጸጥታ ኃይሎች ጭምር ሁኔታው አሳሳቢ መሆኑን መናገራቸውን ይጠቁማሉ። 

የአማሮ ኬሌ ከተማ

እንደ አቶ አማረ ገለጻ፤ በአማሮ ልዩ ወረዳ ውስጥ ከሚገኙ 35 ቀበሌዎች ውስጥ አስራ ስድስቱ “የስጋት ቀጠና ውስጥ” ያሉ ናቸው። በአካባቢው ለዓመታት የቀጠለው አለመረጋጋት መንስኤ የ“መሬት ይገባኛል” ጥያቄ መሆኑን የሚዲያ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት አስተባባሪው ያስረዳሉ። በ2008 ዓ.ም በአካባቢው የነዳጅ ፍለጋ ቅኝት ከተደረገ በኋላ የመሬት ጥያቄው ከተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነት ጉዳይ ጋር መያያዙን ያብራራሉ። 

በካናዳ እና የብሪታንያ ኩባንያ የተደረገው ይሄው የመጀመሪያ ደረጃ የነዳጅ ፍለጋ ጥናት፤ በአማሮ ልዩ ወረዳ ውስጥ ያሉ 18 ቀበሌዎችን እና በምዕራብ ጉጂ ዞን ስር ያሉ አራት ቀበሌዎችን ያካለለ ነበር። የነዳጅ ጥናት ፍለጋው “seismic survey” ከተሰኘው የጥናት ደረጃ ባያልፍም፤ በአካባቢው አሁንም ቢሆን “ነዳጅ ሊገኝ ይችላል” የሚል ተስፋ አለመሟጠጡን አቶ አማረ አመልክተዋል። 

በአማሮ እና ምዕራብ ጉጂ አዋሳኝ ቦታዎች ያለውን የጸጥታ መደፍረስ የደቡብም ሆነ የኦሮሚያ ክልል ዘላቂ መፍትሄ ሊሰጡት ባለመቻላቸው “የሰዎች ህይወት በየጊዜው እየጠፋ ይገኛል” ይላሉ የሚዲያ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት አስተባባሪው። በአጎራባች ቦታዎቹ የሚታየውን ይህን የጸጥታ ችግር ለመፍታት በማለም ባለፈው ሳምንት የእርቀ ሰላም መድረክ በአካባቢው ቢዘጋጅም ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ግቡን ሳያሳካ ተስተጓጉሏል። 

ስብሰባውን በቅርበት ሲከታተሉ የነበሩ የዓይን እማኞች፤ ጥቃቱን የፈጸሙት በአቅራቢያው በነበረ ጫካ ውስጥ ተሸሽገው የነበሩ ታጣቂዎች እንደሆኑ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በወቅቱ ገልጸው ነበር። በእርቀ ሰላሙ ስብሰባ ላይ ተሳታፊ በነበረ ታዳሚ የተቀረጸና “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እጅ የገባ ቪዲዮም በድንገት በተከፈተ ተኩስ ስብሰባው ሲቋረጥ ያሳያል። 

ተኩሱ የጀመረው የአካባቢው ባለስልጣናት የሁለቱን አጎራባች ስፍራዎች ነዋሪዎችን እያነጋገሩ ባለበት በአስረኛው ደቂቃ ላይ እንደነበር ከቪዲዮው ማየት ተችሏል። ከተኩሱ በኋላ የስብሰባው ታዳሚዎች ነፍሳቸውን ለማትረፍ በየአካባቢው በመበታተን፤ በአቅራቢያው ወደነበረ ጫካ ሲሸሹም በቪዲዮው ተቀርጿል። አለፍ አለፍ እያለ የሚሰማው ተኩሱ ለአምስት ደቂቃዎች ያህል መዝለቁን በቪዲዮው ተመልክቷል።       

ባለፈው ሳምንት ሰኞ፤ የካቲት 29 በተፈጸመው በዚሁ ጥቃት የአማሮ ልዩ ወረዳ የብልጽግና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አቶ ዳኛቸው አቼላን ጨምሮ ስድስት ሰዎች ተገድለዋል። በጥቃቱ የልዩ ወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ወገኔ ደጀኔ እና ሌሎች ስድስት ሰዎች በጠና ቆስለዋል። ተጎጂዎቹ በአርባምንጭ፣ ሀዋሳ እና በአማሮ ኬሌ በሚገኙ ሆስፒታሎች እስካሁንም የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው እንደሆነ አቶ አማረ አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)