በተስፋለም ወልደየስ
ባለፉት ጥቂት ቀናት በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የተከሰተው የጸጥታ ችግር በፓርላማ አከራካሪ ጥያቄዎችን አስነሳ። ጥያቄዎቹ የተነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ዛሬ ማክሰኞ በተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ከፓርላማ አባላት የሚቀርቡ ጥያቄዎችን ባስተናገዱበት ወቅት ነው።
የፓርላማ አባላቱ ያነሷቸው ጥያቄዎች በወቅታዊ ጉዳዮች እና በ10 ዓመቱ የልማት ዕቅድ ላይ ያተኮሩ ነበሩ። ወቅታዊ የፖለቲካ እና የጸጥታ ጉዳዮችን በተመለከተ በምክር ቤት አባላት ከቀረቡ ጥያቄዎች ውስጥ የሰሜን ሸዋ የጸጥታ ጉዳይ ያነሱቱ፤ በገዢው ፓርቲ የተወካዮች ምክር ቤት አባላት ዘንድ ያለውን ልዩነት ያሳዩ ሆነዋል።
ከሰሞኑ በአጣዬ፣ ማጀቴ፣ ሸዋ ሮቢት እና አካባቢው የተከሰተው ችግር “በዜጎች ላይ የህይወት መጥፋት ተከስቷል ያሉት” ዘላለም ታረቀኝ የተባሉ የፓርላማ አባል ፤ በችግሩ ምክንያት የሞቱ የአካባቢው ነዋሪዎች “ዛሬም ድረስ ሬሳቸው እንዳይነሳ እየተደረገ ነው” ብለዋል።
ችግሩን “ብሔር ተኮር” ሲሉ የጠሩት የፓርላማ አባሉ፤ በአማራ ብሔር ላይ የአሁኑን ጨምሮ ተከታታይ የሆነ “የህይወት መጥፋት” እና “ጉዳት እየደረሰበት ይገኛል” ሲሉ ከስሰዋል። በመንግስት በኩል “ዜጎች ጉዳት ሳይደርስባቸው አስቀድሞ መከላከል ለምን አልተቻለም?” የሚል ጥያቄ በህዝቡ ዘንድ እንዳለ ጠቅሰዋል። “እንደዚህ አይነት የአማራ ሞቶች፣ መፈናቀሎች፣ ሰቆቃዎች የሚቆሙት መቼ ነው?” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጠይቀዋል።
መሐመድ ሐሰን የተባሉ የፓርላማ አባል ግን በአካባቢው የተቀሰቀሰው ግጭት በመግለጫዎች እና በመገናኛ ብዙሃን ከሚነገረው ተቃራኒ ነው ባይ ናቸው። በአካባቢው ካለው ችግር ጀርባ ያለው “ኦነግ ሸኔ ነው” የሚለው መግለጫ፤ ችግሩን በ“ዳቦ ስም” ለመሸፈን የሚደረግ ጥረት ነው የሚል እምነታቸውንም አንጸባርቀዋል። እንደ እርሳቸው ገለጻ በተለይ በወሎ አካባቢ ያለው ግጭት፤ “በኦሮሞ አርሶ አደሮች እና በአማራ ልዩ ሃይል መካከል” የተካሄደ ነው።
“በተለይ በሸዋ ሮቢት ሆስፒታል በማንነታቸው ብቻ በአሰቃቂ ሁኔታ የተጨፈጨፉ ቁስለኞች፣ ታማሚዎች፣ አስታማሚዎች እና እናቶች [አሉ]። በነገራችን ላይ የ10 ሰው አስክሬን ዛሬም አልወጣም። እዚያው ሆስፒታሉ ውስጥ ፈንድቶ እየሸተተ ነው” ሲሉ ከስሜታቸው ጋር እየታገሉ ለፓርላማው ገልጸዋል።
እንደ አቶ መሐመድ ሁሉ ሌላ የፓርላማ አባልም በሰሜን ሸዋ እና በኦሮሚያ ልዩ ዞን የተከሰተው ግጭት፤ በአማራ ክልል መግለጫዎችም ሆነ በብዙሃን መገናኛዎች ዘገባዎች “በሚዛናዊነት አልቀረበም” ሲሉ ወቀሳ አቅርበዋል። በአካባቢው የተከሰተውን “ትክክለኛ ችግር አውጥቶ ጉዳዩን ከማርገብ ይልቅ” የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች እና የተወሰኑ የብዙን መገናኛዎች፤ “ህብረተሰቡ ላይ ‘ኦነግ ሸኔ’ የሚል ያልሆነ ታርጋ በመለጠፍ የአካባቢውን ነዋሪ ለበለጠ እልቂት እያነሳሱ ነው” ሲሉ ወንጅለዋል።
“አማራ ሲሞት ንጹሃን፤ ኦሮሞ ሲሞት ኦነግ መሆን የለበትም” ያሉት የፓርላማ አባሏ፤ “በአካባቢው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን፤ በህዝባችን ላይ በቀጥታ ጦርነት የከፈተው የአማራ ልዩ ሃይል ከዞናችን እንዲወጣና የፌደራል መንግስት የጸጥታ መዋቅሩን እንዲመራ እንዲደረግልን እንጠይቃለን” ሲሉ አሳስበዋል።
በሁለቱ የፓርላማ አባላት የቀረቡት መረር ያሉ አስተያየቶች፤ አቶ ሰጠኝ አዲሱ በተባሉ የተወካዮች ምክር ቤት አባል ተተችቷል። የፓርላማ አባላት በተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ ያሉት “የኢትዮጵያን ህዝብ ወክለው” እንደሆነ የጠቆሙት እኚሁ የምክር ቤት አባል፤ አባላቱ ለኢትዮጵያ ህዝብ ማስተላለፍ የሚገባቸው “እውነተኛ፣ ትክክለኛ እና የተረጋገጠ መረጃ” መሆን እንደሚገባው አጽንኦት ሰጥተዋል።
“አሁን በአንዳንድ የምክር ቤት አባላት የሚነገረው ግን በተለያየ ጽንፈኛ ፖለቲከኞች የሚገለጽን አስተሳሰብ፣ ባልተረጋገጠ እና ባልተጨበጠ ሁኔታ፣ የክልል መንግስትም ሆነ የፌደራል መንግስት በደንብ በማያውቀው፣ ባልተረዳው አግባብ የሚገለጸው ነገር ተገቢነት ያለው አይመስለኝም። ወደፊትም አይጠቅምም” ብለዋል።
በፓርላማ አባላት ለተነሱት ለእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፤ ጉዳዩን ከ“ሰፈር ሃሳብ” አቀንቃኝነት ጋር አያይዘውታል።
“ትልቁ የኢትዮጵያ ካንሰር፣ ነቀርሳ፤ እንዳናድግ፣ እንዳንለወጥ፣ እንዳንሻሻል እያደረገን ያለው ከሰፈራችን የዘለለ ነገር ማሰብ አለመቻል ነው። በሰፈር ሀሳብ ኢትዮጵያን ማሳነስ እንጂ ማሳደግ አይቻልም። እባካችሁን ቢያንስ የፓርላማ አባላት ከዚህ ውጡ” ሲሉ ማሳሰቢያ አዘል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
“ኦሮሞ እና አማራን ለማባላት ገንዘብ፣ ጊዜ ሰውተው የሚሰቃዩ ሃይሎች እንዳሉ እያወቃችሁ፤ በተቀደደ ቦይ ውስጥ የምትገቡ ፖለቲከኞች፣ አመራሮች፣ ሰዎች ትገርሙኛላችሁ” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በከሚሴ አካባቢ ለተከሰተው ችግር “የጁንታው ቅልብተኞች” ያሏቸውን ሃይሎች ተጠያቂ አድርገዋል። እነዚህ ሃይሎች “ሁለት አይነት” እንደሆኑም ጠቁመዋል።
“አንደኛው ሃይል ‘ኦሮሞ አለቀ፤ ኦሮሞ ተነስ’ ይላል። [ሌላኛው] ሃይል አማራ አለቀ ተነስ ይላል። ደግሞ እኮ እርሱ አይነሳም፤ እዚያ ነው ያለው። ሁለቱም ግባቸው ህዝቡን በማባላት የጁንታውን ህልም ማሳካት ነው” ሲሉ ለፓርላማ አባላት ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)