የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ ከየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢ በላቀ ብዙ ችግር የገጠመው በኦሮሚያ ክልል መሆኑን መሪው ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ተናገሩ። በክልሉ ያሉ የፓርቲው አባላት መታሰር፣ መሰደድ እና የጽህፈት ቤቶች መዘጋት ባለፉት ሁለት ወራት ይበልጥ ተባብሷል ብለዋል።
ፕሮፌሰር ብርሃኑ ይህን ያሉት ፓርቲያቸው በአዳማ ከተማ ዛሬ እሁድ ረፋዱን በጠራው የምርጫ ቅስቀሳ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ነው። “በየትኛውም አካባቢ በፍጹም የማይጠበቁ ነገሮች የምንሰማው ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ነው” የሚሉት የኢዜማ መሪ፤ በክልሉ በመንግስት አስተዳደርም ሆነ በብልጽግና ውስጥ ያሉ አመራሮች የሚያስፈራቸው ምን እንደሆነ እንደማይገባቸው ለመርሃ ግብሩ ታዳሚያን ገልጸዋል።
በፓርቲያቸው ላይ ችግር በደረሰ ቁጥር የኦሮሚያ መስተዳድር ሰዎችን እና የክልሉ የብልጽግና ፓርቲ አመራሮችን እንደሚያነጋግሩ የጠቀሱት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ የባለስልጣናቱን ግፊት ተጠቅመው አባሎቻቸውን እንደሚያስፈቱ አስረድተዋል። “ለምንድነው ይሄ የሚሆነው?” ሲሉም የፓርቲው መሪ ጠይቀዋል።
“በዚህ አይነት ሰዎችን፣ ተፎካካሪዎችን ወይም ሌላ ሀሳብ ይዘው የሚመጡ ሰዎችን በማስፈራራት ስልጣን ላይ ብትወጡ፤ በጣም ደካማ መንግስት ነው የምትሆኑት። ለራሳችሁም አይጠቅማችሁም” ሲሉ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ለባለስልጣናቱ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
“ብዙሃኑ ህዝብ ይደግፈናል ካላችሁ፤ ድጋፉን የሚያሳያችሁ በነጻነት መምረጥ ሲችል ነው። የተለያዩ ሃሳቦችን ሰምቶ፣ ከእነዚያ ሃሳቦች ውስጥ ‘የቱ ይሻለኛል’ ብሎ ሲመርጣችሁ፤ ያኔ ስልጣናችሁ ጠንካራ ነው። የህዝብ ድጋፍ ያለው፤ የህዝብ ፍላጎትን የሚያንጸባርቅ ነው ሁሌ ጠንካራ” ሲሉም አክለዋል።
በኦሮሚያ አካባቢ ያሉ የብልጽግና ወይም የመንግስት ሃላፊዎች፤ ከቅርብ ጊዜ የኢትዮጵያ ታሪክ መማር ይችሉ እንደነበር የኢዜማ መሪ በንግግራቸው ጠቁመዋል። ለዚህም ሕወሓት በትግራይ ህዝብ ላይ አድርሶታል ያሉትን “ችግር” በምሳሌነት አንስተዋል።
“‘እወክልሃለሁ’ ብሎ የሚመጣ በዘር ላይ የተቧደነ ቡድን ያንን ‘እወክልሃለሁ’ የሚለውን ህዝብ እንኳ እንዴት ችግር ውስጥ እንደሚከት፤ ከትግራይ በላይ ሌላ ቦታ ልናየው አንችልም። የተወሰነ ጊዜ ሊዘርፉ ይችላሉ። የተወሰነ ጊዜ በዚያ ዝርፊያ ከመንግስት ጋር ተጣብቀው፤ ገንዘብ የሚሰበስቡ ሰዎች ይኖሩ ይሆናል። በዘላቂነት ግን ያንን ህብረተሰብ ሊጠቅሙት እንደማይችሉ ከሕወሓት በላይ ምንም ማስተማሪያ የለም” ብለዋል ፕሮፌሰር ብርሃኑ። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)