በመተከል፣ ካማሺ እና ወለጋ ዞኖች ለመራጮች ምዝገባ አስፈጻሚዎች ስልጠና ማድረግ አልተቻለም – ምርጫ ቦርድ

በተስፋለም ወልደየስ 

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የጸጥታ ችግር በሚስተዋልባቸው ሁለት ዞኖች እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል በወለጋ አካባቢ ባሉ አራት ዞኖች ለመራጮች ምዝገባ አስፈጻሚዎች ስልጠና መስጠት አለመቻሉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ። ቦርዱ ይህን የገለጸው የመራጮች ምዝገባ ሂደትን እና ሌሎችንም ጉዳዮች በተመለከተ ዛሬ ቅዳሜ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በአዲስ አበባ ባደረገው ውይይት ላይ ነው። 

የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች እንዳሉት፤ የመራጮች ምዝገባ ከትናንት በስቲያ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል መጀመር ቢኖርበትም በተወሰኑ አካባቢዎች ለምርጫ አስፈጻሚዎች የሚሰጠው ምዝገባ ላይ መጓተት ተከስቷል። “ከጸጥታ ጋር እና ከእንደዚህ አይነት መሰል አሳሳቢ ሁኔታዎች ጋር [በተያያዘ] ስልጠና ያላደረግንባቸው ቦታዎች አሉ” ያሉት ሰብሳቢዋ፤ በቦታዎቹ ላይ ለምን ስልጠና ማካሄድ እንዳልተቻለ ለተሳታፊዎቹ በዝርዝር አስረድተዋል። 

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ስልጠና ያልተደረገባቸው ቦታዎች የመተከል እና ካማሺ ዞኖች መሆናቸውን የጠቆሙት ብርቱካን፤ የክልሉ መንግስት በሚያቀርበው መረጃ ላይ በመመስረት ለሁለቱ ቦታዎች “የተለየ የአመዘጋገብ ሂደት” እንደሚከተሉ ተናግረዋል። በመተከል ዞን ስልጠናውን ማካሄድ ያልተቻለው “ምን ያህሉ የህብረተሰብ ክፍል ተፈናቅሎ እንደሚገኝ እና ምን ያህሉ ደግሞ ወደ ቀዬው እንደተመለሰ” ከክልሉ መንግስት የተጠየቀው መረጃ በቶሎ ባለመላኩ መሆኑን አብራርተዋል። የመተከሉ መረጃ በትላንትናው ዕለት ለቦርዱ መድረሱንም አክለዋል።        

“በካማሺ ዞን ምናልባት የተወሰኑ ቦታዎች ላይ ልናደርግ እንችላለን። ሆኖም ግን የክልሉ መንግስት የትኛዎቹ ቦታዎች ለስልጠናም ሆነ ለመራጮች ምዝገባ አፈጻጸም ምቹ እንደሆኑ፣ የትኞቹ አሳሳቢ እንደሆኑ ለይቶ እንዲያቀርብ ተጠይቆ ምላሽ ስላልሰጠ እርሱን እየጠበቅን ነው” ሲሉ ከምዝገባው መስተጓጉል ጀርባ ያለውን ምክንያት ገልጸዋል።    

በኦሮሚያ ክልል ስልጠና ያልተካሄደባቸው በተለምዶ አራቱ ወለጋዎች ተብለው የሚጠሩት ምዕራብ ወለጋ፣ ቄለም፣ ሆሮጉድሩ እና ምስራቅ ወለጋ ዞኖች መሆናቸውን የቦርዱ ሰብሳቢ አመልክተዋል። በእነዚህ ቦታዎችም እንደ ቤኒሻንጉል ሁሉ ከኦሮሚያ ክልል መንግስት የሚጠበቅ መረጃ ተጠናቅቆ ስላልገባ ችግሮች እንደገጠሟቸው አክለዋል። 

ከሁለቱ ክልሎች በተጨማሪ ከሰሞኑ የጸጥታ መድፈረስ ችግር በተከሰተባቸው፤ የአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ እና የኦሮሞ ብሔረሰብ ልዩ ዞን አራት ምርጫ ክልሎች ላይ፤ የምርጫ አስፈጻሚዎች ስልጠናም ሆነ የመራጮች ምዝገባ ቁሳቁሶች ስርጭት ቦርዱ ማካሄድ አለመቻሉን ሰብሳቢዋ አብራርተዋል። 

“ልዩ የኦሮሚያ ዞን አማራ ክልል አሁን ሰሞኑን ባጋጠሙ ሁኔታዎች የተነሳ፤ አንድ ሁለት ምርጫ ክልሎች ላይ የተሟላ ስልጠና ማድረግ አልቻልንም፤ የዕቃ ስርጭቱም እንደዚያው [ሆኗል]። የሰሜን ሸዋ ዞን ላይ ደግሞ ያሉት በምታውቁት የአጣዬ ችግር የተነሳ ኤፌሶን፣ ማጀቴ የሚባሉት ምርጫ ክልሎች እንዲሁ የዘገዩበት ሁኔታ አለ” ብለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)