በቅድስት ሙላቱ
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲ በኢትዮጵያ ያሉ የኤርትራ ወታደሮች መቼ እንደሚወጡ “መረጃ የለኝም” አሉ። የወታደሮቹ ብዛት ምን ያህል እንደሆነ እንደማያውቁም ዛሬ ማክሰኞ በነበራቸው ሳምንታዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።
መግለጫውን የተከታተሉት ጋዜጠኞች ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ “የኤርትራ መንግስት ጦሩን ከኢትዮጵያ ድንበር ለማስወጣት መስማማቱን” ባለፈው ሳምንት መግለጻቸውን ጠቅሰው፤ ወታደሮቹ መቼ ኢትዮጵያን ለቅቀው እንደሚወጡ ጥያቄ አቅርበዋል። ቃል አቃባዩ “በድንበር አካባቢ ያለው ኃይል ይወጣል የሚል ነው እንጂ፤ ‘መቼ ነው የሚወጣው እና ስንት ነው’ የሚለው መረጃ ስለሌለኝ፤ ምናልባት መረጃ ስናገኝ መነጋገር እንችላለን” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
“ ‘ድንበር አካባቢ የህግ ማስከበር እንቃስቃሴ በነበረበት ሰዓት፤ ወደ ድንበር ገብቶ የነበረው የኤርትራ ሃይል ይወጣል’ የሚል መረጃ already ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በቀደም በአስመራ [ጉብኝት] ካደረጉ በኋላ ስለሰማን፤ እርሱ መረጃ በቂ ነው” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወደ አስመራ የተጓዙት፤ የኤርትራ ወታደሮች በኢትዮጵያ እንደሚገኙ ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ ካመኑ ከአንድ ቀን በኋላ ነው። የኤርትራ ወታደሮች ጉዳይ የተነሳው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከፓርላማ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት የመደበኛ ስብሰባ ወቅት ነበር።
ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ በተካሄደው በዚሁ ስብሰባ፤ የኤርትራ ወታደሮች የኢትዮጵያን ድንበር ያቋረጡት “በደህንነት ስጋት ምክንያት” እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። በትግራይ የተጀመረው “ኦፕሬሽን” ሲገባደድ ወደ “ድንበር መከላከል ደረጃ” እንደሚደረስም ጠቁመዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአስመራ ጉብኝታቸው በኋላ ባወጡት መግለጫ፤ ኢትዮጵያ እና ኤርትራን የሚያዋስነውን ድንበር የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት እንደሚጠብቅ አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉብኝታቸው ስለተደረሰው ስምምነት ያሉት እና የኤርትራ መንግስት ስለ ጉብኝቱ ያወጣው መግለጫ ይዘት መለያየት በጋዜጠኞች ዘንድ ጥያቄ አስነስቷል። የሁለቱ ሀገራት በየፊናቸው ያወጡት መግለጫ “ሊለያይ ይችላል” ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቃባይ፤ በድንበር አካባቢ ያሉት ሃይሎች እንደሚወጡ የተላለፈው መረጃ “ትክክለኛ ነው” ብለዋል። “ይሄ በማንኛውም ጊዜ ሊተገብር የሚችልበት ሁኔታ ነው ያለው” ሲሉ በድጋሚ ማረጋገጫ ሰጥተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)