የፌደራል ዋና ኦዲተር ከኃላፊነታቸው ተሰናበቱ

ላለፉት 12 ዓመታት የፌደራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ዋና ዳይሬክተር ሆነው የሰሩት አቶ ገመቹ ዱቢሶ ከኃላፊነታቸው ተሰናበቱ። የሥራ ጊዜያቸውን በማጠናቀቃቸው ከኃላፊነታቸው ለተሰናበቱት አቶ ገመቹ በመስሪያ ቤታቸው የሽኝት መርሐ- ግብር ተከናውኖላቸዋል።

አቶ ገመቹ ከኃላፊነታቸው የተሰናበቱት የሥራ ዘመናቸው በመጠናቀቁ ነው። የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ማቋቋሚያ አዋጅ “የዋና ኦዲተሩ እና ምክትሎቹ የሥራ ዘመን ስድስት አመት ይሆናል” በማለት ይደነግጋል። እንደ አቶ ገመቹ ሁሉ፤ በመስሪያ ቤቱ የድጋፍ ዘርፍ ምክትል ዋና ኦዲተር የሆኑት ወይዘሮ ባዩሽ ተስፋዬም እንዲሁ የተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በተገኙበት ተሸኝተዋል።   

ዋና ኦዲተሩም ሆነ አራት ረዳቶቹ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በፓርላማ የሚሾሙ ሲሆን ተጠሪነታቸውም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው። በዚህ የኃላፊነት ቦታ ላይ የማንኛውም ፖለቲካ ፓርቲ አባላት እንደማይሾም የማቋቋሚያ አዋጁ ይደነግጋል።

በሰኔ 2000 ዓ.ም የተሾሙት አቶ ገመቹ በስራ ጊዜያቸው ከሶስት ጠቅላይ ሚኒስትሮች ጋር ሰርተዋል። አቶ ገመቹ የመሩት የፌደራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የኢትዮጵያ መንግሥት ተቋማትን የገንዘብ አስተዳደር፣ የሒሳብ አያያዝ፣ የገንዘብ አሰባሰብ እና ወጪ እየመረመረ ጠጠር ያሉ ሪፖርቶችን ለተወካዮች ምክር ቤት ሲያቀርብ ቆይቷል። 

ዋና ኦዲተሩ ለፓርላማ ባቀረቧቸው ሪፖርቶች፤ ያለ ሕግ እና ሥርዓት የተፈጸሙ ክፍያዎች፣ የየተቋማቱን ሥርዓት ያልተከተሉ ግዢዎች፤ በወቅቱ ያልተወራረደ ውዝፍ ሒሳብ እንዲሁም የሒሳብ አያያዝ ግድፈቶችን አጋልጠዋል። ከዚህም በተጨማሪ መስሪያ ቤታቸው በየተቋሟቱ ባደረገው ማጣራት ከሚገባ በላይ የተከፈሉ እንዲሁም ከሰራተኞች ያልተሰበሰቡ የሥራ ግብር ክፍያዎች ማግኘቱን ሲያስታውቁ ቆይተዋል።   

የ56 አመቱ አቶ ገመቹ በመጀመሪያ ዲግሪ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አካውንቲግ ኋላም የገንዘብ አስተዳደር (Financial Management) በስኮትላንድ ግላስጎው ካሌዶንያን ዩኒቨርሲቲ አጥንተዋል። ተሰናባቹ ኃላፊ የፌደራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ዋና ዳይሬክተር ሆነው ከመሾማቸው በፊት፤ በኦሮሚያ ብድር እና ቁጠባ ኩባንያ፣ በኦሮሚያ ክልል የንግድ ቢሮ የኦዲትና ኢንስፔክሽን ቢሮ፣ በኦሮሚያ ክልል ሥራና ከተማ ልማት ቢሮ በኃላፊነት አገልግለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)