በቅድስት ሙላቱ
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከእነ አቶ ጃዋር መሐመድ የህክምና ጉዳይ ጋር በተያያዘ የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር እና የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ችሎት ፊት ቀርበው እንዲያስረዱ ትዕዛዝ ሰጠ። ፍርድ ቤቱ ዛሬ ትዕዛዙን የሰጠው በተከሳሽ ጠበቆች የቀረበለትን አቤቱታ ከመረመረ በኋላ ነው።
አቶ ጃዋርን ጨምሮ አራት ተከሳሾችን የወከሉት ጠበቆች አቤቱታቸውን ያቀረቡት፤ ደንበኞቻቸው በግል ሆስፒታል ህክምና እንዲያገኙ በፍርድ ቤት የተላለፈላቸው ውሳኔ መጣሱን በመቃወም ነበር። በግል ሆስፒታል ህክምና እንዲያገኙ በፍርድ ቤት የተወሰነላቸው ጃዋር መሐመድ፣ በቀለ ገርባ፣ ሐምዛ አዳነ እና ደጀኔ ጣፋ የካቲት 9፤ 2013 ወደ ላንድ ማርክ ሆስፒታል በመሄድ ላይ ሳሉ በጸጥታ አካላት ከመንገድ እንዲመለሱ መደረጉ ነበር ለአቤቱታው መነሻ ምክንያት የሆነው።
የተከሳሽ ጠበቆች ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባቀረቡት ቅሬታ ላይ፤ “ፍርድ ቤት በግል ሆስፒታል እንዲታከሙ ፈቅዶ ሳለ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የፍርድ ቤትን ትዕዛዝ ተላልፎ ጦር ኃይሎች ሆስፒታል ይታከሙ ማለቱ ህጉን የተከተለ አይደለም” ሲሉ አቤት ብለዋል። “ፍርድ ቤቱ ትዕዛዙ ትክክለኛ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ሊገመግም ይገባል” በማለት ችሎቱ ጉዳዩን እንዲመረምር ጠይቀዋል።
የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አራቱ ተከሳሾች በጦር ኃይሎች ሆስፒታል እንዲታከሙ ትዕዛዝ ያስተላለፈው፤ ተጠርጣሪዎቹ በግል ህክምና ተቋም ይታከሙ በሚል በፍርድ ቤት የተሰጠው ውሳኔ “ተገቢነት እና “ሕጋዊ መሰረት” ላይ ጥያቄ በማንሳት ነው። የይግባኝ ማመልከቻ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት በማቅረብ ጭምር የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ የተቃወመው ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ፤ ትዕዛዙ እንዲታገድ በማመልከቻው ጠይቆ ነበር።
በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዶ/ር ጌድዮን ጢሞትዮስ ፊርማ ለቃሊቲ ማረሚያ ቤት በየካቲት 9፤ 2013 የተላከ ደብዳቤ፤ የይግባኝ ክርክሩ እልባት እስኪያገኝ ድረስ ማረሚያ ቤቱ ተከሳሾችን ወደ ጦር ኃይሎች ሆስፒታል ወስደው እንዲያሳክሙ “መመሪያ” መሰጠቱን ገልጿል። መመሪያው የተሰጠው “የተከሳሾች ጤና አደጋ ላይ እንዳይወድቅ” በማሰብ እንደሆነ በደብዳቤው ተገልጿል። ከዚህ በተጨማሪም ማረሚያ ቤቱ በማቋቋሚያ አዋጁ ላይ “የእስረኛ የጤና ሁኔታ እንዲጠበቅ የማድረግ ኃላፊነት የተጣለበት” በመሆኑ መመሪያውን እንዲያስፈጽም መታዘዙም ተጠቅሷል።
የተከሳሽ ጠበቆች አቤቱታ የቀረበለት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የጸረ ሽብር እና የሕገ መንግስታዊ ጉዳዮች ችሎት፤ “የፍርድ ቤቱ ውሳኔ እንዳይከበር ሚና ነበራቸው” ያላቸውን የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ተወካዮችን ከዚህ ቀደም በነበረው ውሎው አስጠርቶ ጠይቋል። ተከሳሾች ወደ ህክምና ተቋም በመሄድ ላይ ባሉበት ወቅት፤ የነበሩበት ተሽከርካሪ “በመንገድ ላይ ታግቶ እንዲቆም አድርገዋል” የተባሉ ኃላፊ ደግሞ ለዛሬ ረቡዕ መጋቢት 22፤ 2013 እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር።
“እዚያ የተገኘሁት ተከሳሾችን ለማጀብ ነው እንጂ ማንንም ለማገት አይደለም”
ኢንስፔክተር መገርሳ ገሙ – የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን የፈጥኖ ደራሽ ኃይል አዛዥ
የችሎቱን ትዕዛዝ ተቀብለው ዛሬ ችሎት ፊት የቀረቡት የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን የፈጥኖ ደራሽ ኃይል አዛዥ ኢንስፔክተር መገርሳ ገሙ በዕለቱ የሆነውን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል። እነ አቶ ጃዋር ወደ ላንድ ማርክ ሆስፒታል ሲወሰዱ አጅበዋቸው እንደበር የጠቀሱት አዛዡ፤ አፍሪካ ህብረት አካባቢ ሲደርሱ ተከሳሾቹ ያሉበት ተሽከርካሪ እንዲቆም በስልክ ትዕዛዝ እንደተላለፈላቸው ተናግረዋል።
ትዕዛዙን ያስተላለፈው አካል ማን እንደሆነ በፍርድ ቤቱ በተከታይነት ለቀረበው ጥያቄ ኢንስፔክተር መገርሳ ምላሽ በሰጡት ምላሽ፤ የደወሉላቸው የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀማል አባሶ መሆናቸውን ገልጸዋል። የኮሚሽነሩን ትዕዛዝ ተከትሎ እነ አቶ ጃዋር የነበሩበትን ተሽከርካሪ ማስቆማቸው ያመኑት አዛዡ፤ “እዚያ የተገኘሁት ተከሳሾችን ለማጀብ ነው እንጂ ማንንም ለማገት አይደለም” ብለዋል።
የኢንስፔክተር መገርሳን ማብራሪያ ያደመጠው ችሎቱ አዛዡ “ከጉዳዩ ነጻ ናቸው” በሚል አሰናብቷቸዋል። “የፍርድ ቤትን ትዕዛዝ ወደ ጎን በማለት ተከሳሾች ጦር ኃይሎች ሄደው እንዲታከሙ አድርገዋል” የተባሉት፤ የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀማል አባሶ እና የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዶ/ር ጌድዮን ጢሞትዮስ በቀጣይ ቀጠሮ በአካል ቀርበው ሁኔታውን እንዲያስረዱ ችሎት ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ሁለቱ የስራ ኃላፊዎች በአካል ይቅረቡ የተባለው በ20 ቀናት ውስጥ ባለ እና ከችሎት በኋላ በሚያዝ ቀጠሮ ነው። የስራ ኃላፊዎቹ ምላሽ የሚታየው ከተከሳሾች ዋና የፍርድ ክርክር ሂደት በተናጠል እንደሚሆንም ፍርድ ቤቱ አሳውቋል።
በዛሬው የችሎት ውሎ አቶ ጃዋርም ሆነ ሌሎቹ ተከሳሾች ፍርድ ቤት አልቀረቡም። ተከሳሾቹን ወክለው በችሎት የተገኙት ከጠበቆቻቸው አንዱ የሆኑት አቶ ከዲር ቡሎ ናቸው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)