በቅድስት ሙላቱ
በሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ዘንድ አንቱታን ያተረፉት አቶ ተፈራ ዊላ፤ በብዙዎች ዘንድ የሚታወቁት “ለተቸገረ ሁሉ ደራሽ” በመሆናቸው ነው። ይህ የበጎ አድራጎት ተግባራቸው በሀዋሳ ብቻ ሳይሆን በብዙ የሀገሪቱ ክፍሎች በርካታ ወዳጅ እንዳፈራላቸው የቅርብ ሰዎቻቸው ይናገራሉ። ተጨዋች እና በቀላሉ ተግባቢ መሆናቸውም ለዕውቅናቸው እንዲናኝ ምክንያት ሆኗል።
“የሆስፒታልን ደጃፍ እምብዛም ረግጠው አያውቁም” የሚባልላቸው አቶ ተፈራ፤ ከሰሞኑ ወደ ህክምና ተቋም ጎራ እንዲሉ ያደረጋቸው የህመም ስሜት ገጥሟቸው ነበር። የህመሙ ስሜት በመጀመሪያ “ጉንፋን ነው” በሚል ችላ ብለውት የነበረ ቢሆንም፤ ከቀናትም በኋላ አለመጥፋቱ ግን በቅርብ ሰዎቻቸው ጥርጣሬ ማስከተሉ ለነገሩ ትኩረት እንዲሰጡ አስገድዷቸዋል። የአቶ ተፈራ ወዳጆች ከህመማቸው ምልክት ተነስተው የተጠራጠሩት “ምናልባትም በሽታው ኮሮና ሳይሆን አይቀርም” የሚል ነበር።
ቅዳሜ መጋቢት 18፤ 2013 ወደ ሀዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል የሄዱት አቶ ተፈራ፤ ኮሮና ይኖርባቸው እንደው ለማወቅ ናሙና ከሰጡ በኋላ ውጤታቸው እስኪታወቅ በህክምና ተቋም እንዲቆዩ ይደረጋሉ። ከሁለት ቀናት በኋላ የመጣው የምርመራ ውጤት ታዲያ የቅርብ ሰዎቻቸውን ጥርጣሬ ያረጋገጠ ሆነ።
ውጤቱ ከጠበቁት በተቃራኒ የሆነባቸው አቶ ተፈራ፤ የጤና ባለሙያዎች የነገሯቸውን ለማመንም ሆነ ለመቀበል ተችግረው እንደነበር የሚያውቋቸው ይናገራሉ። በኮሮና ቫይረስ እንደተጠቁ ማወቃቸው የፈጠረባቸው ጭንቀት የጤንነታቸው ሁኔታ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲያሽቆለቆል ሰበብ መሆኑንም ይገልጻሉ።
የአቶ ተፈራ ሁኔታ ያሳሰባቸው የህክምና ባለሙያዎች፤ የአተነፋፈስ ስርዓት እንዲስተካከል የሚያግዘውን ኦክስጅን ሊያጠልቁላቸው ሙከራ ቢያደርጉም፤ ኸህመምተኛው የገጠማቸው ብርቱ እምቢተኝነት ግን ያሰቡትን ማድረግ አላስቻላቸውም። የመተንፈሻ አጋዥ መሳሪያ ለማድረግ አሻፈረኝ ያሉት አቶ ተፈራ፤ በኮሮና መያዛቸው የተነገራቸውን ዕለት ተሻግረው ሌላ ቀን ማየት አልታደሉም። የዚያኑ ዕለት አመሻሽ ላይ ህይወታቸው ማለፉን የቅርብ ሰዎቻቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
በግላቸው የኢንቨስትመንት ስራ ላይ ለመሰማራት በእንቅስቃሴ ላይ እንዳሉ እንዳለፉት አቶ ተፈራ ሁሉ፤ በሲዳማ ክልል በኮሮና በሽታ ምክንያት ስምንት ሰዎች በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ብቻ ህይወታቸውን አጥተዋል። የክልሉ ዋና ከተማ የሆነችው ሀዋሳ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከኮሮና ስርጭት ጋር በተያያዘ ስሟ ሲነሳ ሰንብቷል። በያዝነው መጋቢት ወር የወጡ መረጃዎች እንደውም ሀዋሳን፤ በሽታው የመገኘት ዕድል በጣም ከፍተኛ ከሆነባቸው ከተሞች በአንደኛ ደረጃ አስቀምጠዋታል።
ሀዋሳ ይህንን ደረጃ የያዘችው በመጋቢት 1 እና 2 እንደነበር በጤና ሚኒስቴር የህክምና አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ያዕቆብ ሰማን በዚያኑ ወቅት በማህበራዊ ትስስር ገጾቻቸው ያስነበቧቸው መረጃዎች ያመለክታሉ። እንደ አቶ ያዕቆብ ገለጻ፤ በሁለቱ ቀናት በከተማይቱ የተመዘገበው የበሽታው የመገኘት ምጣኔ ሀዋሳን በቅርብ ርቀት ከሚከተሏት ሶስት ከተሞች በላይ እንድትሆን አድርጓታል። ሀዋሳ በመጋቢት ወር የመጀመሪያ ቀን 38.5 በመቶ ምጣኔ ማስመዝገቧን የዋና ዳይሬክተሩ መረጃ ያሳያል። የምጣኔው ቁጥር በተከታዩ ቀን በ3.5 በመቶ ከፍ ማለቱም በመረጃው ተመልክቷል።
ከእነዚህ ቀናት በኋላ የወጡ ተመሳሳይ መረጃዎች፤ የበሽታው ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ ከታየባቸው ቦታዎች መካከል ሀዋሳ የምትገኝበት የሲዳማ ክልል የመጀመሪያውን ደረጃ መያዙን ጠቁመዋል። ከመጋቢት 5 ጀምሮ በነበሩ አራት ተከታታይ ቀናት ሲዳማ በኮሮና በሽታ ስርጭት ከፍተኛውን ቁጥር ማስመዝገቡን በዶ/ር ያዕቆብ የተጠናቀረው መረጃ ይፋ አድርጓል። ሲዳማ ባለፈው ሳምንት መጨረሻም፤ የኮሮና በሽታ ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ የታየባቸው ክልሎችን ዝርዝር መምራት መቀጠሉ ተገልጿል።
በሲዳማ የመጀመሪያው የኮሮና ቫይረስ ህመምተኛ የተገኘው፤ በሽታው ወደ ኢትዮጵያ ከገባ ከሁለት ወር በኋላ በግንቦት ወር 2012 ዓ.ም ነው። በክልሉ እስከ ከዚህ ሳምንት ድረስ በአጠቃላይ 6,538 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው በምርመራ ተረጋግጧል። ከእነዚህ ሰዎች መካከል 110 ያህሉ በበሽታው ህይወታቸውን ማጣታቸውን ከሲዳማ ክልል የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዮት የተገኘ መረጃ ያመለክታል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ በኮሮና ቫይረስ የሞቱ ሰዎች 2,915 መድረሱን ትላንት አርብ መጋቢት 24 ያስታወቀው የጤና ሚኒስቴር፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የበሽታው ስርጭት በአሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ እየሰጠ ይገኛል። ኢትዮጵያ የመጀመሪያው የኮሮና ቫይረስ ተጠቂን ያገኝችበትን የመጀመሪያ ዓመት ባሰበችበት መጋቢት 4፤ 2013 ብቻ፤ 1,483 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ሪፓርት ተደርጓል። በዚሁ ቀን 464 ሰዎች በጽኑ ህሙማን ክፍል ተኝተው ህክምናቸውን ሲከታተሉ እንደነበርም ተገልጿል። በዕለቱ በኮሮና ምክንያት 30 ግለሰቦች ሞተዋል።
ኢትዮጵያ ኮሮና የገባበትን አንደኛ ዓመት አስባ በዋለችበት ማግስት የተሰማው ዜናም ጥሩ አልነበረም። በዕለቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ የነበረው በኮሮና በሽታ የመያዝ ምጣኔው ከዚያ ቀደም ባልታየ ሁኔታ 24 በመቶ የገባበበት ነበር። ይህ ማለት “በሀገር አቀፍ ደረጃ ከአራት ሰው አንድ ሰው በኮቪድ ተይዟል ወይም ኮቪድ ሊኖርበት ይችላል እንደማለት ነው” ሲሉ ዶ/ር ያዕቆብ የሁኔታውን አሳሳቢነት አጽንኦት ሰጥተዋል።
በዚህ ቀንም ሆነ ከዚያ በኋላ በነበሩ ቀናት፤ በሽታው በከፍተኛ ሁኔታ ከተሰራጨባቸው ክልሎች ዝርዝር ላይ በመጀመሪያው ረድፍ ላይ የተቀመጠው ሲዳማ ነበር። ሀገር አቀፍ በበሽታ የመያዝ ምጣኔው ወደ 26 በመቶ ከፍ ባለበት በመጋቢት 15፤ የሲዳማ ክልል የበሽታ ስርጭት 68 በመቶ በመግባት የመሪነቱን ደረጃ ይዞ ቀጥሏል። በመጋቢት 21 በክልሉ በቫይረሱ መያዛቸው ሪፖርት የተደረጉ ሰዎች ቁጥር 118 የነበረ ሲሆን ይህ ቁጥር ከአንድ ወር በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር በ74 ሰዎች ከፍ ብሏል።
የሲዳማ ክልል በኮሮና በሽታ ስርጭት ከፍተኛውን ቦታ በተደጋጋሚ መያዙን መረጃዎች በግልጽ ቢያመለክቱም፤ የክልሉ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ግን መጠኑ ከሌሎች ክልሎች “የላቀ ነው” የሚለውን መረጃ አይቀበለውም። የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ማቴ መንገሻ፤ “ሲዳማ ከልል በስርጭት አንደኛ ነው ብዬ አላምንም” ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። “በህብረተሰቡ ውስጥ ያለውን ናሙና እየወሰድን ቢሆን ኖሮ በስርጭት ደረጃ ሊባል ይችል ነበር። አሁን ግን የመያዝ ምጣኔ ልንለው ነው የሚገባው” ሲሉ የተሰራጨውን መረጃ የማይቀበሉበትን ምክንያት አስረድተዋል።
በሲዳማ ክልል ያለው፤ የኮሮና በሽታን የመመርመር አቅም “ደካማ ነው” የሚሉት ዶ/ር ማቴ፤ በክልሉ የሚመረመሩት “በበሽታው ተጠርጥረው ወደ ጤና ተቋማት የሚመጡትን እና ቫይረሱ ሊኖርባቸው ይችላል ተብለው የሚገመቱትን ብቻ” እንደሆነ ያብራራሉ። በክልሉ የሚደረገው የላብራቶሪ ምርመራ ከደቡብ እና ከኦሮሚያ ከተሞች ህክምና ፈልገው የሚመጡ ታካሚዎች ያጠቃለለ መሆኑም ግንዛቤ ውስጥ ሊገባ እንደሚገባም ዋና ዳይሬክተሩ ይገልጻሉ።
በሀዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል ሲካሄድ የቆየው ይህ የላብራቶሪ ምርመራም ቢሆን የመመርመሪያ ማሽኑ በመበላሸቱ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ተቋርጧል። በሲዳማ ክልል ካሉ ከተለያዩ ቦታዎች የሚሰበሰብ ናሙና ውጤት በአሁኑ ወቅት እየተገለጸ ያለው፤ ወደ ደቡብ አና ኦሮሚያ ክልሎች የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቶች በመላክ ነው ተብሏል።
ዶ/ር ማቴ፤ ሲዳማ “በኮሮና ስርጭት ከኢትዮጵያ ቀዳሚ መሆኗን” ባይቀበሉም፤ በክልሉ ያለው የበሽታው ወረርሽኝ ከዚህ ቀደም ከነበረው በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ግን አልካዱም። በክልሉ ስር በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች፤ የኮሮና ቫይረስ ይኖርባቸዋል ተብለው ከተጠረጠሩ ሰዎች መካከል በበሽታው መያዝ ምጣኔ ከ50 በመቶ በላይ ሆኖ መገኘቱን ይናገራሉ።
ለዚህም በዋና ምክንያትነት የሚጠቅሱት “አላስፈላጊ እና ጥንቃቄ የጎደለው የህዝብ መሰባሰብን” ነው። በክልሉ የሚደረጉ ህዝባዊ እና ፖለቲካዊ ስብሰባዎች፣ ስልጠናዎች፣ የሰርግ ስነ ስርዓቶች፣ የበዓላት አከባበር፣ በእምነት ተቋማት የሚደረጉ መሰባሰቦች፣ በህዝብ መጓጓዣዎች የሚታዩ መጨናነቆች እንዲሁም በመዝናኛ ቦታ ሰዎች በብዛት መገኘታቸው ለወረርሽኙ መስፋፋት አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ይዘርዝራሉ።
የሀዋሳ የኢንዱስትሪ ፓርክን በመሰሉ በርካታ ሰራተኞችን በሚይዙ ቦታዎች ያለው ሁኔታም ቫይረሱ በቀላሉ እንዲሰራጭ ምቹ ሁኔታን መፍጠራቸውን ዶ/ር ማቴ ያነሳሉ። ህብረተሰቡ በሽታው የሚያስከተለውን ጉዳት አቃልሎ መመልከቱ እና ጭርሱን መኖሩኑም አለመቀበሉ ለመስፋፋቱ ሌላ ምክንያት መሆኑን ይጠቅሳሉ። ህብረተሰቡ የኮሮና በሽታ ፖለቲከኞች የሚጠቀሙበት እንጂ በእውን በመሬት ያለ ነው ብሎ የማመን ችግር እንዳለበትም በተጨማሪነት ያክላሉ።
እርሳቸውን ይህን ቢሉም፤ የኮሮና በሽታን ለመቆጣጠር ባለስልጣናት ራሳቸው ያሳዩት ቸልተኝነት ለቫይረሱ ስርጭት ጉልህ ድርሻ ነበረው የሚሉ አስተያየቶች ከክልሉ ነዋሪዎች ይደመጣሉ። ነዋሪዎቹ ለዚህ በምሳሌነት የሚያነሱት በኮሮና ወረርሽኝ ስጋት ምክንያት ተራዝሞ የነበረው የሲዳማ የክልል ምስረታ የአደባባይ የደስታ መግለጫ፣ በባለስልጣናቱ አዘጋጅነት በያዝነው መጋቢት ወር እንዲካሄድ መደረጉ ነው።
ነዋሪዎቹ ከዚህም በተጨማሪ በክልሉ ከተማ የሚገኙ የግልም ሆነ የመንግስት የጤና ተቋማት የሚታየው የጥንቃቄ ጉድለት ለቫይረሱ መስፋፋት የራሱን ሚና ተጫውቷል የሚል እምነት አላቸው። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው የሀዋሳ ነዋሪዎች፤ በከተማይቱ ያሉ የተወሰኑ የግል ሆስፒታሎች የኮሮና ተጠርጣሪዎችን ከመደበኛ ህመምተኞች ጋር በመቀላቀል ህክምና የሚሰጡበት አሰራር “ለበሽታው የሚያጋልጥ ነው” ሲሉ ይተቻሉ።
የሲዳማ ክልል የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ይህ ችግር በጤና ተቋማት ሊከሰት እንደሚችል ይናገራሉ። “የህክምና ተቋማት ለዚህ በሽታ መሰራጨት ድርሻ አይኖራቸውም ብሎ ማንሳት ይከብዳል” ያሉት ዶ/ር ማቴ፤ በጤና ተቋማት ውስጥ አስታማሚዎች፣ ለበሽታው ቅርብ የሆኑ ባለሙያዎች በአንድ ጣራ ስር ስለሚገኙ ለበሽታው ተጋላጭ ያደርጋቸዋል ይላሉ።
ይህንን ስጋት ለመቅረፍ በሀዋሳ ከተማ በሚገኙት እና በክልሉ መንግስት ስር በሚተዳደሩት አዳሬ፣ ሀዋሳ ሪፈራል እንዲሁም ቱላ ሆስፒታሎች የተለያዩ የጥንቃቄ መስፈርቶች እና ጥብቅ ቁጥጥሮች ተግባራዊ መደረግ መጀመራቸውን ያስረዳሉ። ከመስፈርቶቹ መካከል ወደ ሆስፒታሎቹ የሚገቡ አስታማሚዎች ቁጥሮች ወትሮ ከነበረው በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀነስ መደረጉ አንዱ መሆኑን ይገልጻሉ። የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል የማያደርጉም ሆነ ሌሎች የጥንቃቄ መስፈርቶችን የማይከትሉ ተገልጋዮችን እስከ አለማስተናገድ የደረሰ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑንም ያክላሉ።
በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ የምርምር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ዳሬክተር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር አለሙ ታሚሶ ግን ከኮሮና ጋር በተያያዘ አሁንም በመንግስት ጤና ተቋማት ውስጥ ያልተፈቱ ችግሮች እንዳሉ ይናገራሉ። “ሰው እየሞተ ያለው በኮሮና በሽታ ብቻ ሳይሆን ትክክለኛ የሆነ ድጋፍ እያገኘ ባለመሆኑ ነው” ሲሉም የሁኔታውን አሳሳቢነት ይገልጻሉ። የጤና ባለሙያዎች ተገቢውን ክትትል ላለመድረጋቸው በምክንያትነት የሚጠቅሱት ከመንግስት የሚደረግላቸው ክፍያ እና ድጋፍ “በጣም አነስተኛ” መሆኑን ነው።
ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ጥያቄ የቀረበላቸው የክልሉ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር፤ ክልሉ በኮሮና ማዕከል ለሚሰሩ የጤና ባለሙያዎች አቅሙ የፈቀደውን ያህል እያደረገ ነው ይላሉ። “መንግስት ከሚከፍለው ገንዘብም ይሁን ከተለያዩ ማበረታቻዎች በላይ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ያሉ ባለሙያዎች እንዳሉ ይሰማኛል” ብለዋል ዶክተር ማቴ።
የኮሮና በሽታ ሲዳማን ጨምሮ በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች እየተስፋፋ መምጣቱ ያሰጋው፤ የፌደራል የጤና ሚኒስቴር የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል ከዚህ ቀደም ወጥቶ በነበረው መመሪያ ላይ የተዘረዘሩ የክልከላ እርምጃዎች በጥብቅ ተግባራዊ እንዲሆኑ ውሳኔ አስተላልፏል። መመሪያው በየትኛውም ቦታ የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል (ማስክ) ሳይደረግ መንቀሳቀስን ይከለክላል።
በንግድና ሌሎች የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ማስክ ሳያደርጉ መስተናገድም ሆነ አገልግሎት መስጠት ክልክል መሆኑን መመሪያው አስቀምጧል። ማንኛውም ቫይረሱ የተገኘበት ሰው ወደ ማህበረሰቡ እንዳይቀላቀል የሚከለክለው መመሪያው፤ ቫይረሱ ሊተላለፍ በሚያስችል ሁኔታም ንክኪ ማድረግ በህግ እንደሚያቀጣ ደንግጓል።
የሲዳማ ክልል ይህንን መመሪያ ከመጋቢት 20 ጀምሮ በተግባር ላይ መዋል መጀመሩን፤ የሲዳማ ክልል የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ይገልጻሉ። ክልሉ የኮሮና ስርጭትን ለመከላከል የሚረዳውን መመሪያ ተግባራዊ ማድረግ በጀመረበት ዕለት ግን ሀዋሳ ዕውቅ ነዋሪዋን በዚሁ በሽታ በሞት ተነጥቃለች። ከተማይቱ በ54 ዓመታቸው ያረፉትን አቶ ተፈራ ዊላን በነቂስ ወጥታ ለመሰናበት ግን ኮሮናን አልፈራችም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)