የአውሮፓ ህብረት ልዩ መልዕክተኛ በትግራይ ሁኔታ ላይ ለመምከር በድጋሚ ወደ አዲስ አበባ ሊመጡ ነው

የአውሮፓ ህብረት ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት የፊንላንዱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፔካ ሐቪስቶ፤ “በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ በተለይም የትግራይ ቀውስ እና በቀጠናው ባለው አንድምታ ላይ ለመወያየት” ዳግም ወደ አዲስ አበባ እንደሚያቀኑ የአውሮፓ ህብረት አስታወቀ። ሚኒስትሩ ከሁለተኛ ዙር የኢትዮጵያ ጉብኝታቸው በኋላ፤ የተመለከቷቸውን ጉዳዮች የያዘ ሪፖርት በሚቀጥለው ወር ለሚካሔደው የአውሮፓ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ያቀርባሉ ተብሏል።  

ሐቪስቶ የአውሮፓ ህብረት ልዩ መልዕክተኛ ሆነው ባለፈው የካቲት ወር የተሾሙት በህብረቱ የዉጪ ግንኙነት ኃላፊ ጆሴፕ ቦሬል ነው። የህብረቱ የውጭ ግንኙነት ቢሮ ዛሬ ቅዳሜ ባወጣው መግለጫ፤ ሐቪስቶ “ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ተገናኝተው የአውሮፓ ህብረት በትግራይ ባለው ሰብዓዊ ሁኔታ አሁንም ያለውን ስጋት” ያስረዳሉ። 

ዲፕሎማቱ በዚሁ ጉዟቸው “ሁሉም ወገኖች ከግጭት እንዲታቀቡ፣ ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ እና የስደተኞች መብቶች ጥበቃ ህግጋት እንዲያከብሩ እንዲሁም ተፈጽመዋል በተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ገለልተኛ ምርመራ እንዲከናወን እንዲፈቅዱ” ጥሪ እንደሚያቀርቡ በመግለጫው ተመልክቷል።

ሐቪስቶ በኢትዮጵያ ቆይታቸው የሚያነሱት ሌላው ጉዳይ የኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ መውጣት የተመለከተ እንደሆነም መግለጫው ጠቅሷል። ትላንት አርብ ቡድን ሰባት ተብለው የሚጠሩት የካናዳ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ጃፓን፣ ብሪታኒያ እና አሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ እንደሚወጡ ይፋ ማድረጋቸውን በበጎ አንስተው ተመሳሳይ ሀሳብ አንስተው ነበር። 

ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በትላንቱ መግለጫቸው የኤርትራ ወታደሮች “በፍጥነት፣ ያለ ቅድመ ሁኔታ እና ሊረጋገጥ በሚችል መንገድ” መውጣት እንደሚገባቸው ገልጸው ነበር። ሚኒስትሮቹ “ሁከት እንዲቆም እና በትግራይ የሚገኙትን ጨምሮ በሁሉም ኢትዮጵያውያን ተቀባይነት ያለው፤ ወደ ተዓማኒ ምርጫ እና ብሔራዊ ዕርቅ የሚመራ ግልጽ እና አካታች ፖለቲካዊ ሒደት እንዲመሰረት” ጥሪ አቅርበዋል።

ባለፈው የካቲት ወር ወደ አዲስ አበባ የተጓዙት የፊንላንዱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚልን ጨምሮ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ውይይት አድርገው ነበር። ሐቪስቶ በአሁኑ የአዲስ አበባ ቆይታቸው ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት በተጨማሪ ከአፍሪካ ህብረት መሪዎች ጋር ጭምር ይወያያሉ። 

ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በየካቲቱ ጉዟቸው ወደ ካርቱም ተጉዘው ከሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር እንደተነጋገሩት ሁሉ በአሁኑ ጉዟቸውም እግረ መንገዳቸውን ወደ ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ይጓዛሉ። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)