የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ ላይ የሚሰሙ ምስክሮች በግልጽ ችሎት እንዲሆን ወሰነ

በቅድስት ሙላቱ

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ ላይ የቆጠራቸው 146 ምስክሮች በግልጽ ችሎት እንዲሰሙ አዘዘ። ፍርድ ቤቱ ዛሬ ትዕዛዙን የሰጠው በአቃቤ ህግ የቀረበውን “በዝግ ችሎት ያታዩልኝ” አቤቱታ ውድቅ ማድረጉን ተከትሎ ነው።

ከሳሽ ዐቃቤ ህግ በእነ አቶ ጃዋር የክርክር መዝገብ ሊያሰማ ያዘጋጃቸው ምስክሮች፤ “ጥበቃ እንዲያገኙ ስላደግረኩኝ፤ ማንነታቸው በስም ሳይጠቀስ በዝግ ችሎት እና ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው እንዲመሰክሩ” ሲል ከዚህ ቀደም ለችሎቱ አቤቱታ አቅርቦ ነበር። ዐቃቤ ህግ አቤቱታውን ያቀረበው የወንጀል ምስክሮችና ጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጅን በመጥቀስ ነው። 

ይህን አቤቱታ የተቃወሙት የተከሳሽ ጠበቆች የመከላከያ ሀሳባቸውን ጥቅምት 3፤ 2013  ለፍርድ ቤቱ በጽሁፍ አስገብተዋል። ጠበቆቹ በዚሁ መከላከያቸው፤ “ተከሳሾች የሚቀርብባቸውን ምስክሮች የማየት እና የመጠየቅ መብታቸው በህገ መንግስት ተደንግጎ ሳለል፤ ዐቃቤ ህግ ምክንያቱን በውል ባልጠቀሰበት እና በምስክሮቹ ላይ የሚደርስውን አደጋ በዝርዝር ባላስቀመጠበት ሁኔታ የተከሳሾችን የመከላከል መብት ማጣበብ አይገባውም” ሲሉ ተቃውመዋል።  

ጠበቆቹ ከዚህ መከራከሪያቸው በተጨማሪም “ተከሳሾች በህግ ጥላ ስር የሚገኙ ሆኖ ሳለ 146 ምስክሮች ላይ ጫና ሊያደርሱ የሚችሉበት ሁኔታ የለም” ሲሉ አቤቱታው ተቀባይነት እንዳያገኝ ሞግተዋል። የሁለቱንም ወገን ክርክሮች የመረመረው የጸረ ሽብር እና የሕገ መንግስታዊ ጉዳዮች ችሎት፤ በዛሬው ውሎው በአቤቱታው ላይ ብይን ሰጥቷል። 

ችሎቱ የጉዳዩን አመጣጥ ካስረዳ በኋላ፤ በመርህ ደረጃ አንድ የተከሰሰ ሰው ግልጽ በሆነ ችሎት መዳኘት እንዳለበት ህገ መንግስቱ እንደሚደነግግ ገልጿል። ሆኖም ይህ መብት የህዝብን ደህንነት ወይም ብሔራዊ ጸጥታን የሚያናጋ እንዲሁም የዳኝነትን ስርዐት የሚጎዳ ከሆነ ግን በፍርድ ቤት ሊገደብ እንደሚችል ችሎቱ ጠቅሷል። 

ከዚህ በተጨማሪም በወንጀል ጠቋሚዎች፣ ምስክሮች ወይም በቤተሰቦቻቸው ላይ ከባድ ጥቃት ሊደርስ የሚችል ከሆነ ፍርድ ቤቱ ማንነታቸውን ሳይናገር ምስክርነታቸውን የሚሰማበት ሁኔታ እንዳለም ችሎቱ አመልክቷል። ዐቃቤ ህግ ለችሎቱ ያቀረበው አቤቱታ ግን “ለምስክሮች ጥበቃ ስለተደረገ ብቻ፣ በዝግ ችሎት እና ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው እንዲመሰክሩ” በሚል የቀረበ እንጂ ፍርድ ቤቱን በሚያሳምን መልኩ በምስክሮቹ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት በምክንያት እንዲሁም በማስረጃ ዘርዝሮ አለማስረዳቱን ችሎቱ አትቷል። 

ከዚህ ዋነኛ ምክንያት በተጨማሪም አቤቱታው “የተከሳሾችን መብት ያለ በቂ ምክንያት የሚገድብ ሆኖ” ማግኘቱን ችሎቱ ገልጿል። በተጠቀሱት ሁለት ምክንያቶችም ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ህግን አቤቱታ ውድቅ ማድረጉን አስታውቆ የምስክር ማሰማት ሂደቱ በይፋ ወይም በግልጽ እንዲሆን ሲል ወስኗል።

የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ያቀረበው አቤቱታ ውድቅ መደረጉን ተከትሎ ለችሎቱ ተጨማሪ ጥያቄ አቅርቧል። ዐቃቤ ህግ በወንጀል ምስክሮችና ጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጅ የተካተቱ የጥበቃ አማራጮችን ለምስክሮቹ አማልቶ እስኪያቀርብ ድረስ፤ የምስክር የማሰማት ቀጠሮ ይራዘመልኝ ሲል ነበር የጠየቀው። ዐቃቤ ህግ ከጠቀሳቸው የጥበቃ አማራጮች ውስጥ “ትጥቅ መስጠት እና አድራሻ መቀየር” የሚሉት ይገኙበታል።        

የተከሳሽ ጠበቆች በበኩላቸው ዐቃቤ ህግ የጠቀሳችው የጥበቃ አማራጮች “ገና ከዚህ በኋላ የሚሰሩ ሳይሆን ከዚህ በፊት በምስክርነት በመረጣችው ጊዜ መከናወን የነበረበት ነው” በማለት ፍርድ ቤቱ የጊዜ ቀጠሮ ማራዘም እንደማይገባው ጠይቀዋል። ከዚህ ቀደም በነበረ ችሎት የምስክር ማሰማት ሂደቱ መጋቢት 29 እንዲጀመር ቀጠሮ ተይዞ ነበር። 

ለነገ መጋቢት 29 በተያዘው ቀጠሮ የሚሰሙት ምስክሮች ሁሉም አለመሆናቸውን ያነሱት የተከሳሽ ጠበቆች፤ ዐቃቤ ህግ “ ከልቡ ካሳበበት ዛሬ አስፈላጊውን ጥበቃ ሊያደርግ ይችላል” ሲሉ ተከራክረዋል። አንድ የተከሳሽ ጠበቃ “ዐቃቤ ህግ ፍርድ ቤቱ የሚሰጠውን ብይን ለመቀበል እየተቸገረ ነው” ሲሉ ተችተዋል። ሌላ የተከሳሽ ጠበቃ በበኩላቸው፤ ተከሳሾች ለረጅም ጊዜ በእስር በመቆየታቸው ሌላ የጊዜ ቀጠሮ መሰጠቱ ለበለጠ ችግር እንደሚዳርጋቸው ተናግረዋል።  

ችሎቱ ዐቃቤ ህግ በተከሳሽ ጠበቆች ለተሰነዘረበት መከላከያ መልስ እንዲሰጥ ሳይፈቅድ በጉዳዩ ላይ ትዕዛዝ ሰጥቷል። በትዕዛዙም የምስክሮች አሰማም ሂደት ብይን ያገኘው ዛሬ በመሆኑ እና ምናልባትም ዐቃቤ ህግ “በዝግ ችሎት ሊሆን ይችላል” የሚል እምነት ጥሎ የመጣ ስለሚሆን ሌሎች የጥበቃ አማራጮችን ለመተግበር ጊዜ እንደሚያስፈልገው ጠቅሷል። 

በዚህም መሰረት በመጋቢት 29 እና 30 ሊከናወን የነበረው የምስክሮች መስማት ሂደት፤ ከማክሰኞ ሚያዝያ 5 እንዲጀመር ችሎቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል። የምስክሮች መስማት ሂደቱ እስከ ሚያዝያ 14 እንደሚቀጥልም ችሎቱ ገልጿል። 

በዛሬው ችሎት በተከሳሽ ጠበቆች ከቀረቡ ጥያቄዎች መካከል፤ ዐቃቤ ህግ 146 ምስክሮቹን ማን በማን ላይ እንደሚመሰክር እና የትኛውን ጭብጥ እንደሚያስረዱለት በዝርዝር ለፍርድ ቤቱ በፅሁፍ አቅርቦ ግልባጩን ለተከሳሽ ጠበቆች እንዲደርሳቸው እንዲያደርግ የሚል። የጠበቆችን ጥያቄ የተቀበለው ዐቃቤ ህግ፤ የትኞቹ ምስክሮች በየትኛው ጭብጥ ላይ እንደሚመሰክሩ ለይቶ ዝርዝሩን ለማቅረብ ተስማምቷል።

በሌላ በኩል፤ የተከሳሽ ጠበቆች ከዚህ ቀደም ባሉ ችሎቶች ላይ የተጠየቁትን የዋስትና ጥያቄዎች በሚመለከት ፍርድ ቤቱ ብይን ይስጥልን ሲሉ ጠይቀዋል። አስፈላጊ ከሆነም ዋስትና የተጠየቁባቸውን ተከሳሾች በዝርዝር ጽፈን እናስገባለን ብለዋል። ሆኖም ፍርድ ቤቱ የወንጀለኛ መቅጫ ህግን በመጥቀስ “ሁሉም ተከሳሾች የተከሰሱበት ጉዳት ከአንድ በላይ የሆኑ ሰዎች የሞቱበት በመሆኑ የዋስትና መብት አያሰጣቸውም በማለት ጥያቄውን ውድቅ በማድረግ ማረሚያ ቤት እንዲቆዩ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

በዛሬው ችሎት አቶ ጃዋር መሐመድ እና በቀለ ገርባን ጨምሮ በእስር ላይ ያሉ ሁሉም ተከሳሾች በችሎት ተገኝተዋል። ከተከሳሾች ውስጥ አቶ ጉቱ ሙሊሳ እና አቶ ሸምሰዲን ጣሃ ለፍርድ ቤቱ ቅሬታቸውን አሰምተዋል። 

የጤናቸው ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ጉቱ፤ አስፈላጊውን የጤና ክትትል የሚያገኙበት መንገድ እንዲመቻች ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል። አቶ ሸምሰዲን ጣሀ በበኩላቸው በውጪ የሚገኙ ቤተሰቦቻቸውን በስልክ ማግኘት እንዳልቻሉ ተናግረዋል። ማረሚያ ቤቱ “በግል፤ በስማቸው ትዕዛዝ ይምጣ” በማለቱ ምክንያት ለዘጠኝ ወር ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዳልተገናኙም አመልክተዋል። 

ሁለቱ ተከሳሾች ላቀረቡት አቤቱታ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል። ፍርድ ቤቱ ለአቶ ሸምሰዲን ጣሀ ስማቸው በግልፅ እንዲተላለፍ እና በስልክ ከቤሰቦቻቸው ጋር እንዲገናኙ ትዕዛዝ አስተላልፏል። አቶ ጉቱን በተመለከተም ፍርድ ቤቱ ተገቢውን የጤና ክትትል እንዲያገኙ ትዕዛዝ የሰጠ ሲሆን ይኸው በጽህፈት ቤት በኩል እንደሚላክ ጠቅሰዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)