የሶማሌ ክልል በስሩ ባሉ አራት ቀበሌዎች በደረሰ ጥቃት ቁጥራቸው በወል ያልታወቀ ሰዎች መገደላቸውን አስታወቀ

በቅድስት ሙላቱ

በሶማሌ ክልል ስር በሚገኙ አራት ቀበሌዎች ላይ ዛሬ ማክሰኞ በተሰነዘረ ጥቃት ቁጥራቸው በወል ያልታወቁ ሰዎች መገደላቸውን የክልሉ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ገለጸ። ጥቃቱን የሰነዘሩት “የአፋር ክልል ልዩ ኃይል እና አጉጉማ የሚባል ታጣቂ ቡድን ነው” ሲል ቢሮው ወንጅሏል። የአፋር ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ ደረሰ የተባለው ጥቃት “ከእውነት የራቀ ነው” ብሏል። 

የሶማሌ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አሊበደል መሐመድ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደተናገሩት ጥቃቱ የተሰነዘረባቸው አካባቢዎች በክልሉ ሲቲ ዞን ስር በሚገኙት ደዋዲድ፣ ገውረአን፣ ቀላሌ እና ደንለሄ በሚባሉ ቀበሌዎች ላይ ነው። አራቱ ቀበሌዎች ከአፋር ወሰን በግምት ከ10 እስከ 15 ኪሎ ሜትር ገደማ እንደሚርቁ ኃላፊው አስረድተዋል። 

በአራቱም ቀበሌዎች በተመሳሳይ ጊዜ ጥቃት መሰንዘሩን የሚያስረዱት አቶ አሊበደል፤ “ጥቃቱ የተፈጸመው በአፋር ክልል ልዩ ኃይል እንደሆነ ከህብረተሰቡ እና በአካባቢው መዋቅር ስር ካሉት የጸጥታ አካላት ማረጋገጥ ችለናል” ብለዋል። በዛሬው ጥቃት ከአፋር ክልል ልዩ ኃይል በተጨማሪ የክልሉ ሚሊሺያዎች እና በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ “አጉጉማ” የተባሉ ታጣቂዎች ተሳትፈዋል ሲሉ ከስሰዋል። 

ዛሬ መጋቢት 28 በደረሰው ጥቃት “ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ የአካባቢው ነዋሪዎች ህይወታቸውን እንዳጡ” የሶማሌ ክልል መንግስት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። በክልሉ ያሉ አንድ የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጭ እንደገለጹት፤ በዛሬው ጥቃት በትንሹ በ30 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት ደርሷል። ተጎጂዎቹ በአሁኑ ወቅት በቢኪ ከተማ በሚገኝ ሆስፒታል የህክምና ዕርዳታ እየተደረገላቸው እንደሚገኙም ገልጸዋል። 

በሶማሌ ክልል አራት ቀበሌዎች ተፈጸመ ስለተባለው ጥቃት የተጠየቁት የአፋር ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አሊዲኒ አላሳ፤ በክልሉ መንግስት የተሰራጨው መረጃ ውድቅ አድርገዋል። “ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮኻል” ያሉት ኮሚሽነሩ፤ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል አባላት ዛሬም ጭምር በአፋር ክልል ጥቃት ሰንዝረዋል ሲሉ ወንጅለዋል። 

ጥቃቱ የተሰነዘረበት ቦታ ባለፈው አርብ መጋቢት 24 ተመሳሳይ ድርጊት የተፈጸመበት የሀሩቃ ቀበሌ እንደሆነም ተናግረዋል። ኮሚሽነሩ ዛሬ ከጠዋቱ 11 ሰዓት ደረሰ ባሉት በዚህ ጥቃት በርካታ ሰዎች መገደላቸውን እና መጎዳታቸውንም ገልጸዋል። 

በሀሩቃ ቀበሌ ባለፈው አርብ በተፈጸመ ጥቃት በትንሹ 30 ሰዎች መገደላቸውን እና ከ50 በላይ የአካባቢው ነዋሪዎች መቁሰላቸውን የአፋር ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በትላንትው ዕለት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” መግለጹ ይታወሳል። በአካባቢው ተፈጸመ የተባለውን ጥቃት ያስተባበለው የሶማሌ ክልል፤ በዚያኑ ቀን ደአዋዲ እና ቀረፋ በተባሉ ቀበሌዎች በተሰነዘረ ጥቃት ከ25 በላይ አርብቶ አደሮች መገደላቸውን እና ከ30 በላይ የሚሆኑት ደግሞ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ዛሬ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።

በሁለቱም ክልሎች እየተስተዋሉ ግጭቶች “ከዚህ ቀደምም የነበሩ ናቸው” የሚሉት የሶማሌ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አሊበደል፤ “የአሁኑን ለየት ያደረገው ግን በተደጋጋሚ መሆኑ ነው” ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የሶማሌ ክልል መንግስት በዛሬው መግለጫው፤ “ጉዳዩ ወደለየለት ግጭት” ከማምራቱ በፊት የአፋር ክልልም ሆነ የፌዴራል መንግስቱ የመፍትሔ አካል እንዲሆኑ በጥብቅ አሳስቧል። 

በሶማሌ እና አፋር ክልሎች መካከል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን ግጭት እና መካረር በተመለከተ ከፌደራል መንግስት እስካሁን በይፋ የተሰጠ መግለጫ የለም። የሶማሌ ክልል ግን ግጭቱ በዚህ ሁኔታ የሚቀጥል ከሆነ፤ “በክልሉ የሚደርሰውን ሞትና መፈናቀል ለመከላከል ሲባል ተገቢውን እርምጃ ሊወስድ እንደሚገደድ” በዛሬው መግለጫው አስጠንቅቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)