በእነ ስብሃት ነጋ ላይ ሊሰማ የነበረው የቅድመ ምርመራ ምስክርነት ለጊዜው ታገደ

በቅድስት ሙላቱ

የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በእነ ስብሃት ነጋ ላይ በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሊያሰማው የነበረው የቅድመ ምርመራ ምስክርነት ለጊዜው ታገደ። ምስክርነቱ የታገደው የተከሳሽ ጠበቆች በምስክር አሰማም ሂደቱ ላይ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ በማለታቸው ነው።

ዐቃቤ ህግ አቶ ስብሃት ነጋን ጨምሮ የ42 ተጠርጣሪዎችን የጊዜ ቀጠሮ እየተመለከተ ላለው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ አራዳ ምድብ ችሎት ከዚህ ቀደም ባቀረበው አቤቱታ፤ የቅድመ ምርመራ የምስክርነት ሂደቱ በዝግ ችሎት እና በስውር እንዲሆን ጥያቄ አቅርቦ ነበር። የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች ይህንን አቤቱታ ተቃውመው ለችሎት አቤት ቢሉም መቃወሚያቸው ውድቅ ተደርጓል። 

ጠበቆቹ ጉዳዩን ወደ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመውሰድ ይግባኝ መጠየቃቸውን ተከትሎ፤ የጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ የቅድመ ምርመራ የምስክር መስማት ሂደቱ ታግዶ እንዲቆይ በዛሬው ውሎው ወስኗል። ችሎቱ “የይግባኝ ክርክሩ መልስ እስኪያገኝ ድረስ መዝገቡ ተዘግቶ ይቆያል” ሲል በዛሬው ውሎው ትዕዛዝ ሰጥቷል። 

ዛሬ መጋቢት 29 በነበረው ችሎት፤ አቶ ስብሃት ነጋን ጨምሮ 39 ተጠርጣሪዎች በአካል ተገኝተው ተከታትለዋል። በዛሬው ችሎት ሰሎሞን ኪዳኔ እና ብርሃነ ጸጋዬ በህመም ምክንያት አልተገኙም። 

በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የነበረው የዕለቱ የችሎት ውሎ ካበቃ በኋላ፤ ዐቃቤ ህግ የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች ይግባኝ ላሉበት ፍርድ ቤት ጥያቄ አቅርቧል። ዐቃቤ ህግ በቢሮ በኩል ያቀረበው ጥያቄ፤ የይግባኝ የጊዜ ቀጠሮው በአጠረ ጊዜ እንዲደረግ  የሚጠይቅ ነው።    

ጥያቄውን የተመለከተው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት፤ የጊዜ ቀጠሮው ከአንድ ሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ሊሆን እንደማይችል ምላሽ ሰጥቷል። ፍርድ ቤቱ ለውሳኔው በምክንያትነት የጠቀሰው በችሎቱ ከሚሰየሙት ዳኞች አንደኛው መታመማቸው እና ሌሎቹ ደግሞ በከፍተኛ የስራ ጫና ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን ነው። በመጨረሻም ፍርድ ቤቱ የይግባኝ ክርክሩን ለሚያዝያ 6፤ 2013 ለመስማት ቀጥሯል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)