ኢዜማ ለአዲስ አበባ ከተማ ያዘጋጀውን የምርጫ ማኒፌስቶ ይፋ አደረገ

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ ለአዲስ አበባ ከተማ ያዘጋጀውን የምርጫ ማኒፌስቶ ዛሬ ረቡዕ ይፋ አድርጓል። “የቃል ኪዳን ሰነድ” ስያሜ በተሰጠው በዚህ ማኒፌስቶ፤ ፓርቲው ሊያሳካቸው ያቀዳቸው 138 ቁልፍ ግቦች ተካትተውበታል። 

በአስራ አምስት ክፍሎች ተከፋፍሎ በተዘጋጀው ሰነድ፤ የአዲስ አበባ ሰላምና ደህንነት የማረጋገጥ፣ የመኖሪያ ቤቶች እጥረት መቅረፍ፣ ዘመናዊ የመሬት አስተዳደር መዘርጋት፣ የከተማዋን የትራንስፖርት ችግር እና በእንቅስቃሴ ላይ የሚታየውን መጨናነቅ መቅረፍን የመሳሰሉ ጉዳዮች ተዳስሰውበታል። ሰነዱ ፓርቲው በቀጣዩ ምርጫ ቢመረጥ እነዚህን እና ሌሎች የከተማይቱ ችግሮችን ለመፍታት የያዛቸውን ዕቅዶች እና ዋና ዋና ዓላማዎችንም ያስቃኛል። 

“አዲስ አበባ በተለያዩ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ችግሮች በታሰረችበት በዚህ አሳሳቢ ወቅት ላይ፤ ከምንም በላይ የከተማዋን ነዋሪ ሕዝብ ለማሻሻልና በተጠና መዋቅራዊ ለውጥ በታገዘ ብቁ አስተዳደር እና የተለያዩ ስር ነቀል የአገልግሎትና የመሰረተ ልማት ማስፋፋት ስራዎች ለማከናወን ቀዳሚ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ኢዜማ ጠንቅቆ ያምናል” ሲል ፓርቲው በሰነዱ የመግቢያ ክፍል ላይ አስቀምጧል።

ፓርቲው ሰነዱን ይፋ ማድረጉን ለማስተዋወቅ ባዘጋጀው መርሃ ግብር ላይ የኢዜማ መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና ፓርቲውን በመወከል ለአዲስ አበባ ምክር ቤት የሚወዳደሩት አቶ ክብር ገና ንግግር አድርገዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)