አዲሱን ክልል መፈተን የጀመሩት የወሰን እና አስተዳደር ጥያቄዎች

በቅድስት ሙላቱ

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግስት ስልጣኑን ከተረከበ ከሶስት ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ ተደጋግመው ከሚታዩ ፖለቲካዊ ትኩሳቶች መካከል፤ የክልሎች ወሰንና የማንነት ጉዳዮች፣ የመሬት ይገባኛል ጥያቄ እና “በዚህኛውም አሊያም በዚያኛው ክልል መተዳደር እንፈልጋለን” የሚሉ ተደጋጋሚ ድምጾች ይገኙበታል። እኒህን መሰል ጥያቄዎች ከተቋቋመ 10 ወራትን ብቻ ወዳስቆጠረው ወደ አዲሱ የሲዳማ ክልልም መሻገር ጀምረዋል። 

ክልሉ በያዝነው በመጋቢት ወር ብቻ በሶስት ቦታዎች ላይ ከወሰን ጉዳዮች ጋር በተገናኘ ችግሮች ገጥመውታል። ሁለቱ ጉዳዮች የተያያዙት በኦሮሚያ ክልል ከሚገኘው ምዕራብ አርሲ ዞን ሲሆን አንዱ ደግሞ በደቡብ ክልል ከሚገኘው የወላይታ ዞን ጋር ነው። ከሁነቶቹ ሁሉ ከበድ ያለውና በጊዜ ረገድም ቀረብ ያለው፤ ባለፈው ሳምንት አርብ መጋቢት 24፤ 2013 በክልሉ ስር በምትገኘው ወንዶ ገነት ወረዳ የተከሰተው ነው። 

በዕለቱ በወረዳው ስር ካሉ ቀበሌዎች አንዷ በሆነቸው ኤዶ ያሉ የታጠቁ ኃይሎች የመከላከያ ሰራዊት ላይ ተኩስ እስከ መክፈት ድረስ የተጓዘ ጥቃት መፈጸማቸውን የክልሉ ባለስልጣናት ይናገራሉ። የመከላከያ ሰራዊቱ በአካባቢው የተሰማራው ከሁለት ዓመት በፊት በስፍራው የተፈጠረውን ግጭት ለማረጋጋት በሚል ሲሆን እስካለፈው ሳምንትም በኤዶ ቀበሌ ቆይቷል።

ኤዶ ቀበሌ በኦሮሚያ ምዕራብ አርሲ ዞን እና በሲዳማ ክልል ድንበር ላይ ከሚገኙ 13 ቀበሌዎች አንዱ ነው። የጉጂ ማህበረሰብ ተወላጆች የሚኖሩባቸው እነዚህ ቀበሌዎች በምዕራብ አርሲ አሊያም በሲዳማ ስር ይተዳደሩ የሚለው ጉዳይ ሲያወዛግብ ቆይቶ ምላሽ ያገኘው በ2001 ዓ.ም. ነበር። በወቅቱ በቀበሌዎቹ ላይ በተካሄደ (ህዝበ ውሳኔ) ኤዶን ጨምሮ ዘጠኝ ቀበሌዎች በሲዳማ ስር እንዲሆኑ ሲወሰን ቀሪዎቹ አራት ቀበሌዎች በምዕራብ አርሲ ዞን ስር እንዲተዳደሩ ተደርጓል። 

ይህ ህዝበ ውሳኔ በአካባቢው ያለውን ችግር ይፈታል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት የነበረ ቢሆንም ከ10 ዓመት በኋላ ግን ግጭቱ እንደገና መልሶ አገርሽቷል። በኤዶ ቀበሌ የሚኖሩ የጉጂ ማህበረሰብ አባላት “በኦሮሚያ ክልል ስር መተዳደር እንፈልጋለን” የሚለውን ጥያቄ እንደገና ማንሳታቸው ለግጭቱ መንስኤ እንደነበር ይነገራል። 

የሰው ህይወት የተቀጠፈበትና በርካታ ቤቶች የተቃጠሉበት ይህን ግጭት ለማረጋጋት በስፍራው የተሰማራው የመከላከያ ሰራዊት፤ ላለፉት ሁለት ዓመታትም የአካባቢውን ጸጥታ በማስጠበቅ ስራ ላይ ተሰማርቶ ቆይቷል። በቀበሌው የነበረው ሰራዊት ለሌላ ግዳጅ አካባቢውን መልቀቁን ተከትሎ፤ ያንን የሚተካ የጸጥታ ኃይል ባለፈው ሳምንት አርብ ወደ ስፍራው ሲንቀሳቀስ ነበር ታጣቂዎች ተኩስ መክፈታቸው የተነገረው።

የሲዳማ ክልል የጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቴዎስ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደተናገሩት ታጣቂዎቹ ጥቃቱን ያደረሱት ሰራዊቱ ወደቦታው እንዳይገባ  ነው። የመከላከያ ሰራዊት አባላት ጉዳዩን በትዕግስት ለማረጋጋት መሞከራቸውን የሚገልጹት አቶ አለማየሁ “ተኩሱ እየበረታ ሲመጣ ሠራዊቱ በወሰደው የመከላከል እርምጃ አራት ሰዎች ቆስለዋል” ብለዋል።

ታጣቂዎቹን “የተደራጁ ወጣቶች” ሲሉ የገለጿቸው ኃላፊው፤ ተቀያሪ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ወደ አካባቢው እንዳይገቡ ለማስተጓጎል የሞከሩት “በቦምብ ውርወራ ጭምር ነው” ይላሉ። ታጣቂዎቹን የተደራጁበት ሁኔታ ከገመገሙ በኋላም ከእንቅስቃሴያቸው ጀርባ “ኦነግ ሸኔ እጁን አስገብቷል” የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል። “ከዚህ ቀደምም ስምንት የሚሆኑ የኦነግ ሸኔ አባላቶችን ከነትጥቃቸው ይዘናል” ሲሉም የአማጺ ቡድኑ በአካባቢው መንቀሳቀስ አዲስ ነገር እንዳልሆነ ያስረዳሉ። 

በአካባቢው ግጭት መቀስቀሱን ተከትሎ የሲዳማ ልዩ ኃይል አባላት በቦታው ላይ ተሰማርተው እንደነበር ከአካባቢው የወጡ መረጃዎች ቢያመለክቱም፤ የክልሉ የጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ግን ይህን አስተባብለዋል። የሲዳማ ልዩ ኃይል በጉዳዩ ላይ አለመሳተፉን የሚናገሩት ኃላፊው፤ ይህ የሆነበት ምክንያትን እንደሚከተለው አብራርተዋል። 

“በኤዶ ቀበሌ ውስጥ የሚኖረው የጉጂ ማህበረሰብ ወደ ኦሮሚያ መካተት የመፈለግ አስተሳሰብ ስላለው፤ ልዩ ኃይሉ ወደቦታው ከገባ ጸጥታን ለማስከበር ነው ብሎ ያለማሰብ ሁኔታዎች ሊያጋጥሙ ስለሚችሉ ነው” በማለት ምክንያቱን የሚያስረዱት ኃላፊው፤ “መከላከያ ላይ የተደረገው ትንኮሳ ልዩ ኃይል ላይ ቢሆን ኖሮ ወደ ትልቅ ዕልቂት ሊገባ ይችል ነበር” ሲሉ ሁኔታው ከቁጥጥር ውጪ ሊሆን ይችል እንደነበር ይጠቁማሉ። 

በአካባቢው የሚስተዋለውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት “የህዝብ ለህዝብ ውይይት መደረግ እንዳለበት ተወስኗል” ያሉት አቶ አለማየሁ፤ ውይይቱ በምዕራብ አርሲ ዞን ጸጥታ ኃላፊ እና በሲዳማ ክልል ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ የሚመራ ይሆናል ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪም በአካባቢው የተደራጁ ታጣቂዎችን ትጥቅ የማስፈታት ስራዎች ከመከላከያ ሰራዊት ጋር በመሆን እየተሰሩ እንደሆነ አክለዋል። 

ጉዳዩን በተመለከተ የተጠየቁት የምዕራብ አርሲ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አበራ ቡኖ በአካባቢው የነበረውን ግጭት ለማረጋጋት ከሲዳማ ክልል ጋር በትብብር መስራታቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። “የእኛም አመራሮች ወደ ቦታው ሄደው ሁኔታውን በማስረዳት ህዝቡ እንዲረጋጋ አስረድተናል” ብለዋል።   

የሲዳማ ክልል ከምዕራብ አርሲ ጋር በሚያዋስነው ኤዶ ቀበሌ ላይ የነበረውን ግጭት በዚህ መልኩ ለመፍታት ጥረት ቢያደርግም፤ ግጭቱ ከመነሳቱ ከቀናት በፊት በሌላ አዋሳኝ ቦታ ላይ የተቀሰቀሰን ችግር በመፍታት ተጠምዶ ነበር። የችግሩ መነሻ በክልሉ ስር ባለው ብላቴ ዙሪያ ወረዳ የባሌላ ከተማ አስተዳዳሪ ከስልጣን መነሳት ነበር። 

“አስተዳዳሪው ከስልጣናቸው የተነሱት በብላቴ ዙሪያ ወረዳ ስር የሚገኙ አራት ቀበሌዎች ለኦሮሚያ ክልል ተላልፈው እንዲሰጡ ባለመስማማታቸው ነው” የሚል መረጃ በመሰራጨቱ በአካባቢው ውጥረት ነግሶ እንዲቆይ ምክንያት ሆኗል። ይህም በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ “መሬታችንን ሊሸጡት ነው” የሚል ጥርጣሬ ማሳደሩን አንድ የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጭ ያስረዳሉ።

በሲዳማ ስር ባለው ብላቴ ዙሪያ ወረዳ እና በምዕራብ አርሲ ዞን ባለው ሲራሮ ወረዳ ነዋሪዎች መካከል “በመሬት ይገባኛል” ጥያቄዎች የዛሬ አራት ዓመት በተቀሰቀሰ ግጭት በሁለቱም ወገኖች 80 የሚሆኑ አርሶ አደሮች መገደላቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። የብላቴ ዙሪያ ወረዳ አስተዳዳሪ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ የተደረገው “ለግጭት የሚያነሳሱ ድርጊቶችን በመፈጸማቸው ነው” የሚሉት የሲዳማ ክልል የጸጥታ ቢሮ ኃላፊ፤ በአካባቢው የሚናፈሰው መረጃ “ሀሰት ነው” ሲሉ አስተባብለዋል።  

የብላቴ ዙሪያ ወረዳ አስተዳዳሪ “ ‘አራት ቀበሌዎች ወደ ኦሮሚያ ይመለስ ተብሎ፤ እኔ አልፈርምም ስላልኩ ከኃላፊነቴ ተነሳሁ” በማለት ህዝቡን አነሳስተዋል” የሚሉት ኃላፊው፤ በዚህም ምክንያት ከኃላፊነታቸው ተነስተው በቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጉን አስረድተዋል። “አስተዳዳሪው ብቻ ሳይሆኑ ግጭት እንዲነሳ የሚያደርጉ የመሳሪያ አዘዋዋሪዎችን ጨምሮ 13 ተባባሪ አካላትን አስረናል” ሲሉ ኃላፊው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

የጸጥታ ቢሮ ኃላፊው፤ የሲዳማ ክልል የአስተዳዳሪው አይነት ግለሰባዊ ችግሮች ወደ አካባቢያዊ ግጭቶች እንዳያድጉ በፍጥነት እንደሚቆጣጠርም ሌላ ማሳያ ጠቅሰዋል። በዚሁ ወር አጋማሽ ሲዳማ ክልልን ከወላይታ ዞን በሚያዋስነው የአባያ ሀይቅ ላይ በአሳ አጥማጆች መካከል የተነሳ ግጭት በአዋሳኝ ቦታዎች ላይ ወደሚኖሩ ነዋሪዎች በማዛመት የብሔር ግጭት ለማስነሳት ሙከራ ተደርጎ ነበር ይላሉ። ሆኖም ክልሉ ወዲያውኑ የማረጋጋት ስራ በመስራቱ ሙከራው መክሸፉን ያስረዳሉ። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)