በቅድስት ሙላቱ
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በእነ አቶ ስብሀት ነጋ ላይ የተቆጠሩ የቅድመ ምርመራ ምስክሮች አሰማም ሂደት ላይ የቀረበውን ክርክር መርምሮ ብይን ለመስጠት ለሚያዝያ 12 ቀጠሮ ሰጠ። የከፍተኛው ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ይግባኝ ሰሚ ችሎት ቀጠሮውን የሰጠው፤ የተጠርጣሪ ጠበቆችን እና የዐቃቤ ህግን ክርክር በዛሬው ውሎው ካደመጠ በኋላ ነው።
ችሎቱ ዛሬ ተሰይሞ የነበረው የዐቃቤ ህግ የቅድመ ምርመራ ምስክሮች በዝግ ችሎት ይሰሙ ወይስ በግልጽ ችሎት የሚለውን ጉዳይ ላይ የቀረበለትን ይግባኝ ለመመልከት ነበር። አቶ ስብሃትን ጨምሮ 42 ተጠርጣሪዎችን የወከሉ ጠበቆች ለችሎቱ ይግባኝ ያሉት፤ የምስክሮች አሰማም ሂደት በዝግ ችሎት እንዲሆን በስር ፍርድ ቤት ውሳኔ መተላለፉን ተከትሎ ነው።
በዛሬው የችሎት ውሎ፤ የቅድመ ምርመራ ምስክሮች ማሰማት ሂደቱ “በከፊል ዝግ” እንዲሆን በዐቃቤ ህግ በኩል ጥያቄ መቅረቡን ከተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች አንዱ የሆኑት አቶ ታደለ ገብረመድህን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። ዐቃቤ ህግ ይህ ሂደት የሚከናወንባቸው መንገዶችን ሲያብራራ፤ አንዳንድ ጉዳዮች በዝግ ችሎት እንዲታዩ፣ ከፊሎቹ ምስክሮች ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው እንዲመሰክሩ እና አንዳንድ ጉዳዮች ደግሞ በሚዲያዎች እንዳይዘግቡ የሚሉ አገላለጾችን መጠቀሙን ጠበቃው ተናግረዋል።

ይህ የሚደረገው “የምስክሮች ደህንነት ለመጠበቅ” መሆኑን የጠቀሰው ዐቃቤ ህግ፤ ለዚህም በአስረጂነት “የወንጀል ምስክሮች እና ጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጅ”ን መጥቀሱን ጠበቃው አስረድተዋል። የዐቃቤ ህግን ክርክር ያደመጡት ጠበቆች፤ “ዐቃቤ ህግ ጉዳዮችን ዘርዝሮ ባላስቀመጠበት ሁኔታ በከፊል ዝግ ይሁን ብሎ መከራከር የለበትም” ሲሉ ተቃውመዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ጠበቆች “ምስክሮች በግልፅ ችሎት መሰማታቸው ህገ መንግስታዊ መብታችን ነው” በማለት መቃወማቸውን አቶ ታደለ አብራርተዋል። የዐቃቤ ህግ መከራከሪያ ከሕገ መንግስቱ እንዲሁም ኢትዮጵያ ከፈረመቻቸው አለም አቀፍ ህጎች አንፃር ተቀባይነት የለውም የሚሉት ጠበቃው፤ “የተጠቀሰውን አዋጅ አያሟላም የሚል መከራከሪያ ነጥብ አቅርበናል” ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው ይግባኝ ሰሚ ችሎቱ፤ በጉዳዩ ላይ ብይን ለመስጠት ለሚቀጥለው ሳምንት ማክሰኞ ሚያዝያ 12 ቀጠሮ በመስጠት የዛሬ የችሎት ውሎውን አጠናቅቋል። በዛሬው የችሎት ውሎ ተጠርጣሪዎቹ በአካል ያልተገኙ ቢሆንም በጠበቆቻቸው ተወክለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)