የአውሮፓ ህብረት የቀውስ አስተዳደር ኮሚሽነር ያኔዝ ሌናርቺች፤ ነገ ማክሰኞ በአዲስ አበባ ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር እንደሚወያዩ አስታወቁ። የውይይታቸው ዋነኛ ትኩረት በትግራይ ግጭት ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያገኙበትን ሁኔታ ማረጋገጥ እንደሆነ ገልጸዋል።
ነገ አዲስ አበባ የሚገቡት ሌናርቺች ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ለመነጋገር ቀጠሮ ይዘዋል። “በትግራይ የተቀሰቀሰው ግጭት ቀድሞም በኢትዮጵያ አስቸጋሪ የነበረውን ሁኔታ አባብሶታል” የሚሉት ኮሚሽነሩ፤ “ምግብ፣ የደህንነት ጥበቃ፣ ጤና እና መጠለያን ጨምሮ ሰብዓዊ ፍላጎቶች እየጨመሩ ነው” ሲሉ ያለውን አሳሳቢ ሁኔታ ባወጡት መግለጫ ላይ አንስተዋል።
“በበርካታ የአገሪቱ ክፍሎች ሁከት እየጨመረ ነው። በትግራይ ያለው ሁኔታ ጥቂት መሻሻል ቢያሳይም አሁንም የከፋ ነው። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ዕርዳታ ይፈልጋሉ” ያሉት ሌናርቺች፤ በተለይ በትግራይ ዕርዳታ ለሚሹ ሰዎች ድጋፍ የሚደርስበትን ሁኔታ ማመቻቸት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።
ኮሚሽነሩ በዛሬው መግለጫቸው፤ የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ እጅግ ተጋላጭ ለሆኑ ሰዎች የሚውል ከ53 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ተጨማሪ ዕርዳታ ማጽደቁንም አስታውቀዋል። ገንዘቡ በግጭት እና የከባቢ አየር ለውጥ ለችግር ለተጋለጡ ለተፈናቀሉ እና የተፈናቀሉትን ላስጠለሉ ማህበረሰቦች የሚውል ነው።
የአውሮፓ ህብረት ባለፈው ዓመት ብቻ ለኢትዮጵያ ለሰብዓዊ ድጋፍ የሚውል 63 ሚሊዮን ዮሮ ገንዘብ መስጠቱ ይታወሳል። ህብረቱ ለኢትዮጵያ ተጨማሪ ድጋፎችን መስጠቱን ቢቀጥልም በተለይ በትግራይ ክልል ያለው የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ እንደሚያሳስበው በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል።
የአውሮፓ ህብረት የቀውስ አስተዳደር ኮሚሽነሩ በዛሬው መግለጫቸውም ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ህግጋት እንዲከበሩ አሳስበዋል። “የሰብዓዊ ዕርዳታ ሰራተኞች ደህንነት በዓለም አቀፍ ህግጋት መሰረት ሊረጋገጥ ይገባል” ያሉት ኮሚሽነሩ፤ የሰላማዊ ሰዎች ደህንነት እንዲጠበቅ እና በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት የፈጸሙ በአፋጣኝ ለፍትህ እንዲቀርቡ ጠይቀዋል።
ስሎቬንያዊው ዲፕሎማት ሌናርቺች ወደ ኢትዮጵያ ሲያመሩ የአሁኑ የመጀመሪያቸው አይደለም። በመስከረም 2013 ዓ.ም ከአውሮፓ ህብረት የውጪ ግንኙነት ኃላፊ ጆሴፕ ቦሬል ጋር ወደ አዲስ አበባ ተጉዘው ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና ከፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ተወያይተው ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)