የግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሽኩሪ “የታላቁ የህዳሴ ግድብ ድርድር የደረሰበትን ደረጃ ለማስረዳት” ያለመ ነው የተባለለትን፤ በስድስት የአፍሪካ አገሮች የሚያደርጉትን ጉብኝት ዛሬ ጀመሩ። ሳሜህ ሽኩሪ ከሚጎበኟቸው አገራት መካከል ድርድሩ በቀጥታ የሚመለከታቸው ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ደቡብ አፍሪካ ይገኙበታል።
የግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አሕመድ ሐፌዝ የሽኩሪ ጉዞ “ድርድሩ ያለበትን ትክክለኛ ደረጃ ለአፍሪካ አገሮች ለማስረዳት እና ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ሳይጀመር አስገዳጅ ህጋዊ ስምምነት ላይ የሚደረስበትን መንገድ ለመደገፍ” ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።
ሽኩሪ የጉዟቸው የመጀመሪያ መዳረሻ ያደረጉት፤ የኢትዮጵያን ጎረቤት እና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታ ጥበቃው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል የሆነችውን ኬንያን ነው። ሽኩሪ ዛሬ ናይሮቢ ሲደርሱ የኬንያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስተዳደር ዋና ጸሀፊ አባቡ ናምዋምባ ተቀብለዋቸዋል። ናምዋምባ እንዳሉት “ሽኩሪ የፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አልሲሲን ልዩ መልዕክት ለኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ያደርሳሉ።”
የግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በአሁኑ ጉዟቸው ከኬንያ በተጨማሪ የጸጥታው ምክር ቤት ሌላኛዋ ተለዋጭ አባል ወደ ሆነችው ቱኒዝያም ያቀናሉ። በግብጽ መዲና ካይሮ ባለፈው ሳምንት ከፕሬዝዳንት አልሲሲ ጋር የተወያዩት የቱኒዝያው ፕሬዝዳንት፤ አገራቸው በህዳሴው ግድብ ውዝግብ የግብጽን አቋም እንደምትደግፍ በይፋ ተናግረው ነበር።
ሽኩሪ ወደ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ደቡብ አፍሪካ የሚያደርጉት ጉዞም ሀገራቱ በግድቡ ድርድር ላይ ካላቸው ሚና በመነሳት ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ሆኗል። ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ጉዳይ ላይ ለመወያየት ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙት በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎዋ ኪንሻሳ ነበር። የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ትሺሴኬዲ የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀ-መንበር ናቸው።
ሶስቱ ዋነኞቹ የአባይ ተፋሰስ ሀገራት “አንድ ቀን ተኩል” ከፈጀ የኪንሻሳ ውይይት በኋላ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ባዘጋጀችው ባለ ዘጠኝ ነጥብ መግለጫ እንኳ ሳይስማሙ ተለያይተዋል። አገሮቹ በመጨረሻ ይፋ ያደረጉት ጠቅለል ያሉ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ባለ ሶስት ነጥቦች መግለጫ ነበር።
ኢትዮጵያ ድርድሩ በአፍሪካ ህብረት በኩል እንዲቀጥል ጽኑ ፍላጎት አላት። የኢትዮጵያ የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ስለሺ በቀለ ከኪንሻሳ መልስ በሰጡት መግለጫ፤ ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ትሺሴኬዲ “የመሪነት ሚናቸው ባልተሸረሸረ መልኩ” ድርድሩን እንዲመሩ የማድረግ ፍላጎት እንዳለ ተናግረው ነበር።
“በቀጣይ የሚከተለው መሪው በሚሰጡት አቅጣጫ መሰረት ይሆናል። በውይይታችን ወቅት፤ በመግለጫውም ተጽፎ ቀርቦ የነበረው አንዱ ጉዳይ እና መጽደቅ ያልቻለው፤ ከሚያዝያ 12 ጀምሮ ኪንሻሳ ተመልሰን ድርድሩን እንድንቀጥል የሚል ሐሳብ የያዘ ነበር” ሲሉ ዶ/ር ስለሺ በውይይቱ ስለተነሳው ሀሳብ አስረድተዋል።
ሶስቱ ሀገራት በኪንሻሳው ውይይት ያልተስማሙበት ሌላኛው ጉዳይ፤ አሁን በታዛቢነት ድርድሩን የሚካፈሉት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የአውሮፓ ህብረት እና አሜሪካ በድርድሩ በቀጥታ እንዲሳተፉ የቀረበው ሀሳብ ነው። ሶስቱ አካላት በድርድሩ “ከአፍሪካ ህብረት እኩል ሚና እንዲኖራቸው” ግብጽ እና ሱዳን ይፈልጋሉ።
የኪንሻሳው “ድርድር ውጤታማ አልሆነም” የሚል አቋም ያላት ሱዳን፤ የሶስቱ አገሮች ጠቅላይ ሚኒስትሮች ተገናኝተው እንዲወያዩ ባለፈው ሳምንት ጥያቄ አቅርባ ነበር። ከኢትዮጵያ እና ግብጽ በኩል ለጥያቄው እስካሁን በይፋ የተሰጠ ምላሽ የለም።
የህዳሴው ግድብ ድርድር ዳግም በተጨናገፈበት በዚህ ወቅት የግብጹ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ግን የፕሬዝዳንታቸውን መልዕክት በመያዝ ሀገራትን ማዳረስ ጀምረዋል። ሚኒስትሩ ከናይሮቢ ቆይታቸው በኋላ ምሽቱን ኮሞሮስ ገብተዋል። ሽኩሪ በዚህ ጉዟቸው ወደ ሴኔጋልም ጎራ ይላሉ። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)