በእነ ስብሀት ነጋ መዝገብ የቅድመ ምርመራ የምስክሮች አሰማም ሂደትን በተመለከተ በስር ፍርድ ቤት የተሰጠ ብይን ውድቅ ተደረገ

በቅድስት ሙላቱ   

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በእነ ስብሀት ነጋ መዝገብ የቅድመ ምርመራ የምስክሮች አሰማም ሂደትን በተመለከተ፤ የስር ፍርድ ቤት የሰጠውን ብይን ውድቅ አደረገ። ፍርድ ቤቱ ውድቅ ያደረገው የቅድመ ምርመራ የምስክሮች አሰማም ሂደት በዝግ ችሎት እንዲሆን በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የተላለፈውን ብይን ነው።

የስር ፍርድ ቤትን ብይን በዛሬው ውሎው የሻረው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አንደኛ ይግባኝ ሰሚ ችሎት ነው። ችሎቱ የዛሬውን ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት፤ የቅድመ ምርመራ ምስክሮች አሰማም ሂደትን በተመለከተ በተጠርጣሪ ጠበቆች የቀረበውን ይግባኝ ተቀብሎ የመረመረ ሲሆን ከዐቃቤ ህግ ጋር ያለውን ክርክርም አድምጧል። 

ዐቃቤ ህግ ባለፈው ሳምንት በነበረ የችሎት ውሎ፤ የቅድመ ምርመራ ምስክሮቹን ደህንነት ለማስጠበቅ ሲባል የምስክር ማሰማት ሂደቱ “በከፊል ዝግ በሆነ ችሎት” እንዲሆን ጠይቆ ነበር። አቶ ስብሃትን ጨምሮ 42 ተጠርጣሪዎችን የወከሉ ጠበቆች ግን ጉዳዩ ከህገ መንግስቱ እና ኢትዮጵያ ከፈረመቻቸው አለም አቀፍ ህጎች አንፃር ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም ሲሉ ተከራክረዋል። ጠበቆቹ የምስክሮች ስም እና አድራሻ በግልጽ እንዲነገርም ጠይቀዋል።

ፎቶዎች፦ ትግራይ ሚዲያ ሀውስ

ጉዳዩን ሲመለከት የነበረው ይግባኝ ሰሚ ችሎትም በሁለቱ ወገኖች የቀረቡትን መከራከሪያዎች መርምሮ ብይን ለመስጠት ለዛሬ ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር። ፍርድ ቤቱ በዛሬው የችሎት ውሎውም ከዚህ በፊት በስር ፍርድ ቤት የተሰጠውን ብይን ውድቅ በማድረግ ጉዳዩ እንደገና ወደ ፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ተመልሶ ክርክር እንዲደረግበት ወስኗል። የስር ፍርድ ቤት ሁለቱንም ወገኖች አከራክሮ በጉዳዩ ላይ ተገቢውን ውሳኔ እንዲሰጥበትም ፍርድ ቤቱ አዝዟል።

የከፍተኛው ፍርድ ቤት ከዚህ በተጨማሪም  በዚሁ ጉዳይ ላይ የይግባኝ መብትን በተመለከተ ዐቃቤ ህግ ቀደም ሲል አቅርቦት የነበረውን ተቃውሞ ተመልክቷል። ዐቃቤ ህግ የቅድመ ምርመራ የምስክር አሰማም የፍርድ ቤት ክርክሩ “ያላለቀ በመሆኑ በከፍተኛው ፍርድ ይግባኝ ሊጠየቅበት አይገባም ሲል ነበር ተቃውሞውን ያቀረበው። 

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሰጠውን አስገዳጅ የህግ ትርጓሜ የጠቀሰው የይግባኝ ሰሚ ችሎቱ ግን የዐቃቤ ህግን ተቃውሞ ሳይቀበለው ቀርቷል። ችሎቱ በጉዳዩ ላይ ይግባኝ መባሉ ትክክል ነው ሲል በዛሬው ውሎው ወስኗል።

እንዳለፈው ሳምንት ሁሉ በዛሬውም ውሎ ተጠርጣሪዎች በአካል በፍርድ ቤት አልተገኙም። ተጠርጣሪዎችን ወክለው በችሎት የተገኙት ሶስት ጠበቆች ናቸው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)