የሱዳን “በዝግ እንወያይ” ጥያቄ በኢትዮጵያ በኩል ተቀባይነት ሳይገኝ ቀረ

በተስፋለም ወልደየስ 

የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ የህዳሴው ግድብን በተመለከተ “በዝግ እንወያይ” ሲሉ ያቀረቡትን ጥሪ ኢትዮጵያ አለመቀበሏን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ። የሚኒስቴሩ ቃል አቃባይ ዲና ሙፍቲ ዛሬ በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫቸው እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ጥሪውን ያልተቀበለችው በህዳሴው ግድብ ላይ የተጀመረው ሂደት ሙሉ ለሙሉ ባልተቋረጠበት ሁኔታ መሰል ውይይት መካሄድን ስለማትሻ ነው። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ሀምዶክ የዝግ ውይይቱን ሀሳብ ከሳምንት በፊት ያቀረቡት ሶስቱ ሀገራት እስካሁን ባደረጓቸው ድርድሮች ወደ ስምምነት አለመድረሳቸውን በማንሳት ነው። ሀገራቱ በ2007 ዓ.ም. በፈረሙት “የመርሆዎች ስምምነት” (Declaration of Principles) የተባለ ውል እርሳቸውን ያቀረቡትን የመሪዎች ውይይት እንደሚፈቅድ የጠቀሱት ሀምዶክ፤ የሶስቱ ሀገራት መሪዎች በ10 ቀናት ተገናኝተው በዝግ እንዲወያዩ ጠይቀው ነበር።

የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ለጥሪያቸው በማመሳከሪያነት የጠቀሱት በውሉ ላይ በአንቀጽ 10 የተቀመጠውን ድንጋጌ ነው። ይህ አንቀጽ “ሶስቱ ሀገራት አለመግባባቶችን በምክክር ወይም በድርድር መፍታት ከተሳናቸው ዕርቅ ወይም ሽምግልና ሊጠይቁ ወይም ጉዳዩን ወደ መሪዎቻቸው ሊመሩ ይችላሉ” ይላል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቃባይ ዲና ሙፍቲ “ሶስቱ ሀገሮች በ2015 በተፈራረሙት decalaration of principles  አንቀጽ 10 ላይ የሚለው የተጀመረው ሂደት መቀጠል ካልቻለ የሚል ነው። Fail  አላደረገም። ሂደቱ እያለ፤ ሂደቱ እንዲከሽፍ የሚፈልጉ ሰዎች ናቸው ሂደቱን ከዚያ ለማውጣት አሁንም [በዚህ መልኩ] የመጡት” ሲሉ በዛሬው መግለጫቸው ተናግረዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ “ወደ ዝግ ውይይት እንሂድ” ለሚለው የሀምዶክ ጥያቄ ምላሽ መስጠታቸውንም ቃል አቃባዩ አክለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በምላሻቸው፤ ባለፈው ዓመት በተካሄደው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ህብረቱ ለድርድሩ ተነሳሽነቱን እንዲወስድ ውሳኔ እንደተላለፈ ማንሳታቸውን ጠቅሰዋል። በህብረቱ አማካኝነት የተጀመረው ሂደት ሙሉ ለሙሉ ሳይከሽፍ ሌላ ውይይት ማድረግ በኢትዮጵያ በኩል ተቀባይነት እንደሌለውም ዲና አስረድተዋል።     

 “በምንም መድረክ ላይ ለመገኘት ኢትዮጵያ ችግር የለባትም ግን አስፈላጊ ሲሆን ነው። አለበለዚያ ትርጉም የለሽ ነው። ዝም ብሎ የማይሆን እንቅስቃሴ ነው። ዞሮ ዞሮ የተጀመረውን ሂደት ውጤታማ እናደርገው ነው። ለጸጥታው ምክር ቤት የጻፍነው እሱን ነው። አሁንም ጠቅላይ ሚኒስትር ሃምዶክ ላመጡት ነገር ያለው ምላሽ እሱ ነው” ሲሉ ዲና አብራርተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)