የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የፌደራል መንግስት ጽንፈኛ ኃይሎችን ሥርዓት እንዲያሲዛቸው ጠየቀ

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት “ጽንፈኛ” ሲል የጠራቸው ኃይሎች የሚያራምዱትን “የጥፋት እና የብጥብጥ አጀንዳ” የሚመለከታቸው የፌዴራል መንግሥት አካላት ሥርዓት እንዲያሲይዙ ጥያቄ አቀረበ። ክልሉ ጥያቄውን ያቀረበው ዛሬ ረቡዕ ሚያዝያ 13 ባወጣው መግለጫ ነው። 

ኢትዮጵያን “ወደባሰ ውጥንቅጥ ውስጥ ለመክተት የሚሰሩ ኃይሎች” እንዳሉ የጠቆመው የክልሉ መንግስት መግለጫ፤ ሀገሪቱን “ወደ ቀውስ አዙሪት” ውስጥ ለማስገባት “የውጭ ኃይሎችና የውስጥ ተባባሪዎቻቸው ጥረት ማድረግ ጀምረዋል” ብሏል። ለጽንፈኛ ኃይሎች “እሳት እና ቤንዚን” የሚያቀብሉ እንዳሉም ወንጅሏል።

ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልን ጨምሮ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች “በዜጎች ላይ እየተፈጸሙ ያሉ አስከፊ ድርጊቶች የሚወገዙ” መሆናቸውን የጠቀሰው መግለጫው፤ “የድርጊቱ ፈጻሚዎች ላይ ተገቢውን እርምጃ የመውሰድ አስፈላጊነትም” የማያከራክር መሆኑን አስገንዝቧል። ችግሮች ሲከሰቱ “በሰከነ መንገድ ተወያይቶ ዘላቂነት ያለው የጋራ መፍትሄ መስጠት ሲገባ” ወደባሰ ቀውስ ለመክተት መሞከር ሊወገዝ የሚገባው አካሄድ ነው ብሏል።    

“የተለያዩ ጽንፈኛ ኃይሎች ሀገራችንን ወደ ባሰ ቀውስ እና ወደተወሳሰበ ችግር ውስጥ ለመክተት የሚያደርጉትን ጥረት በጥብቅ ማውገዝ፣ እሳትና ቤንዚን የሚያቀብሉትንም በአንድ ስሜት መቃወም ከሁላችን የሚጠበቅ ወቅታዊ ሀገራዊ ኃላፊነት ይሆናል”

– የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት

“የተለያዩ ጽንፈኛ ኃይሎች ሀገራችንን ወደ ባሰ ቀውስ እና ወደተወሳሰበ ችግር ውስጥ ለመክተት የሚያደርጉትን ጥረት በጥብቅ ማውገዝ፣ እሳትና ቤንዚን የሚያቀብሉትንም በአንድ ስሜት መቃወም ከሁላችን የሚጠበቅ ወቅታዊ ሀገራዊ ኃላፊነት ይሆናል” ያለው የክልሉ መግለጫ፤ እነዚህ ኃይሎች “ከድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል” ሲል አሳስቧል። 

የፌደራል መንግስት አካላት በጽንፈኛ ኃይሎች ላይ ተገቢውን እና ህጋዊ እርምጃ እንዲወስድ የጠየቀው ክልሉ፤ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የተለያዩ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ የጥፋት ቡድኖች ላይ የክልሉ መንግስት እየወሰደ ያለውን እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጧል። የክልሉ ህዝብም በማንኛውም ሁኔታ ከመንግስት ጎን እንዲቆም ጥሪ አስተላልፏል። (በቅድስት ሙላቱ – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)