በደቡብ ክልል አማሮ ልዩ ወረዳ የሚሰነዘሩ ተደጋጋሚ ጥቃቶች መቀጠላቸውን የአካባቢው ባለስልጣናት ገለጹ

በቅድስት ሙላቱ

በደቡብ ክልል አማሮ ልዩ ወረዳ ትላንት እና ዛሬ በሁለት ቀበሌዎች በተከታታይ በተፈጸሙ ጥቃቶች የሁለት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ በሌሎች ሁለት ነዋሪዎች ላይ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው የልዩ ወረዳው አስተዳደር ገለጸ። ጥቃት አድራሾቹ ከአካባቢው አርሶ አደሮች በመቶዎች የሚቆጠሩ ከብቶችንም “ዘርፈው ወስደዋል” ተብሏል።     

የአማሮ ልዩ ወረዳ የሚዲያ እና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አማረ አክሊሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደተናገሩት ዛሬ ጠዋት 11 ሰዓት ላይ በጀሎ ቀበሌ በተሰነዘረው ጥቃት የአንድ ሰው ሕይወት ሲያልፍ ሁለት ሰዎች ቆስለዋል። ጥቃት ፈጻሚዎቹ ከ100 በላይ ከብቶች መዝረፋቸውንም አክለዋል።

የጀሎ ቀበሌ አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ሰብስቤ ቸርነት እስከ ምሽት 12 ድረስ ተኩስ ይሰማ እንደነበር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። በአካባቢው ባለው ጥቃት ምክንያትም በቀበሌው የሚኖሩ ነዋሪዎች “ሙሉ ለሙሉ ተፈናቅለዋል” ብለዋል።  

እንደ ጀሎ ቀበሌ ሁሉ በታጣቂዎች በትላንትናው ዕለት ጥቃት እንደተከፈተባት በተነገረባት በዳኖ ቀበሌ አንድ አርሶ አደር ሲገደሉ፤ የአራት አርሶ አደሮች ከብቶች ተዘርፈው መወሰዳቸውን የልዩ ወረዳ የሚዲያ እና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር ጨምረው አስረድተዋል። በአካባቢው ጥቃቱን እየፈጸሙ ያሉት አካላት “በሶስት ቡድን” ተከፍለው እንደሆነ የሚናገሩት ዳይሬክተሩ፤ “ሰው ለማጥፋት፣ ከብቶች ለመዝረፍ፤ ከመንግስት አካል የሚደገፍ እና በመኪና ጭምር የሚመጣ ኃይል አለ” ሲሉ ይከስሳሉ።  

አካባቢውን ለማረጋጋት የደቡብ ክልል ልዩ ኃይል እና የፌደራል ፖሊስ አባላት ቢሰማሩም፤ ጥቃት ፈጻሚዎቹ በ“ዘመናዊ መሳሪያዎች” የታገዙ በመሆናቸው፤ ሁኔታውን ለመቆጣጠር የሚያደርጉትን ጥረት ከ“አቅም በላይ” እንዳደረገባቸው ዳይሬክተሩ ያብራራሉ። “የኦሮሚያ ክልል መንግስት በአካባቢው የሸፈተ የኦነግ ሸኔ ኃይል አለ” ማለቱን የሚያስታውሱት የጀሎ ቀበሌ አስተዳዳሪ በበኩላቸው፤ “ኦነግ ሸኔ የሚባል ቡድን በእኛ ቀጠና አንድም ቀን ጥይት ተኩሶ አያውቅም” ሲሉ ያስተባብላሉ። 

በአማሮ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን እየፈጸሙ ያሉት ልዩ ወረዳውን ከሚያዋስነው የምዕራብ ጉጂ ዞን የሚነሱ ታጣቂዎች እንደሆኑ የአካባቢው አስተዳዳሪዎች በተደጋጋሚ ሲገልጹ ቆይተዋል። ልዩ ወረዳው ከ2009 ዓ.ም ማብቂያ ጀምሮ መጠነ ሰፊ ጥቃቶችን ሲያስተናግድ መቆየቱን የሚናገሩት ባለስልጣናቱ፤ በወቅቱ የመከላከያ ሰራዊት ቦታው ላይ ገብቶ ሁኔታዎችን ለማረጋጋት ሞክሮ እንደነበር ያስረዳሉ። 

በያዝነው አመት ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ ሰራዊቱ ቦታውን ለቆ በመውጣቱ ሁለተኛ ዙር የተባሉት ጥቃቶች እየተሰነዘሩ እንደሆነም ይጠቁማሉ። በምዕራብ ጉጂ ዞን ገላና ወረዳ እና በአማሮ ልዩ ወረዳ መካከል ያለውን የጸጥታ ችግር በዕርቀ ሰላም ለመፍታት ቢሞክርም በዚያው መርሃ ግብር ላይ የተሰነዘረው ጥቃት በአካባቢው ያለውን ሁኔታ ከድጡ ወደ ማጡ አሸጋግሮታል።  

ባለፈው የካቲት 29 በተጠራው በዚህ መርሃ ግብር ላይ በመሳተፍ ላይ በነበሩ እድምተኞች ላይ በተከፈተ ተኩስ ስድስት ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል። በጥቃቱ ህይወታቸውን ካጡት ውስጥ የአማሮ ልዩ ወረዳ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳኛቸው ኤቼላ እና አንድ ፖሊስ ይገኙበታል። 

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ሚያዝያ 15 ድረስ በተሰነዘሩ ተደጋጋሚ ጥቃቶች የ18 ሰዎች ህይወት ማለፉን የአማሮ ልዩ ወረዳ የሚዲያ እና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ባለፈው አንድ ወር ከግማሽ ጊዜ ውስጥ በነበረው ጥቃትም በጀሎ እና ዶርባዴ በተባሉ ቀበሌዎች የሚገኙ በርካታ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውንም አስረድተዋል። 

ከጀሎ ቀበሌ የተፈናቀሉት 2,187 ነዋሪዎች መሆናቸውን የሚገልጹት ዳይሬክተሩ፤ ከዶርባዴ ቀበሌም በተመሳሳይ መልኩ 4,207 ሰዎች ተፈናቅለው በአሁኑ ወቅት በዳስ መጠለያ እንዳሉ ያብራራሉ። ለተፈናቃዩቹ በመንግስት በኩል የስንዴ ዱቄት ድጋፍ እየተደረገላቸው ቢሆንም በቂ እንዳልሆነ አመልክተዋል። 

በአጠቃላይ በልዩ ወረዳው የተፈናቀሉ 52 ሺህ ነዋሪዎች እንዳሉ የጠቆሙት አቶ አማረ፤ እነዚህን ተፈናቃዮች ለመርዳት የበጎ አድራጎት ድርጅቶች አስፈላጊውን ሁሉ እንዲያደርጉ ጥሪ አስተላልፈዋል። የአካባቢውን ሰላም ለመመለስም የፌደራል መንግስት በአፋጣኝ ጣልቃ በመግባት ከሃይማኖት አባቶች ጋር በመሆን እንዲሰራ ተማጽነዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)