አዲግራት እና አክሱምን የሚያገናኘው መንገድ በመዘጋቱ የህክምና ስራዎቹ መስተጓጎላቸውን ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን አስታወቀ

በትግራይ ክልል አዲግራት እና አክሱም ከተሞችን የሚያገናኘው መንገድ ላለፉት 12 ቀናት በመዘጋቱ፤ የነፍስ አድን የህክምና ስራዎቹ መስተጓጎላቸውን ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን (MSF) አስታወቀ። ድርጅቱ በአክሱም ድጋፍ ለሚያቀርብላቸው የሕክምና ተቋማት ቁልፍ አቅርቦቶች ለመላክ መቸገሩን ገልጿል።

የድርጅቱ የምሥራቅ አፍሪካ ቢሮ ዛሬ በትዊተር ገጹ ባሰራጨው መረጃ መሰረት፤ የድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን በሚደግፋቸው ሆስፒታሎች 27 ህሙማን የኦክስጅን ሕክምና ይፈልጋሉ። እነዚሁ ሆስፒታሎች በየዕለቱ ኦክስጅን የሚያስፈልጋቸው ሰባት የቀዶ ሕክምና ያካሂዳሉ።

“አቅርቦቶቻችን እየተጠናቀቁ ነው። ምንም ነገር ካልተለወጠ በሶስት ቀናት እንጨርሳለን” ያለው የግብረ ሰናይ ድርጅቱ፤ “በአክሱም በመድኃኒቶች እጦት ሳቢያ ከቀዶ ህክምና በኋላ የሕመም ማስታገሻ መስጠት አልቻልንም” በማለት አክሏል።

ድርጅቱ እንደሚለው፤ በርካታ የተጎዱ ሰዎች በሚኖሩበትና የድንገተኛ እርዳታ በሚፈለግበት ጊዜ ሆስፒታሉ ህሙማንን በቅጡ ለማከም ይቸገራል። አክሱም እና አዲግራትን የሚያገናኘው፤ 135 ኪሎ ሜትር ገደማ ርዝመት ያለው አውራ ጎዳና ከአንድ ሳምንት በላይ ተዘግቶ መቆየቱ ደግሞ የህክምና ተቋማት ስራዎች ላይ ይበልጡኑ ጋሬጣ እንደሚያስከትል ጠቁሟል።

“በመንገዱ መዘጋት ምክንያት ከአክሱም ውጪ ባሉ ገጠራማ አካባቢዎች ግልጋሎት የሚሰጡ ተንቀሳቃሽ ክሊኒኮች ስራ ተስተጓጉሏል። የክትባት መርሐ ግብሮች ተቋርጠዋል” ብሏል ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድኑ።

በአክሱም 127 የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ያለባቸው ህፃናት መኖራቸውን የገለጸው ቡድኑ፤ ለጤንነታቸው ክብካቤ አስፈላጊ የሆኑ የበለጸጉ ምግቦች በዚህ ሳምንት እንዳልተከማቹ አስታውቋል።

የትግራይ እና የኢትዮጵያ “የፖለቲካ እና ወታደራዊ ባለሥልጣናት አስፈላጊ አቅርቦቶች ከአዲግራት ወደ አክሱም እንዲጓጓዙ በአፋጣኝ እንዲፈቅዱ” የጠየቀው የግብረ ሰናይ ድርጅቱ፤ “ህይወታቸውን ለማዳን የህክምና ዕገዛ የሚፈልጉ ህሙማን ጊዜው እያለፈባቸው ነው” ሲል የሁኔታውን አሳሳቢነት አጽንኦት ሰጥቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)