የፍርድ ቤት ውሎ፦ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በእነ እስክንድር ነጋ የምስክር አሰማም ሂደት ላይ ውሳኔ ለመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ

በቅድስት ሙላቱ

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሁለተኛ ወንጀል ይግባኝ ችሎት ዛሬ በእነ እስክንድር መዝገብ የምስክሮች አሰማም ሂደትን በተመለከተ ለቀረበለት የይግባኝ አቤቱታ ውሳኔ ለመስጠት ለሚያዝያ 26 ቀጠሮ ሰጠ። ፍርድ ቤቱ ቀጠሮውን የሰጠው በተከሳሽ እና በዐቃቤ ህግ በኩል ያለውን ክርክር በዛሬው የችሎት ውሎው ካዳመጠ በኋላ ነው። 

ጉዳዩ ለዛሬ የተቀጠረው የጠቅላይ ፍርድ ቤት በእነ እስክንድር ነጋ መዝገብ የምስክሮችን አሰማም ሂደት በተመለከተ በአቃቤ ህግ የቀረበውን ይግባኝ ለመመልከት ነበር። ባለፈው ችሎት ተከሳሾች በፕላዝማ ይከታተላሉ ተብሎ የነበረ ቢሆንም ፕላዝማው አገልግሎት መስጠት ባለመቻሉ፤ በተከሳሽ ጠበቃ በቀረበ የተለዋጭ ቀጠሮ ጥያቄ ክርክሩ ለዛሬ ተዘዋውሮ ነበር። 

በዛሬው ችሎት በእነ እስክንድር መዝገብ ከተካተቱ አምስት ተከሳሾች ውስጥ፤ በማረሚያ ቤት የሚገኙት አራቱ ባሉበት ሆነው በፕላዝማ በመቅረብ ችሎቱን ተከታትለዋል። እስክንድር ነጋን ጨምሮ አራቱን ተከሳሾች በመወከል በአካል ቀርበው የተከራከሩት ጠበቃቸው አቶ ቤተማርያም አለማየሁ ናቸው።

በመዝገቡ ላይ በአምስተኛ ተከሳሽነት የተመዘገቡትና ጉዳዩን በውጭ ሆነው በመከታተል ላይ ያሉት ጌትነት በቀለም ከጠበቃቸው ጋር በአካል ተገኝተው በምስክር አሰማም ሂደቱ ላይ ይግባኝ ካቀረበው አቃቤ ህግ ጋር ተከራክረዋል። ተከሳሾቹ የተከሰሱበት ጉዳይ ከባድ መሆኑን ያነሳው ዐቃቤ ህግ በዚህም ምክንያት የምስክር አሰማም ሂደቱ ከፊሉ በዝግ ችሎት እና ከፊሉ ደግሞ ከመጋረጃ ጀርባ እንዲሆን ጠይቋል።   

ዐቃቤ ህግ የጉዳዩ ክብደት ለማስረዳት ተከሳሾች በተከሰሱበት ብሔርና ሀይማኖትን መሠረት ያደረገ ግጭት በመቀስቀስ ወንጀል  የ14 ሰዎች ህይወት ማለፉን ጠቅሷል። የጉዳዩን ክብደት ከግምት ውስጥ በማስገባትም ለምስክሮች ጥበቃ ማድረግ ማስፈለጉንም አስረድቷል። 

በዚህም መሰረት የምስክር አሰማም ሂደቱ፤ 16 ለሚሆኑት ምስክሮች በዝግ ችሎት እንዲሁም አምስት ለሚሆኑት ደግሞ ከመጋረጃ ጀርባ እንዲሆን ዐቃቤ ህግ አመልክቷል። ከዚህ በተጨማሪም “ምስክሮቹ እና ተከሳሾች ትውውቅ ስላላቸው በዝግ ችሎት መሆኑ ትርጉም የሌለው ነው” በማለት የስር ፍርድ ቤት የምስክር አሰማም ሂደቱ በግልጽ እንዲከናወን ያስተላለፈው ውሳኔ “መሰረታዊ ስህተት አለበት” በማለት ተሟግቷል። 

ተከሳሾች “የአንድ ፓርቲ አባላት” መሆናቸውን ያስረዳው ዐቃቤ ህግ፤ ተከሳሾቹ ብዙ ደጋፊዎች ስላሏቸው ምስክሮቹ ላይ “ጉዳት የማይደርስበት ሁኔታ አይኖርም” ሲል የደህንነታቸው ጉዳይ አሳሳቢ መሆኑን ጠቁሟል። “አንድ ለፍትህ አሰራር ሲል ምስክርነት የሚሰጥ ሰው ለሕይወቱ አያሰጋውም አይባልም” በማለትም አክሏል።

በተከሳሾችና በጠበቆቻቸው ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ሲነሳ የነበረውን “በግልጽ ችሎት የመዳኘት ህገ መንግስታዊ መብት” ያጣጣለው ዐቃቤ ህግ፤ የህገ መንግስቱ አንቀጽ 20 ሚያትተው “ማስረጃዎችን የማየት እና ምስክሮችን የመጠየቅ እንጂ ፊት ለፊት እያዩ የመጠየቅ” አለመሆኑን አስረድቷል። “ማስረጃዎችን የመመልከት መብት እና ምስክሮችን የመጠየቅ መብት እንጂ የመመልከት መብት የላቸውም” ብሏል።

ዐቃቤ ህግ የተጠቀሱትን መቃወሚያ ነጥቦች ለማጠናከር በአለም አቀፍ ደረጃ የተሰጡ የተለያዩ ውሳኔዎችን ዘርዝሯል። በኢትዮጵያ የምስክሮችን ጥበቃ በተመለከተ በወጣው አዋጅ ቁጥር 699/2010 ላይም፤ ፍርድ ቤት በዝግ ችሎት ይሁን ብሎ የመወሰን ወይም የማሻሻል ስልጣን ያለው “ልዩ ጥበቃ ለሚሹ አካለ መጠን ላልደረሱ ልጆች” ብቻ መሆኑን ጠቅሷል። ከእነዚህ ውጭ ላሉ ምስክሮች ስለሚደረግ ጥበቃም ሆነ የምስክርነት ቃላቸው የሚሰሙበት ሂደት “በዝግ ወይም በግልጽ ችሎት ይሁን ብሎ የመወሰን ስልጣን ያለው ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ነው” ሲልም ተከራክሯል።

ዐቃቤ ህግ ከዚህ በተጨማሪ ምስክሮቹ ራሳቸው የደህንነት ስጋት ያለባቸው መሆኑን ከራሳቸው መረዳቱን ገልጿል። ምስክሮቹ “አመራር እንኳን ለማስገደል የተዘጋጀው ኃይል እኔ ብመሰክርበት ጉዳት ያደርስብኛል” እንደሚሉ የገለጸው ዐቃቤ ህግ፤ ማንነታቸው ለዳኞች ብቻ ግልፅ ሆኖ ከተከሳሾች እና ደጋፊዎቻቸው ድብቅ መሆኑ፤ “የተከሳሾችን የመጠየቅ መብት አያጣብብም” ብለዋል።

በዛሬው ክርክር ላይ የዐቃቤ ህግ ይግባኝ ላይ መቃወሚያቸውን ያቀረቡት ሁለቱ ጠበቆች እና አራቱ ተከሳሾች የምስክር አሰማም ሂደቱ ለእነሱም ሆነ ለህዝብ ግልፅ በሆነ መንገድ እንዲደረግ ጠይቀዋል። ተከሳሾቹ ከዚህም በተጨማሪ የምስክሮቹ ቃል፤ በራሳቸው መመዘኛ እውነተኛነቱን ማረጋገጥ እንደሚሹ ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል።

የዐቃቤ ህግን አቤቱታ “መሰረታዊ መብቶችንና ነፃነቶችን የጣሰ ነው” በማለት የተቃወሙት የተከሳሽ ጠበቃ፤ በአቤቱታው ላይ የዐቃቤ ህግ ስም አለመፃፉ “እራሱ ያላመነበትን ጉዳይ ነው” ብለን እንድናስብ አድርጎናል ብለዋል። ጠበቃው አክለውም “መንግስትን አላፈናፍን ያሉ የፖለቲካ ተፎካካሪዎችን ገለል ለማድረግ ሆን ተብሎ የቀረበ ነው” በማለት ለፍርድ ቤቱ ተቃውሟቸውን አቅርበዋል። ተከሳሾቹ በሰላማዊ መንገድ ስልጣን ለመያዝ፤ በመጪው ሀገራዊ ምርጫ ላይ ለመወዳደር በዝግጅት ላይ እንደሆኑም ጨምረው ገልፀዋል። 

አቃቤ ህግ የምስክሮች አሰማም ሂደት በዝግ ችሎት እና ከመጋረጃ ጀርባ ይሁን ማለቱ “ሪሞቱን እኔ ይዤ አካሄዱን ልቆጣጠረው” አይነት እንደሆነ የጠቀሱት ጠበቃው፤ በኢትዮጵያ ህግ አስፈጻሚ አካላት ታምነው ስለማያውቁ ሚዛናዊ የሆነውን አሰራር ይጎዳል ሲሉ ተከራክረዋል። አንደኛ ተከሳሽ የሆኑት አቶ እስክንድር ነጋ የጠበቃውን ክርክር ደግፈው የስር ፍርድ ቤት በግልጽ ችሎት ይሁን ብሎ ያስተላለፈው ውሳኔ “መጽናት አለበት” ብለዋል። 

አቶ እስክንድር፤ ዐቃቤ ህግ ለምስክሮቹ “አድራሻን መቀየር እና መሳሪያ ማስታጠቅን” የመሰሉ ሌሎች የጥበቃ አማራጮችን እንዲወስድም ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል። “በደረቅ ወንጀል ሳይሆን በፖለቲካ ወንጀል ተከሰን የመጣን ስለሆነ ፍርድ ቤቱ በግልጽ ችሎት ያደርገው” ሲሉም አክለዋል። 

ፍርድ ቤቱ ዐቃቤ ህግ ባስቀመጠው መሠረት “በዝግ ችሎት” ይሁን ብሎ ከወሰነ ግን ጉዳዩ “የህዝብም የታሪክም ፍርድ ያስፈልገዋል” ሲሉ አቶ እስክንድር አሳስበዋል። “እያንዳንዱ ክርክር ለመገናኛ ብዙሀን እንዲገለፅ ፍርድ ቤት ማመቻቸት አለበት” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል። 

በዚሁ ሀሳብ ላይ አስተያየት የሰጡት ሁለተኛ ተከሳሽ ስንታየሁ ቸኮል፤ ምስክሮች ሀሰተኛ ናቸው የሚለውን ህዝቡ መመዘን ስለሚገባው በግልፅ ችሎት ይሁን ሲሉ ተመሳሳይ ሀሳብ ሰጥተዋል። “ፍርድ ቤቱ ዐቃቤ ህግ ባለው መንገድ ውሳኔውን ቢሰጥ በኢትዮጵያ ለውጥ መጥቷል መባሉ ሀሰት መሆኑን በአደባባይ የምናሳይበት ይሆናል” ብለዋል። 

አቶ ስንታየሁ መከራከሪያቸውን በሚያቀርቡበት ወቅት፤ ፍርድ ቤቱ ተገቢውን ንግግር እያደረጉ እንዳልሆነ በማንሳት በተደጋጋሚ እርማት እንዲያደርጉ አስጠንቅቋቸዋል። እንዲያም ቢሆን ተከሳሹ “የብልጽግና ፓርቲ ህዝቡ የስልጣን ባለቤት እንዳይሆን ለማድረግ ነው በሀሰት የወነጀለን” ሲሉ ገዢውን ፓርቲ የሚከስስ ንግግር አድርገዋል።

ከተከሳሾቹ አንዷ የሆኑት ቀለብ (አስቴር) ስዩም “የእኛ እውነት በችሎቱ ወንበር ስር ስለተደበቀችብን እውነታችንን እንድትመልሱልን በኢትዮጵያ ስም እጠይቃለሁ” ሲሉ ተደምጠዋል። ተከሳሿ ምስክሮች ዝምድና ወይም ፀብ እንዳላቸው ካላየናቸው እንዴት እናውቃለን? ሲሉም ለፍርድ ቤቱ ጥያቄ አቅርበዋል። 

የአምስተኛ ተከሳሽ የአቶ ጌትነት ጠበቃ በበኩላቸው በዐቃቤ ህግ በኩል በማጣቀሻነት የቀረበው የሌሎች ሀገራት የዳኝነት ስርዐት ምሳሌን ተችተዋል። ምሳሌው አሁን ካለው ጉዳይ ጋር ግንኙነት እንደሌለውና እሱን እንዲተገበር የሚያደርግ የህግ ድንጋጌ በኢትዮጵያ አለመኖሩንም በማንሳት ተከራክረዋል። 

የምስክሮች ጥበቃ አዋጅ “አንድ ምስክር ጥበቃ ለማግኘት ቀድሞ ማመልከት እንዳለበት በአስገዳጅነት ያስቀምጣል” ሲሉ የጠቀሱት ጠበቃው፤ በስር ፍርድ ቤት በነበረ ክርክር ከምስክሮች የቀረበ ማመልከቻ የለም ብለዋል። በተጨማሪም ዐቃቤ ህግ አንቀጽ በመጥቀስ ብቻ “ለምስክሮች ጥበቃ አድርጊያለሁ” ማለቱ በህግ አግባብ የተጠቀሱ አንቀጾች እንደጊዜው የሚለዋወጡ በመሆናቸው “ተቀባይነት የለውም” ሲሉ ሞግተዋል።

በተከሳሾች በኩል ለተነሱት መከራከሪያዎች መልስ የሰጠው ዐቃቤ ህግ፤ “በጠበቆች የቀረቡት የህግ አንቀጾች ትክክል አይደሉም” በማለት ችሎቱ ህጉን ከፍቶ ማየት እንዳለበት ተናግረዋል። ማንም ምስክር ቀርቦ ለመመስከር ፍቃደኛ ካልሆነ የፍትህ ስርዐቱ ሊዛባ ስለሚችል የምስክርነት መስማት ሂደቱ በዝግ ችሎት እንዲሆን በድጋሚ ለፍርድ ቤቱ አመልክቷል። 

በመጨረሻም ፍርድ ቤቱ ቀጠሮ ከመስጠቱ በፊተ ለዐቃቤ ህግ የማጣሪያ ጥያቄዎች አቅርቧል። ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በአዋጁ መሠረት በዝግ ችሎት ይሁን የማለት ስልጣን አለው መባሉን የጠቀሰው ችሎቱ፤ ፍርድ ቤቱ “የተሰጠውን ዝም ብሎ መቀበል አለበት ወይ?” ሲል ጠይቋል። 

ዐቃቤ ህግም በምላሹ፤ የፍርድ ቤት ሚና ችሎቱ በዝግ ወይም በግልጽ ይሁን ማለት ሳይሆን ከዚያ በኋላ የሚከተሉ ሂደቶችን በተገቢው መንገድ መካሄዳቸውን ማረጋገጥ እንደሆነ አብራርቷል። በአዋጁ መሰረት አንድ ፍርድ ቤት የዐቃቤ ህግን ጥበቃ የማቋረጥ ስልጣን የለውም ሲልም አስረድቷል።

ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ህግን ምላሽ ካደመጠ በኋላ ተጨማሪ ማጣሪያ ጥያቄ ሰንዝሯል። ዐቃቤ ህግ የምስክር አሰማም ሂደቱ በዝግ ችሎት ይሁን ሲል ተከሳሾች ከተከሰሱበት ወንጀል አንጻር እንደሆነ መጥቀሱን ያስታወሰው ፍርድ ቤቱ፤ አንድ ጊዜ የተጠቀሱ የህግ አንቀጾች በክስ ሂደት ውስጥ ሊለዋወጡ የሚችሉበትን አግባብ ዐቃቤ ህግ እንዴት እንደሚመለከተው ጠይቋል።  

ዐቃቤ ህግ ለዚህ ጥያቄ በሰጠው ምላሽ፤ “በዝግ ችሎት ይሁን ያልኩት በአንቀፅ ብቻ ሳይሆን፤ በተፈጸመው ድርጊት ላይ ተመስርቼ ያለውን ስጋት በማየት ነው” ሲል ተናግሯል። ፍርድ ቤቱ ለውሳኔ ተለዋጭ ቀጠሮ ከመስጠቱ በፊት በአቶ እስክንድር የቀረበውን ማሳሰቢያ ተመልክቷል። አቶ እስክንድር በታች ፍርድ ቤት የታየዘው ቀጠሮ ለሚያዝያ 28 መሆኑን ጠቅሰው ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ከዚያ በፊት ውሳኔውን እንዲሰጥ ጠይቀዋል። 

ለዚህ ማሳሳቢያ በተከሳሹ በኩል በማጠናከሪያነት የቀረበው ማብራሪያ፤ የተከሳሾች የተፋጠነ ፍትህ የማግኘት መብት እና ተከሳሾቹ በመጪው ግንቦት ወር መጨረሻ በሚደረገው ጠቅላላ ምርጫ ላይ ለመሳተፍ ያላቸው ፍላጎት ነው። የተከሳሽን ማሳሰቢያ ያደመጠው ፍርድ ቤቱ፤ የሁለቱን ወገኖች ክርክር መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት ለሚያዝያ 26 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)