ከባህርዳር ወደ አዲስ አበባ ተደራጅተው እየተጓዙ ነበሩ የተባሉ ወጣቶች ከጎሃ ጽዮን እንዲመለሱ መደረጉን ፖሊስ ገለጸ

በቅድስት ሙላቱ 

በትላንትናው ዕለት መነሻቸውን ከባህርዳር አድርገው በህዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች ወደ አዲስ አበባ በመጓዝ ላይ የነበሩ የተወሰኑ ወጣቶች፤ ከጎሃ ጽዮን ከተማ መግቢያ ወደመጡበት እንዲመለሱ መደረጉን የሰሜን ሸዋ ዞን ዋራ ጃርሶ ወረዳ ፖሊስ ገለጸ። ወጣቶቹ እንዲመለሱ የተደረጉት ወደ አዲስ አበባ በመግባት “ችግር ለመፍጠር አቅደዋል” የሚል መረጃ ለፖሊስ በመድረሱ ነው ተብሏል። 

በዋራ ጃርሶ ወረዳ ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ሳጅን ሀብታሙ ግርማ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደተናገሩት ትላንት አርብ ሚያዝያ 15፤ በጎህ ጽዮን ከተማ መግቢያ ላይ ባለ ኬላ ላይ ከተደረገ ፍተሻ በኋላ ሶስት የህዝብ ማመላለሻ ቅጥቅጥ አይሱዙ አውቶብሶች ወደመጡበት ባህርዳር እንዲመለሱ ተደርጓል። እያንዳንዳቸው አውቶብሶች ከ30 እስከ 40 የሚሆኑ ወጣቶችን አሳፍረው እንደነበርም ገልጸዋል። 

አውቶብሶቹን የተመለሱት “የተደራጁ ወጣቶች አዲስ አበባ በመግባት ችግር ሊፈጥሩ መሆኑን መረጃ ደርሶን ነው”

ሳጅን ሀብታሙ ግርማ – በዋራ ጃርሶ ወረዳ ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ

ሳጅን ሀብታሙ፤ አውቶብሶቹ እስከነተሳፋሪዎቹ እንዲመለሱ የተደረጉበትን ምክንያት ሲያስረዱ፤ “የተደራጁ ወጣቶች አዲስ አበባ በመግባት ችግር ሊፈጥሩ መሆኑን መረጃ ደርሶን ነው” ብለዋል። መረጃውን ተከትሎ የአካባቢው ፖሊስ ትላንት ከጠዋቱ አራት ሰዓት እና ከሰዓት በኋላ ባደረጓቸው ፍተሻዎች ወጣቶችን በአውቶብሶቹ ውስጥ ማግኘቱን አስረድተዋል። 

የትላንቱን ፍተሻ፤ ከፖሊስ አባላት በተጨማሪ “የአካባቢው ወጣቶች ሲያከናውኑ ታይተዋል” መባሉን በመጥቀስ ጥያቄ የቀረበላቸው የወረዳው ወንጀል መከላከል ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ፤ መረጃውን አስተባብለዋል። “የፖሊስ አባላት ብቻ ናቸው የፈተሹት” ሲሉ ሳጅን ሀብታሙ ምላሽ ሰጥተዋል።

በዛሬው ዕለት በማህበራዊ የትስስር ገጾች የተሰራጩ መረጃዎች ተጨማሪ አውቶብሶች ዛሬም እንዲመለሱ ተደርገዋል ብለዋል። ከመረጃዎቹ ጋር በአባሪነት የተያያዙ ፎቶዎችም፤ ተሳፋሪዎቻቸውን ያወረዱ እና ከመንገድ ዳር የቆሙ በርከት ያሉ አውቶብሶችን አሳይተዋል። 

ፎቶዎች፦ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የፎቶ ክምችት የተወሰዱ

በእርግጥም ዛሬ ቅዳሜ አውቶብሶች ተመልሰው እንደው ለማጣራት “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ባህርዳር ወደሚገኙ የአባይ ባስ፣ የኛ ባስ እና ዋሊያ ባስ ጽህፈት ቤቶች በመደወል ጥያቄዎችን አቅርባለች። የሶስቱም የህዝብ ማመላለሻ ድርጅቶች ተወካዮች ወደ ባህርዳር የተመለሰባቸው አውቶብስ እንደሌለ ምላሽ ሰጥተዋል።   

የየድርጅቶቹ ሁሉም አውቶብሶች ትላንትና እና ዛሬ ከጠዋቱ 11 ሰዓት ከባህርዳር ወጥተው በሰላም ወደ አዲስ አበባ መግባታቸውን ተወካዮቹ ገልጸዋል። በሁለቱም ቀን በአውቶብሶቻችው ላይ ፍተሻ መካሄዱን ግን ተወካዮቹ ተናግረዋል። 

በዛሬው ዕለትም ፍተሻ መካሄዱን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያረጋገጡት ሳጅን ሀብታሙ፤ ሆኖም የተመለሰ አውቶብስም ሆነ ተጓዥ እንደሌለ አስረድተዋል። በዛሬው ፍተሻ በርከት ያሉ ተጓዝ ተማሪዎች እንደነበሩ የገለጹት የወረዳው ወንጀል መከላከል ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ፤  “እነርሱን እየፈተሽን አሳልፈናል” ብለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)