የሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ አባላትን የምርጫ ሂደት በተመለከተ ምርጫ ቦርድ የሰጠውን ውሳኔ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውድቅ አደረገ

በቅድስት ሙላቱ 

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ አባላት ከክልሉ ውጪ ባሉ የብሔሩ ተወላጆች የሚመረጡበት ሂደትን በተመለከተ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያስተላለፈውን ውሳኔ ውድቅ አደረገ። ፍርድ ቤቱ ዛሬ ማክሰኞ በዋለው ችሎት የጉባኤ አባላቱ የምርጫ ሂደት የሽግግር መንግስት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የክልሉ ህገ መንግስት በሚያስቀምጡት መሰረት እንዲካሄድ ሲል ወስኗል።

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዛሬ ውሳኔውን ያስተላለፈው የሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ፤ በምርጫ ቦርድ ውሳኔ ላይ የይግባኝ አቤቱታ ማቅረቡን ተከትሎ ነው። አቤቱታው የቀረበው፤ “የሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ አባላት ከክልሉ ውጪ ባሉ የብሄሩ ተወላጆች መመረጥ አይችሉም” የሚለውን የምርጫ ቦርድን ውሳኔ በመቃወም ነበር። 

ከሐረሪ ክልል ውጭ የሚገኙ የብሔሩ ተወላጆች ከዚህ ቀደም በነበሩ አምስት ሀገራዊ ምርጫዎች፤ በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ሆነው የሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ አባላትን ሲመርጡ ቆይተዋል። የሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤን ጨምሮ የክልሉ የተለያዩ አካላት በመጋቢት ወር ለምርጫ ቦርድ በጻፏቸው ደብዳቤዎች፤ በመጪው ግንቦት ወር መጨረሻ በሚከናወነው ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫም ተመሳሳይ አፈፃፀም ተግባራዊ እንዲሆን ምርጫ ቦርድን ጠይቀው ነበር።

እነዚህ አካላት ለጥያቄያቸው በማስረጃነት ያያዙት የኢትዮጵያ ሽግግር መንግስት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ1987 ዓ.ም አስተላልፎታል ያሉትን ውሳኔ እና ጉዳዩን በተመለከተ በክልሉ ህገ- መንግስት የተደነገገውን ክፍል ነበር። ጥያቄው የቀረበለት ብሔራዊው የምርጫ አስፈጻሚ መስሪያ ቤት ግን ማብራሪያዎቹ አሳማኝ አለመሆናቸውን በመግለጽ ውድቅ አድርጓቸዋል።

ምርጫ ቦርድ ሚያዝያ 1 በፃፈው የምላሽ ደብዳቤ፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔ ነው ተብሎ በጥያቄ አቅራቢዎቹ በማስረጃነት የቀረበው ሰነድ፤ “ማህተም የሌለው” መሆኑን በመጥቀስ በቦርዱ ዘንድ ተቀባይነት እንደሌለው አስታውቆ ነበር። ጥያቄው ውድቅ በመደረጉ ቅር የተሰኘው የሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ ሚያዝያ 6፤ 2013 ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የይግባኝ አቤቱታ አቅርቧል። 

አቤቱታው ከክልሉ ውጪ የሚገኙ የሐረሪ ብሔር አባላት፤ የሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ አባላትን ለመምረጥ የሚሰጡት ድምጽ “በህገ መንግስቱ የተረጋገጠ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ነው” ሲል ይሞግታል። የሽግግር መንግስቱ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአናሳ ቁጥር ባላቸው ብሄረሰቦችን በተመለከተ የተለያዩ ሀገራትን ልምድ እና ህጎች በመመርመር በ102ኛ መደበኛ ስብሰባ ማጽደቁንም በማስረጃነት ይጠቅሳል። 

ሆኖም ምርጫ ቦርድ በደብዳቤ በሰጠው ምላሽ ላይ የተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔ ህገ መንግስታዊ ድጋፍ የለውም ማለቱንም አቤቱታው አስታውሷል። ከክልላቸው ውጭ ያሉ የሐረሪ ብሔር አባላት የመምረጥ መብት ከተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔ በተጨማሪ በክልሉ ህገ መንግስት አንቀጽ 49 እና 50 ላይ በግልፅ መደንገጉንም በአቤቱታው በተጨማሪነት ተመልክቷል።    

“ቦርዱ የመንግስት አካላት የበላይ የሆነው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔን እና የክልል ህገ መንግስትን በገለልተኝነትና በፍትሐዊነት የማስፈፀም እንጂ፤ በመገምገም የማሻሻልም ሆነ የመቀየር ኃላፊነት አልተሰጠውም” ሲል የሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ በይግባኝ አቤቱታው ላይ ተከራክሯል። 

ብሔራዊ ጉባኤው ከሐረሪ ክልል ውጭ ያሉ የብሔሩ ተወላጆች የምርጫ ተሳትፎን በተመለከተ፤ በ2011 በወጣው የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነምግባር አዋጅ ላይ የተደነገገ አንቀጽን በማስረጃነት ጠቅሷል። በአቤቱታው የተጠቀሰው የአዋጁ አንቀጽ 17፤ ከኢትዮጵያ ውጭ ጭምር የሚኖሩ ዜጎች የመራጭነት ተሳትፎን በተመለከተ ልዩ ስርዓት የሚዘረጋበትን መንገድ ቦርዱ አጥንቶ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀርባል ይላል። 

በዚሁ አዋጅ ላይ የክልል ምክር ቤቶች ምርጫ፤ በክልሎች ህገ መንግስት እና አግባብነት ባላቸው ህጎች እንደሚፈጸም መጠቀሱንም አቤቱታው አትቷል። የምርጫ ቦርድ “በህግ መሠረት የሌላቸውን ልምዶች የሚያስቀር የማሻሻያ እርምጃ ወስጃለሁ” ማለቱ ከክልሉ ውጭ የሚገኙ ሐረሪዎችን የመምረጥ መብት የሚመለከት ሊሆን አይገባም ሲል ብሔራዊ ጉባኤው በአቤቱታው ሞግቷል። 

ጉባኤው በአቤቱታው ማጠቃለያ ላይ፤ ምርጫ ቦርድ በሚያዝያ 1 ቀን የሰጠው ውሳኔ ተሽሮ በህጉ እና በነበረው አሰራር መሠረት ከሐረሪ ክልል ውጪ ያሉ የብሔሩ አባላት የመምረጥ መብት እንዲያገኙ ሲል ጠይቋል። አቤቱታው በሚያዝያ 6 የቀረበለት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፤ ከአንድ ቀን በኋላ በተሰየመ ችሎት ጉዳዩ ይግባኝ ያስቀርብ እንደው ተመልክቷል።

ፍርድ ቤቱ ጉዳዩ ይግባኝ የሚባልበት መሆኑን የሚያመለክት ውሳኔ ካስተላለፈ በኋላ፤ ምርጫ ቦርድ ለአቤቱታው የሚሰጠውን ምላሽ በፅሁፍ እንዲያቀርብ ለሚያዝያ 12 ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር። ነገር ግን ምርጫ ቦርድ መጥሪያው የደረሰው ዘግይቶ ስለነበር ምላሹን በዕለቱ ማቅረብ ሳይችል ቀርቷል። 

ምርጫ ቦርድ ከሁለት ቀናት በኋላ ሚያዝያ 14 ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በጹሁፍ ባስገባው ምላሽ፤ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን የመመልከት “ስልጣን የለውም” ሲል ተቃውሟል። ለዚህ በምክንያትነት የጠቀሰውም የክልሉ ህገ መንግስት በአንቀፅ 50 (2) ላይ የደነገገው “የሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ አባላት በክልሉ ውስጥ እና ከክልሉ ውጭ በሌላ በኢትዮጵያ ክልሎችና ከተሞች የሐረሪ ብሔረሰብ አባላት ይመረጣል” የሚለው ከኢፌዲሪ ህገ መንግስት በአንቀፅ 50 (3) ጋር ይቃረናል በሚል ነው። 

ቦርዱ የጠቀሰው የህገ መንግስቱ አንቀጽ “የፈደራሉ መንግስት ከፍተኛ የስልጣን አካል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው። ተጠሪነቱም ለሀገሪቱ ህዝብ ነው” ይላል። ከዚህ በተጨማሪም ይሄው አንቀጽ “የክልል ከፍተኛ የስልጣን አካል የክልሉ ምክር ቤት” መሆኑን ጠቅሶ “ተጠሪነቱም ለወከለው ክልል  ህዝብ መሆኑን” ያስቀምጣል። ምርጫ ቦርድ ጉዳዩ ህገ መንግስታዊ ትርጓሜ የሚያስፈልገው ስለሆነ ይህንን የማየት ስልጣን ያለው የፌደሬሽን ምክር ቤት ነው ብሏል። 

ምርጫ ቦርድ፤ የሽግግር መንግስቱ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “ውሳኔውን የሚደገፍ ህገ መንግስታዊ አንቀጽ አላስቀመጠም” በማለት በምላሹ ላይ ተከራክሯል። ለአነስተኛ ብሔረሰቦች ልዩ የሆነ የምርጫ አሰራር በህገ መንግስቱ አለመካተቱንም ጠቅሷል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመጋቢት 6፤ 1987 የሰጠው ውሳኔ፤ ነሐሴ 1987 ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ ከገባው የኢፌዲሪ ህገ መንግስት በፊት መሆኑን ምርጫ ቦርድ በተጨማሪነት አንስቷል።    

የምርጫ አስፈጻሚ መስሪያ ቤቱ፤ ከምርጫ ህጉ ጋር የማይጣጣም ልማዶችን ይዞ ቢቀጥል ተመሳሳይ ሁኔታ በሌሎች ክልሎች የሚቀርብ ቢሆን እና ቦርዱ ማስተናገድ ባይችል ፍትሐዊ እና ገለልተኛነቱን ከጥያቄ ውስጥ እንደሚከት በመጥቀስም ከሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ የቀረበውን አቤቱታ ተቃውሟል።  

ይግባኝ ባይ በምርጫ ቦርድ ለተነሱ መቃወሚያዎች፤ እያንዳንዱን ነጥቦች በመዘርዘር በበነጋታው የመልስ መልስ ሰጥቶበታል። በመልስ መልሱ ላይም ከተካተቱት ነጥቦች መካከል፤ አሁን በስራ ላይ ያለው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽግግር መንግስቱ ወቅት በሰጠው ውሳኔ ላይ ማህተም አድርጎ ሚያዝያ 4፤ 2013 ለቦርዱ እንደላከ አንስቷል። ምክር ቤቱ ለቦርዱ በላከው በዚሁ ደብዳቤ ላይ፤ የሐረሪ ክልል የምርጫ ሂደት በሽግግር ጊዜ የነበረው ምክር ቤት ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት እንዲፈጸምም ማሳሰቡንም አክሏል።

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሁለቱም ወገኖች የተነሱትን ነጥቦች ከመረመረ በኋላ ዛሬ ማክሰኞ ሚያዝያ 19 በጽህፈት ቤት በኩል ውሳኔ ሰጥቷል። ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን የሰጠው ሁለት ጭብጦችን ከመረመረ በኋላ ነው።

ምርጫ ቦርድ ጉዳዩ “ህገ መንግስታዊ ትርጓሜ የሚያሻ ነው። በመሆኑም ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ለማየት ስልጣን የለውም” በሚል ያቀረበውን መቃወሚያ የተመለከተው ፍርድ ቤቱ፤ የመከራከሪያ ጭብጡን ውድቅ አድርጎታል። ቦርዱ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከዚህ ቀደም በጉዳዩ ላይ የሰጠውን ውሳኔ እና የሐረሪ ህገ መንግስትን መርምሮ ያስተላለፈውን ውሳኔ፤ “ከሐረሪ ክልል ውጪ ያሉ ዜጎች ቢመርጡ የሚደርሰውን አሉታዊ ተፅዕኖ ያላስረዳ ነው” በሚልም ሳይቀበለው ቀርቷል። 

ፍርድ ቤቱ በመጨረሻም የሐረሪ ጉባኤ አባላትን የመምረጥ ሂደት በሽግግር መንግስት ወቅት የነበረው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባስተላለፈው ውሳኔ እና የክልሉ ህገ መንግስት በደነገገው መሰረት እንዲካሄድ ሲል ወስኗል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)