በእነ ስብሃት ነጋ መዝገብ የምስክር አሰማም ሂደት ሊደረግ የነበረው ክርክር ለነገ ተዘዋወረ

በቅድስት ሙላቱ

የፌደራል አንደኛ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት፤ በእነ አቶ ስብሃት ነጋ መዝገብ በቅድመ ምርመራ የተቆጠሩ ምስክሮችን የአሰማም ሂደት በተመለከተ ለዛሬ ሊደረግ የነበረውን ክርክር ለነገ አዘዋወረ። ፍርድ ቤቱ ለነገ ተለዋጭ ቀጠሮ የሰጠው በዛሬ የችሎት ውሎ ከግማሽ በላይ ተከሳሾች ባለመቅረባቸው ነው።

የጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ዛሬ ረቡዕ ሚያዝያ 19 የተሰየመው፤ የቅድመ ምርመራ የምስክሮች አሰማም ሂደት ላይ በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት እንደገና ክርክር እንዲደረግበት በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ መተላለፉን ተከትሎ ነው። የከፍተኛው ፍርድ ቤት ውሳኔውን ያስተላለፈው የምስክሮች አሰማም ሂደቱን በተመለከተ የተጠርጣሪ ጠበቆች ያቀረቡትን የይግባኝ አቤቱታ ከመረመረ በኋላ ነው። 

በዛሬው ውሎ በእነ አቶ ስብሃት መዝገብ የተካተቱ 42 ተጠርጣሪዎች በችሎት ፊት ቀርበው ክርክር እንዲደረግ የታዘዘ ቢሆንም ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በችሎቱ ላይ መገኘት አልቻሉም። ከተጠርጣሪዎቹ ውስጥ አቶ ስብሃትን ጨምሮ አስራ አምስቱ ብቻ በችሎት በመገኘታቸው፤ ፍርድ ቤቱ ዋናውን የክርክር ጉዳይ ወደ ጎን አድርጎ ቀሪዎቹ ተጠርጣሪዎች ያልተገኙበት ምክንያት ላይ እንዲያተኩር አድርጎታል። 

ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪዎች ለምን እንደቀሩ እንዲያስረዳ የማረሚያ ቤቱን ተወካይ ጠይቋል። ተወካዩም ለሁሉም ተጠርጣሪዎች መጥሪያ የደረሳቸው ማታ መሆኑን አስረድቶ “ግማሾቹ እምቢ ብለው ነው የቀሩት” ሲል ለፍርድ ቤት ምላሽ ሰጥቷል። በጉዳዩ ላይ ምን እንደሚሉ የተጠየቁት በችሎት የተገኙት ተጠርጣሪዎች እና ጠበቆቻቸው የመካከሪያ አፍታ ከወሰዱ በኋላ ምላሻቸውን አሰምተዋል። 

ተጠርጣሪዎቹ በጠበቆቻቸው በኩል ባቀረቡት ምላሽ የተወሰኑ ተጠርጣሪዎች በህመም ምክንያት እንደቀሩ አስረድተዋል። ሌሎችን ተጠርጣሪዎች በሚመለከት ደግሞ ስለ ችሎቱ ያልሰሙ መኖራቸው ገልጸዋል። “እኛም የሰማነው አሁን ነው” ያሉት ተጠርጣሪዎቹ፤ የታሰሩበት ክፍል የተለያየ በመሆኑ መነጋገር አለመቻላቸውንም አክለዋል።

በጉዳዩ ላይ ዐቃቤ ህግ ተቃውሞውን ለፍርድ ቤቱ አሰምቷል። በማረሚያ ቤት የሚገኙ ተከሳሾች ፍርድ ቤት ቅረቡ በተባሉበት ጊዜ የመቅረብ ግዴታ እንዳለባቸው የጠቆመው ዐቃቤ ህግ፤ “ታመዋል” ተብሎ የቀረበውን ምክንያት በተመለከተ “እነማን እንደታመሙ የደረሰን ነገር የለም” ብሏል። 

“ታምሚያለሁ ብሎ ቀርቶ ፍትህን ማዛባት ተቀባይነት የለውም” ሲልም ለፍርድ ቤቱ ተናግሯል። በተጨማሪም “የሐኪም ቤት ማስረጃ የሌለውን ተጠርጣሪ ፍርድ ቤቱ በግድ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ይስጥልን ” ሲልም ጥያቄ አቅርቧል። 

የዐቃቤ ህግን ገለጻ በጽኑ የተቃወሙት የተጠርጣሪዎቹ ጠበቃ “መጥሪያ ደርሶት፤ ቀጠሮውን አውቆ የሚቀር ተጠርጣሪ መብቱን በሚጻረር መልኩ በግድ ይቅረቡ ሊባል አይገባም” በሚል ተከራክረዋል።

የሁለቱንም ወገኖች አስተያየት ያደመው ፍርድ ቤቱ፤ ማናቸውም በህግ ጥላ ስር የሚገኙ ሰዎች ሁሉ ፍርድ ቤት መቅረብ ግዴታቸው ነው ብሏል። በመሆኑም በሀኪም ቤት የተረጋገጠ ማስረጃ ከሌላቸው ተጠርጣሪዎች በስተቀር ሌሎቹ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲቀርቡ ለማረሚያ ቤት ትዕዛዝ ሰጥቷል። ፍርድ ቤቱ የቅድመ ምርመራ ምስክሮች አሰማም ሂደትን በተመለከተ ክርክር ለማድረግ ለነገ ሐሙስ ሚያዝያ 21፤ 2013 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)