በቅድስት ሙላቱ
የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አቶ ልደቱ አያሌው ከሀገር እንዳይወጡ በፖሊስ የተላለፈውና በፍርድ ቤት ጸንቶ የነበረውን እግድ ሻረ። ፍርድ ቤቱ እግዱን ዛሬ ሐሙስ የሻረው ከፌደራል ፖሊስ እና ከኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽኖች የቀረበሉትን ምላሾች ከመረመረ በኋላ ነው።
አቶ ልደቱ ባለፈው ሚያዝያ 8፤ 2013 ለፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት አንደኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ባቀረቡት አቤቱታ፤ ከሀገር እንዳይወጡ ተብሎ የተላለፈው እግድ እንዲነሳላቸው እና ወደ ውጭ ሀገር ተጉዘው ህክምናቸውን ለመከታተል ጥያቄ አቅርበው ነበር። ጉዳዩን የተመለከተው ችሎቱ፤ እግዱን ያስተላለፈው የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ምላሹን በጹሁፍ እንዲያቀርብ ከዚህ ቀደም በነበረ ችሎት ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ትዕዛዙን ተከትሎ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አቶ ልደቱ ከሀገር እንዳይወጡ የታገዱበትን ምክንያት ያብራራበትን ምክንያት ለፍርድ ቤቱ በደብዳቤ አስገብቷል። ለፍርድ ቤቱ በተላከው ምላሽ ላይ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ደብዳቤም ተያይዞ ቀርቧል።
የሁለቱን ፖሊስ ኮሚሽኖች ምላሽ የመረመረው ፍርድ ቤቱ ዛሬ ሐሙስ ሚያዝያ 21 በዋለው ችሎቱ፤ የጉዞ እግዱን ሽሯል። ፍርድ ቤቱ እግዱን በዋነኛነት ውድቅ ያደረገው ሁለት ምክንያቶችን በመጥቀስ ነው።
የመጀመሪያው ምክንያት፤ ፖሊስ በደብዳቤው የጠቀሳቸው አቶ ልደቱ ተከስሰውባቸው በነበሩባቸው ሁለት የወንጀል ጉዳዮች ነጻ መባላቸው ነው። ተከሳሹ በኦሮሚያ ክልል በቀረቡባቸው ሁለት ክሶች ነጻ መባላቸውን ያስታወሰው ፍርድ ቤቱ፤ ከዚያ በኋላ የጉዞ እግዱ ጸንቶ የሚቆይበት ምክንያት አይኖርም ብሏል።
አቶ ልደቱ በአቤቱታቸው የጠቀሱትን የልብ ህመም በሁለተኛ ምክንያትነት ያነሳው ፍርድ ቤቱ፤ አቤት ባዩ ወደ አሜሪካ ሀገር ሄደው ባይታከሙ ሊፈጠር የሚችለውን ችግር ዳስሷል። ይህ ሁኔታም አቶ ልደቱ በህገ መንግስቱ የተሰጣቸውን በህይወት የመኖር መብት የሚጥስ እንደሆነም ጠቅሷል።
ፖሊስ በአቶ ልደቱ ላይ ያወጣው የጉዞ እግድም የግለሰቡን እንደ ልብ የመንቀሳቀስ ህገ መንግስታዊ መብት የሚገድብ መሆኑንም ፍርድ ቤቱ በተጨማሪነት አንስቷል። በእነዚህ ዋነኛ ምክንያቶችም የጉዞ እግዱ እንዲሻር የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በዛሬው የችሎት ውሎው ወስኗል። በጽህፈት ቤት በኩል በተሰየመው በዛሬው ችሎት ላይ አቶ ልደቱ አያሌው ከጠበቃቸው ጋር በአካል ቀርበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)