በእነ አቶ ስብሃት ነጋ መዝገብ የምስክሮች አሰማም ሂደት በመጪው ሳምንት ብይን ሊሰጥ ነው

በቅድስት ሙላቱ 

በእነ አቶ ስብሃት ነጋ መዝገብ የተቆጠሩ ምስክሮች የሚሰሙበትን ሂደት በተመለከተ ብይን ለመስጠት ለመጪው ሳምንት አርብ ሚያዝያ 29፤ 2013 ቀጠሮ ተሰጠ። ቀጠሮውን የሰጠው አቶ ስብሃትን ጨምሮ የ42 ተጠርጣሪዎችን የጊዜ ቀጠሮ ጉዳይ እየተመለከተ ያለው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ነው። 

ችሎቱ ዛሬ ሐሙስ ሚያዝያ 11 በነበረው ውሎው የምስክሮች አሰማም ሂደትን አስመልክቶ በዐቃቤ ህግ እና በተከሳሽ ጠበቆች መካከል ያለውን ክርክር አድምጧል። የተከሳሽ ጠበቆች የምስክሮች አሰማም ሂደቱ በዝግ ችሎት፣ ከመጋረጃ ጀርባ እና ስማቸው ሳይጠቀስ ይደረግ የሚለውን የዐቃቤ ህግ አቤቱታ ተቃውመዋል። 

ዐቃቤ ህግ ሂደቱ በሶስት መንገዶች እንዲከናወን የጠየቀው ለምስከሮች ጥበቃ አድርጊያለሁ በማለት ነው። ይህን መከራከሪያ የተቃወሙት የተከሳሽ ጠበቆች፤ በወንጀል ምስክሮች እና ጠቋሚዎች አዋጅ መሰረት የምስክሮችን ጥበቃ ለማረጋገጥ ሊሟሉ የሚገባቸው ቅድመ ሁኔታዎች አልተሟሉም ብለዋል። 

የምስክሮችን ጥበቃ በተመለከተ መጀመሪያውኑ ዐቃቤ ህግ ማመልከቻ ማቅረብ ነበረበት ያሉት የተከሳሽ ጠበቆች፤ ዐቃቤ ህግ በራሱ ጊዜ ጥበቃ አድርጊያለሁ ማለቱ አግባብ የለውም ሲሉ ተከራክረዋል። በተጨማሪም ምስክሮቹ ራሳቸው የደህንነት ስጋት እንዳለባቸው ማመልከት ነበረባቸው ብለዋል። 

በሌላ በኩል ደግሞ ተጠርጣሪዎቹ በምን እንደተከሰሱ ባልታወቀበት ሁኔታ፤ የወንጀል ምስክሮች እና ጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጅ ተፈጻሚ ሊሆን አይገባም በማለት ጠበቆቹ መከራከሪያ አቅርበዋል። ይህ አዋጅ ተፈጻሚ የሚሆነው በተጠርጣሪዎቹ ላይ ወደፊት የሚቀርበው ማስረጃ፤ ከምስክሮች ውጭ በምንም አይነት መንገድ ማስረዳት የማይቻል ከሆነ ብቻ ነው በማለትም ጠበቆቹ አብራርተዋል። 

የተከሳሽ ጠበቆች በዝግ ችሎት ምስክርን የማሰማት አካሄድንም ተቃውመዋል። ጠበቆቹ ይህ አይነቱ አካሄድ “ህገ መንግስቱን የሚፃረር ነው” ብለዋል። ለዚህ መከራከሪያቸው በማስረጃነት ያቀረቡት የተከሰሱ ሰዎችን መብት በሚመለከት በህገ መንግስቱ የተደነገገውን አንቀጽ ነው። 

ጠበቆቹ የጠቀሱት የህገ መንግስቱ አንቀጽ 20 (1) “የተከሰሱ ሰዎች ክስ ከቀረበባቸው በኋላ ተገቢ በሆነ አጭር ጊዜ ውስጥ በመደበኛ ፍርድ ቤት ለህዝብ ግልጽ በሆነ ችሎት የመሰማት መብት አላቸው” ይላል። ሆኖም የተከራካሪዎቹን የግል ሕይወት፣ የህዝብን የሞራል ሁኔታና የሀገሪቱን ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል ብቻ ክርከሩ በዝግ ችሎት ሊሰማ እንደሚችልም በዚሁ አንቀጽ ተደንግጓል። በመሆኑም በአዋጅ የተጠቀሰው የምስክሮች ጥበቃ በህገ መንግስቱ ላይ አልተጠቀሰም ሲሉ ጠበቆቹ ሞግተዋል።

ህገ መንግስቱ በመርህ ደረጃ የምስክሮች አሰማም ሂደት በግልፅ ችሎት መደንገጉን የገለጹት ጠበቆች፤ ይህ የሆነበት ምክንያትም “በማይታይ ምስክርነት ምክንያት ፍትሀዊነት እንዳይዛባ ነው” ብለዋል። በተጨማሪም ለፍርድ ቤቱ የቀረበው የምስክሮች ዝርዝር እና እየመሰከረ ያለው ሰው አንድ መሆኑን ማረጋገጥ የሚቻለው በማየት ብቻ ነው ሲሉ ተከራክረዋል። አቃቤ ህግ በአቤቱታው ከጠቀሳቸው የጥበቃ እርምጃዎች በተጓዳኝ በአዋጁ የተጠቀሱ ሌሎች የጥበቃ ሁኔታዎችን ማድረግ ይችል ነበር ሲሉም የተጠርጣሪ ጠበቆች አክለዋል።

ዐቃቤ ህግ ለፍርድ ቤቱ ባስገባው አቤቱታ ላይ ለምስክሮች ጥበቃ አድርጊያለሁ  ከማለት ውጪ ለምን ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚያስፈልግ  ዝርዝር ምክንያት አላስቀመጠም ሲሉም የተከሳሽ ጠበቆች በተጨማሪነት አንስተዋል። ከዚህ ቀደም በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በነበረ ክርክር ዐቃቤ ህግ ጥበቃ እንዲደረግላቸው የሚፈልጋቸው ምስክሮች 50 መሆናቸውን መጥቀሱን ጠበቆች አስታውሰዋል። ከእነዚህ ምስክሮች ውስጥ በዝግ ችሎት ወይም ከመጋረጃ ጀርባ የሚመሰክሩት ሁሉም አለመሆናቸውን ዐቃቤ ህግ መጠቅሱንም ገልጸዋል።   

በዛሬው የችሎት ውሎ የፍርድ ቤት ስልጣንን የተመለከተ ክርክርም ቀርቧል። ዐቃቤ ህግ በደብዳቤው ላይ የምስክሮችን ጥበቃ በተመለከተ ፍርድ ቤቱ ምንም አይነት ሚና እንደሌለው አድርጎ መጥቀሱን ያነሱት የተጠርጣሪዎች ጠበቆች፤ ይህን የህግ አተረጓጎም ተቃውመዋል። በወንጀል ምስክሮች እና ጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጅ መሰረት በሶስተኛ ወገኖች ላይ የሚደርሰውን የመብት ጥሰት የሚመረምረው ፍርድ ቤት ነው ሲሉ ጠበቆቹ ተከራክረዋል።  

ዐቃቤ ህግ ለፍርድ ቤቱ በጻፈው የአቤቱታ ደብዳቤ፤ ለምስክሮች ጥበቃ ማድረጉ እንዲታወቅለት ብቻ እንጂ የፍርድ ቤቱን ስልጣን ዕውቅና አልሰጠም ሲሉ ወንጅለዋል። አዋጁ ፍርድ ቤት ሚና የለውም ብሎ ቢያስብ ኖሮ ጥበቃው በአግባቡ መሆኑን የማረጋገጥ ኃላፊነት አይሰጠውም ነበር ያሉት ጠበቆች “ፍርድ ቤቱ ስልጣን ስሌለው ዐቃቤ ህግ ያቀረበውን ተቀብለህ አጽድቅ ብሎ ያስቀምጥ ነበር” ብለዋል። 

ተጠርጣሪዎችን ከወከሉ ጠበቆች አንዱ፤ ዐቃቤ ህግ “ምስክሮቹን እንደማባበያ እየተጠቀመባቸው እንደሆነ ሙሉ መረጃ አለኝ” ሲሉም የጥበቃ መብቱን ያላግባብ አግልግሎት ላይ መዋሉን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል። ዐቃቤ ህግ የወንጀል ምስክሮች እና ጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጅን የሚያነሳው “ጥበቃ ስለተደረገ እንዳትፈሩ እያለ ለማስመስከር ነው” ሲሉም ከስሰዋል። 

እኚሁ ጠበቃ የምስክሮቹ ማንነት በይፋ ካልታወቀ፤ የምስክሩን ማንነት አጥንተን ከዚህ ቀደም በሀሰት ምስክር የተቀጣ ይሁን አይሁን ለማረጋገጥ አንችልም ሲሉም አክለዋል። በዚህ ሁኔታ በምን መልኩ ትክክለኛ ፍትህ ይሰጣል? የሚል ጥያቄም ሰንዝረዋል። 

የምስክሮች አሰማም ሂደቱ በሚዲያ እንዳይዘገብ የሚለውን በተመለከተ የተከራከሩት ጠበቆች፤ ዐቃቤ ህግ ከዚህ ቀደም በከፍተኛ ፍርድ ቤት “ዝግ ችሎት ይሁን ያልኩት ሚዲያ ገብቶ እንዳይዘግብ ነው” ማለቱን አስታውሰዋል። ጉዳዩን ሚዲያ እንዳይዘገብ ለማድረግ፤ ግዴታ ዝግ ችሎት መሆን የለበትም የሚል መከራከሪያም አቅርበዋል። 

የጠበቆችን መከራከሪያ ተከትሎ ዐቃቤ ህግ ማስተካከያ ሊሰጥባቸው የሚገቡ፣ የህግ እና የፍሬ ነገር ክርክሮች በማለት በሶስት ከፍሎ ምላሽ ሰጥቷል። በመጀመሪያ ማስተካከያ ሊሰጥበት ይገባል ካላቸው መከራከሪያዎች ውስጥ፤ በከፍተኛ ፍርድ ቤት ያደረግነው ክርክር በትክክለኛው መንገድ አልቀረበም የሚለው አንዱ ነው። 

በመቀጠልም “50 የሚሆኑት ምስክሮች በየትኛው መንገድ እንደሚመሰክሩ አልቀረበም” የሚለው ሀሳብ “ስህተት ነው” ሲል ዐቃቤ ህግ ተከራክሯል። ይህንም ጉዳይ ሲያስረዳም ደብዳቤው የጻፈው በጥቅሉ እንደሆነ እና ፍርድ ቤቱ ደብዳቤውን ተቀብሎ ካጸደቀ በኋላ ለየትኛው ምስክር የትኛው የጥበቃ እርምጃ ተግባራዊ እንደሚሆን ወደፊት እንደሚወስን አብራርቷል። 

ከዚህ በተጨማሪም “ዐቃቤ ህግ ምስክሮቹን በዝግ ችሎት ነው የምትመሰክሩት የሚላቸው ማባበያ ለመስጠት ነው” በሚል በተከሳሽ ጠበቆች ለቀረበው ውንጀላም ምላሽ ሰጥቷል። ይህ የጠበቆች አገላለጽ በምስክሮች ላይ “ስጋት እንዳለ ማመናቸውን የሚያረጋግጥ ነው ብሏል።  

ዐቃቤ ህግ የህግ ጉዳዮችን ጠቅሶ በተከራከረበት ሀሳብም፤ የምስክሮችን ጥበቃ የመወሰን ስልጣን ለፍርድ ቤት አልተሰጠውም ብሏል። ለዚህ በማስረጃነት የጠቀሰው በወንጀል ምስክሮች እና ጠቋሚዎች አዋጅ ላይ የጥበቃ ስምምነትን የማድረግ ስልጣን ለፍርድ ቤት አልተሰጠም በሚል ነው። 

ፍርድ ቤት በዐቃቤ ህግ የቀረበለትን የምስክሮች ጥበቃ ማጽደቅም፤ መሻርም የሚችለው ከ9 እስከ 18 ዓመት ባሉ ህፃናት ላይ ብቻ ነው ሲል  ዐቃቤ ህግ ተከራክሯል። ከዚህ ውጪ ባሉት ላይ ግን ጥበቃውን እንዲያደርግ ስልጣን የሰጠው ለዐቃቤ ህግ መሆኑን በመከራከሪያው ላይ ተጠቅሷል። ለፍርድ ቤት የተሰጠው ስልጣን የምስክሮች ጥበቃ በአግባቡ ተግባራዊ መደረጉን የማረጋገጥ ስልጣን መሆኑንም በመከራከሪያው ላይ ተብራርቷል። አዋጁ ሙሉ በሙሉ ዐቃቤ ህግ ውሳኔ ላይ የተንተራሰ መሆኑንም አክሏል። 

ዐቃቤ ህግ ለምስክሮች መደረግ አለበት ያለው ጥበቃ “በአዋጁ ላይ የተጠቀሱትን ሁኔታዎች አላሟላም” በሚል ጠበቆች ያነሱትን መከራከሪያ ዐቃቤ ህግ ተቃውሟል። በክርክሩም “ጥቃት የተፈፀመው በሀገር መከላከያ ላይ ነው” ያለው ዐቃቤ ህግ ምስክርነቱ በግልጽ ቢሆን፤ በሀገር በመከላከያ ላይ ምን ያህል ጉዳት ደርሷል? የሚለው ዝርዝር ማብራሪያ በሀገር ደህንነት ላይ ጫና ይኖረዋል ሲል አብራርቷል።  

በተጠርጣሪዎቹ ከቀረቡ የወንጀል ዝርዝሮች አንዱ “ሮኬት ከመከላከያ ሠራዊት እንደተወሰደ ይጠቅሳል” ያለው ዐቃቤ ህግ፤ በችሎቱ ምን ያህል ሮኬት እንደተወሰደ፣ ምን ያህሉ እንደተተኮሱ እናስመሰክራለን ሲል ገልጿል። ይህ ሁኔታ በሚዲያ ቢዘገብ የሀገር ሚስጥር አደባባይ ይወጣል በማለት  ዐቃቤ ህግ ተከራክሯል። 

ምስክሮች ሊያጋጥማቸው የሚችልን የደህንነት ስጋት በተመለከተ ለፍርድ ቤቱ ያስረዳው ዐቃቤ ህግ፤ “ታንክ እና የጦር አውሮፕላንን የታጠቀ ተቋምን የደፈረ ቡድን፤ ለአንድ ሰው አይመለስም” ሲል የአደጋውን ተጨባጭነት አመልክቷል። ይህ ቡድን “አሁንም ያልተያዙ አባላት አሉት” ያለው ዐቃቤ ህግ፤ በትግራይ ክልል ላሉ ምስክሮች ያለው ነባራዊ ሁኔታ “ሰላማዊ ነው ብሎ ፍርድ ቤቱ ሊገምት አይችልም” ብሏል።

በጠበቆች በኩል ከተነሱት መከራከሪያዎች መካከል ዐቃቤ ህግ ሌሎች የጥበቃ እርምጃዎችን ሊወስድ ይገባ ነበር በሚል የቀረበውንም ዐቃቤ ህግ ተቃውሟል። ዐቃቤ ህግ ካሉት ከ400 በላይ ምስክሮች ለሃምሳዎቹ ብቻ ጥበቃ አድርጊያለሁ ማለቱ የሚያሳየው፤ በሌሎች ሊረጋገጥ የማይችል ነገር ግን በእነርሱ ብቻ ሊመሰከር የሚችል ፍሬ ነገር እንዳለ ነው ብሏል። በደህንነት ስጋት ምክንያት እነዚህ ምስክሮች ቀርበው መመስከር ካልቻሉ ፍትህ ይዛባል ሲል ዐቃቤ ህግ ተሟግቷል። 

ዐቃቤ ህግ ለሁሉም ምስክሮች ጥበቃ ያላደረገው በተከሳሾችም በኩል ያለውን በግልጽ ችሎት የመዳኘት መብትን ከግምት ውስጥ በማስገባት መሆኑን ገልጿል። በአጠቃላይ ፍርድ ቤቱ ሶስቱን የምስክር አሰማም ሂደቶችን በመቀበል በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ምስክር ማሰማት ሂደት እንዲገባ ዐቃቤ ህግ ጠይቋል። 

“የስጋት አጀንዳው ሰማይ ላይ የተበተነ ዱቄት ነው በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተናገሩበት ጊዜ አሁንም ስጋት አለ ማለት መሰረት የሌለው ነው”

– ከተጠርጣሪዎች ጠበቆች አንዱ በፍርድ ቤት የተናገሩት

በዐቃቤ ህግ በቀረቡት ምላሾች ላይ የተጠርጣሪ ጠበቆች የመልስ መልስ ሰጥተዋል። በመልስ መልሱ ላይም ዐቃቤ ህግ እኛ ከተከራከርንበት ወሰን በወጣ መልኩ ተከራክሯል ብለዋል። በተጨማሪም ዐቃቤ ህግ በትግራይ ክልል ያሉ ምስክሮች የደህንነት ስጋትን በተመለከተ ላነሳው መከራከሪያ “የስጋት አጀንዳው ሰማይ ላይ የተበተነ ዱቄት ነው በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተናገሩበት ጊዜ አሁንም ስጋት አለ ማለት መሰረት የሌለው ነው” ሲሉ አንድ የተጠርጣሪ ጠበቃ ተናግረዋል። 

“ሻዕቢያ አንገታችንን ይቆርጠዋል ብለው ቤታቸው ተሸሽገው የነበሩ ሰዎች በወንጀል ተጠርጥረው በቀረቡበት” ሁኔታ፤ ተጠርጣሪዎች በምስክሮች ላይ የደህንነት ስጋት ይደቅናሉ በሚል የቀረበው መከራከሪያ የማስኬድ ነው ሲሉ ጠበቃው ተከራክረዋል። ሌላ የተጠርጣሪ ጠበቃ በበኩላቸው “የዐቃቤ ህግ ዓላማ ምስክሮችን መጠበቅ ሳይሆን ማስረጃን መጠበቅ ነው” ብለዋል። 

ሰዓታት የፈጀውን የሁለቱንም ወገኖች ክርክር ያደመጠው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት መዝገቡን መርምሮ ብይን ለመስጠት ለመጪው አርብ ሚያዝያ 29 ተለዋጭ ቀጠሮ በመስጠት የዕለቱን የችሎት ውሎ አጠናቅቋል። በዛሬው ችሎት ከአቶ ጌታቸው ተፈሪ በስተቀር ሁሉም ተጠርጣሪዎች በአካል ቀርበው የችሎት ሂደቱን ተከታትለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)