በአርባ ምንጭ ከተማ በደቡብ ክልል ልዩ ኃይል አባል በተወሰደ እርምጃ የሰው ህይወት አለፈ

● በድርጊቱ በተቀሰቀሰ ግጭት አንድ አዳጊ በጥይት ተመትታ መገደሏን ነዋሪዎች ተናግረዋል 

በቅድስት ሙላቱ

በደቡብ ክልል በምትገኘው በአርባ ምንጭ ከተማ በትላንትናው ዕለት ምሽት በክልሉ ልዩ ኃይል አባል በተወሰደ እርምጃ የአንድ ወጣት ህይወት ማለፉን የከተማይቱ ነዋሪዎች እና የአካባቢው ፖሊስ አስታወቁ። በድርጊቱ በተቀሰቀሰ ግጭት አንድ አዳጊ በጥይት ተመትታ ስትገደል በሌላ አዳጊ ላይ ከባድ ጉዳት መድረሱን ነዋሪዎች ጨምረው ገልጸዋል።  

የወጣቱን ህይወት የቀጠፈው ድርጊት የተፈጸመው በአርባ ምንጭ ሲቀላ ክፍለ ከተማ፣ በድል ፋና ቀበሌ በሚገኝ አንድ ግሮሰሪ ውስጥ ትላንት እሁድ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ገደማ እንደሆነ የጋሞ ዞን ፖሊስ መምሪያ የመረጃ ክፍል ባለሙያ ሳጅን ሙሉነህ ሽፈራው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የጉዳዩ መነሻም በአካባቢው ወጣቶች መካከል የተፈጠረ አለመግባባት እንደሆነ አስረድተዋል። 

በግሮሰሪው ውስጥ የሲቪል ልብስ ለብሶ በመዝናናት ላይ የነበረ አንድ የክልሉ ልዩ ኃይል አባል እንደነበር የሚናገሩት ሳጅን ሙሉነህ፤ በወጣቶቹ መካከል የተፈጠረውን ጠብ ለመገላገል በመሃል መግባቱን ያስረዳሉ። የልዩ ኃይል አባሉ እርምጃውን የወሰደውም ወጣቶቹ ተሰብስበው ጉዳት ሊያደርሱበት ስለነበር ነው ባይ ናቸው። “ቡድን ፈጥረው ሊደበድቡት ሲሉ ራሱን ለመከላከል በተኮሰው ጥይት አንድ ሰው ተመቷል” ሲሉም ድርጊቱ መፈጸሙን አረጋግጠዋል።  

ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አንድ የአካባቢው ነዋሪ፤ የልዩ ኃይል አባሉ እንደተባለውም ወጣቶችን ለመገላገል ሲሞክር ነበር ብለዋል። ድርጊቱ በተፈጸመበት “ኒው ሆፕ” ግሮሰሪ በነበሩ ወጣቶች መካከል አለመግባባቱ የተቀሰቀሰው በሴት አስተናጋጆች ምክንያት እንደነበርም ያስረዳሉ። 

ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ከምሽቱ 12 ሰዓት ተኩል ገደማ ወደ ግሮሰሪው የዘለቀው ሟች፤ ሴት አስተናጋጆችን አላግባብ ተናግረዋል ያላቸውን ሌሎች ተስተናጋጆችን ለምን ይህን እንደሚያደርጉ በመጠየቁ ምክንያት አለመግባባት መፈጠሩን ይገልጻሉ። ወጣቶቹ እርስ በእርስ መደባደብ ሲጀምሩ፤ እዚያው እየተዝናና የነበረው የልዩ ኃይል አባል በመካከላቸው ገብቶ “እረፉ” ሲል እንደነበርም እኚሁ ነዋሪ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

የልዩ ኃይል አባሉ በመጀመሪያ ወደ ላይ መተኮሱን የሚናገሩት ነዋሪው፤ “ወጣቶቹ ጠርሙስ ሲያነሱ የልዩ ኃይሉ አባሉ የሟችን ዓይን በሽጉጥ ተኩሶ መታው” ሲሉ በወቅቱ የተከሰተውን ያብራራሉ። እርሳቸውን ይህን ይበሉ እንጂ ሌላ የአካባቢው ነዋሪ ግን ለድርጊቱ የልዩ ኃይል አባላትን ተጠያቂ ያደርጋሉ።   

ድርጊቱ ሲፈጸም በአካባቢው ነበርኩ የሚሉት አቶ ዘሪሁን አረዴ የተባሉ የከተማይቱ ነዋሪ፤ ነገሩ የተከሰተው ግድያውን የፈጸመው የልዩ ኃይል አባል ከሌሎች ሁለት አባላት ጋር በመሆን ከመጠን ያለፈ ስካር ላይ ስለነበሩ ነው ሲሉ ይወነጅላሉ። የልዩ ኃይል አባላቱ “መጠጥ በወጣቶች ላይ ሲደፉ ነበር” የሚሉት አቶ ዘሪሁን፤ ከሟች ጋር በነበረ አለመግባባት ምክንያት አንደኛው የልዩ ኃይል አባል ወጣቱን  በግንባሩ ላይ ሶስት ጊዜ በጥይት ተኩሶ እንደገደለው ይከስሳሉ። 

ይህን መሰሉ በታጠቁ የፖሊስ አባላት የሚፈጸሙ ግድያዎች በአካባቢው በተደጋጋሚ እንደሚስተዋሉ የሚገልጹት ነዋሪው፤ የድርጊቱ ፈጻሚዎች ላይ የሚወሰድ ህጋዊ እርምጃ የለም ሲሉ ያማርራሉ። የትላንቱ ግድያ ከተፈጸመ በኋላም “ምንም በቁጥጥር ስር የዋለ ሰው የለም” ሲሉ አቶ ዘሪሁን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

ይህንን የአካባቢውን ነዋሪ ገለጻ፤ የጋሞ ዞን ፖሊስ መምሪያ አስተባብሏል። በፖሊስ መምሪያው የመረጃ ክፍል ባለሙያ ሳጅን ሙሉነህ በግድያው የተጠረጠረው የልዩ ኃይል አባል ትላንቱኑ በቁጥጥር ስር ውሏል ብለዋል። ተጠርጣሪው በአሁኑ ወቅትም በሴቻ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ እንደሚገኝም ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። 

በደቡብ ክልል የልዩ ኃይል አባል በጥይት የተመታው ወጣት ወደ ሆስፒታል ቢወሰድም እዚያው እንደደረሰ ህይወቱ ማለፉን የሚናገሩት ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁት የአካባቢው ነዋሪ፤ ከዚያ በኋላ በስፍራው በተፈጠረ ግርግር የተጨማሪ ሰው ህይወት ማለፉን ገልጸዋል። ከወጣቱ በጥይት መመታት በኋላ ወጣቶች በቦታው ተሰብስበው ነበር የሚሉት እኚሁ ነዋሪ፤ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ገደማ አንድ የፖሊስ ፓትሮል መኪና ወደ አካባቢው ከመጣ በኋላ ግጭት መቀስቀሱን አብራርተዋል።  

በፖሊሶች እና በአካባቢው ወጣቶች መካከል በተነሳው በዚሁ ግጭት ሁለት አዳጊዎች በጥይት መመታታቸውንም ተናግረዋል። ፖሊስ ወደ ላይ ለመተኮስ ሲል የ14 እና የ15 አዳጊዎችን በጥይት እንደመታቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተናገሩት ነዋሪው፤ በዚህም የ14 ዓመቷ ልጅ ህይወቷ አልፏል ብለዋል። “አንደኛዋ በኩላሊቷ ላይ ጉዳት ደርሶባት አርባ ምንጭ ሆስፒታል ገብታለች” ሲሉም አክለዋል።

ድርጊቱ በተፈጸመበት በድል ፋና ቀበሌ ዛሬ ውጥረት ነግሶ እንደዋለ ሌላኛው የአካባቢው ነዋሪ አቶ ዘሪሁን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። ፖሊስ በአካባቢው ባጃጅ እና ሞተር ሳይክል እንዳያልፍ መከልከሉንም ገልጸዋል።

የሁለቱን አዳጊዎች ሁኔታ በተመለከተ ጥያቄ የቀረበላቸው የጋሞ ዞን ፖሊስ መምሪያ የመረጃ ክፍል ባለሙያ፤ ስለ ጉዳዩ ምንም አይነት መረጃ የለኝም ብለዋል። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የአርባ ምንጭ ከተማ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዩች ጽህፈት ቤት ባልደረባዎችን እና ጉዳዩን እየተከታተሉ የሚገኙ የፖሊስ አባላትን ለማነጋገር ሙከራ ብታደርግም፤ ጉዳዩ ገና በመጣራት ላይ እንደሆነ በመግለጽ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ታቅበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)