የአውሮፓ ህብረት ለመጪው የኢትዮጵያ ምርጫ ታዛቢዎች እንደማይልክ አስታወቀ

የአውሮፓ ህብረት ለስድስተኛው የኢትዮጵያ አጠቃላይ ምርጫ ታዛቢ ለመላክ የያዘውን እቅድ ሰረዘ። ህብረቱ ግንቦት 28፤ 2013 ለሚደረገው ብሔራዊ ምርጫ ታዛቢዎች ለመላክ በቁልፍ መለኪያዎች ረገድ ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር ከስምምነት መድረስ እንዳልቻለ ትናንት ሰኞ ምሽት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። 

በ74 አመቱ ስፔናዊ ጆሴፕ ቦሬል የሚመራው የአውሮፓ ህብረት የውጭ ግንኙነት ቢሮ ባወጣው መግለጫ እንዳለው “ሁኔታዎች ባለመሟላታቸው የምርጫ ታዛቢ ልዑክ የመላክ ዕቅዱ ተሰርዟል።” የአውሮፓ ህብረት የምርጫ ታዛቢ ለመላክ “መሠረታዊ መስፈርቶች” ካላቸው እና ዕቅዱን ለመሰረዝ ካስገደዱት ጉዳዮች መካከል “የተልዕኮው ገለልተኝነት” አንዱ ነው።

ሁለተኛው ምክንያት የምርጫ ታዛቢ ተልዕኮው የመገናኛ ስርዓት (communication systems) ወደ ኢትዮጵያ ማስገባት መከልከሉ ነው። ይህ ስርዓት “በተለይ ፈታኝ የጸጥታ ከባቢ ባለበት ሁኔታ” ለአውሮፓ ህብረት የምርጫ ታዛቢዎች ደህንነት ቁልፍ ነው ተብሎለታል። 

ጆሴፕ ቦሬል ከሁለት ሳምንታት ገደማ በፊት በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ይበልጥ እየተበላሸ ካልመጣ በስተቀር ህብረቱ ምርጫውን የሚታዘብ ልዑክ እንደሚልክ ጥቆማ ሰጥተው ነበር። “በመጪዎቹ ቀናት የምርጫ ታዛቢ ለመላክ ያለንን ፍላጎት ለማረጋገጥ ሁኔታውን በቅርበት እንከታተላለን” ሲሉ በወቅቱ የተናገሩት ጆሴፕ ቦሬል፤ የኢትዮጵያ መንግስት በአንጻሩ ከምርጫው በፊት ለብሔራዊ ውይይት ሂደት መስማማት እንደሚኖርበት ገልጸው ነበር። 

ከዚህ ቀደም ለሁለት ምርጫዎች በመንግሥት ግብዣ መሠረት ታዛቢዎች የላከው የአውሮፓ ህብረት፤ “ለኢትዮጵያ ሕዝብ የዴሞክራሲ መሻት በግልጽ የሚታይ ድጋፍ ለማቅረብ የሚያስፈልገውን ማረጋገጫ ሳያገኝ መቅረቱ አሳዛኝ ነው” ብሏል። በኢትዮጵያ ለአራተኛ ጊዜ በግንቦት 15፤ 2002 የተካሄደውን ምርጫ ከ150 በላይ አባላት ያሉት የአውሮፓ ህብረት ልዑክ መታዘቡ አይዘነጋም። ይህን ልዑክ የመሩት ታይሽ ቤርማን የተባሉ የኔዘርላንድስ ፖለቲከኛ ነበሩ።  

የአውሮፓ ህብረት የምርጫ ታዛቢዎች ልዑክ በኢትዮጵያ ምርጫ ላይ ከፍተኛ ሚና የነበረው በ1997 ዓ.ም በተካሄደው አጠቃላይ ምርጫ ወቅት ነው። በፖርቹጋላዊቷ ፖለቲከኛ አና ጎሜዝ የተመራው የታዛቢዎች ልዑኩ በበርካታ የኢትዮጵያ ቦታዎች ተንቀሳቅሶ ምርጫውን ታዝቧል። ልዑኩ ከምርጫው በኋላ ያወጣው ጠንከር ያለ ሪፖርት በገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ባለስልጣናት ከፍተኛ ነቀፌታ የተሰነዘረበት ነበር። 

የአውሮፓ ህብረት በዘንድሮው ምርጫ ታዛቢዎቹን እንደማይልክ ቢያስታውቅም፤ የምርጫውን ተዓማኒነት፣ አካታችነት እና ግልጽነት ለማረጋገጥ ከዚህ ቀደም ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ20 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ አቅርቧል። ህብረት በትላንት ምሽት መግለጫው ሁሉም ኢትዮጵያውያን ህጋዊ የፖለቲካ እና የሲቪክ መብቶቻቸውን እንዲጠቀሙ ለማረጋገጥ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጥረታቸውን እንዲጨምሩ ጥሪ አቅርቧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)