የመራጮች ምዝገባ እስካሁን ባልተጀመረባቸው ቦታዎች ምዝገባ “በልዩ ሁኔታ” ሊደረግ ነው

በተስፋለም ወልደየስ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመራጮች ምዝገባ እስካሁን ባልተጀመረባቸው ቦታዎች ምዝገባው “በልዩ ሁኔታ” እንዲከናወን ውሳኔ አሳለፈ። የመራጮች ምዝገባ በልዩ ሁኔታ እንዲከናወን ውሳኔ የተላለፈላቸው ቦታዎች በኦሮሚያ፣ አማራ እና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የሚገኙ ናቸው። 

ምርጫ ቦርድ ዛሬ ማክሰኞ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው በሶስቱ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ ቦታዎች የመራጮች ምዝገባ የሚደረገው ከመጪው ሚያዝያ 29 ጀምሮ ባለው የሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ነው። በሶስቱ ክልሎች የሚገኙት እነዚህ ቦታዎች በጸጥታ ችግር ምክንያት ምዝገባውን እስካሁን ድረስ ማከናወን ያልቻሉ ናቸው። 

በልዩ ሁኔታ የሚካሄደው የመራጮች ምዝገባ ተግባራዊ ከሚደረግባቸው አካባቢዎች ውስጥ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚገኙት አራቱ የወለጋ ዞኖች ይገኙበታል። በቦርዱ ውሳኔ መሰረት በምዕራብ ወለጋ ዞን፤ ከቤጊ እና ሰኞ ገበያ የምርጫ ክልል ውጪ፤ የመራጮች ምዝገባ የሚካሄደው ልዩ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ነው። ከአያና እና ገሊላ የምርጫ ክልል ውጪ በሚገኙ የምስራቅ ወለጋ ዞን የምርጫ ጣቢያዎችም የመራጮች ምዝገባ በተመሳሳይ ሁኔታ ይካሄዳል።

የሆሩ ጉድሩ ዞንም እንደ ምዕራብ እና ምስራቅ ወለጋ ዞኖች ሁሉ ሶስት የምርጫ ክልሎቹ በልዩ የጊዜ ሰሌዳው አልተካተቱም። በመጪዎቹ ሁለት ሳምንታት በሆሩ ጉድሩ ዞን ምዝገባ የማይካሄድባቸው አሊቦ፣ ጊዳም እና ኮምቦልቻ የምርጫ ክልሎች መሆናቸውን ምርጫ ቦርድ በዛሬው መግለጫው ጠቁሟል። ከሶስቱ የወለጋ ዞኖች በተለየ እስከ ግንቦት 13፤ 2013 በሚቆየው ጊዜ በሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች ምዝገባ የሚያከናውነው የቄለም ወለጋ ዞን መሆኑን የቦርዱ መግለጫ ያመለክታል።

በአማራ ክልል ከሚገኙ የምርጫ ክልሎች ውስጥ በጸጥታ ችግር ምክንያት የመራጮች ምዝገባ ማከናወን ያልቻሉትና በኦሮሞ ልዩ ዞን የሚገኙ ሶስት የምርጫ ክልሎች በልዩ የምዝገባ የጊዜ ሰሌዳው እንዲካተቱ ተደርገዋል። በዞኑ ስር ያሉት እነዚህ የምርጫ ክልሎች የሚገኙት በዳዋ ጨፌ፣ ጨፋ ሮቢት እና ባቲ በተሰኙ ቦታዎች መሆኑን ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የልዩ የምዝገባ ሰሌዳው ተፈጻሚ የሚሆነው፤ በካማሺ ዞን በሚገኙ አራት የምርጫ ክልሎች እንደሆነ የቦርዱ መግለጫ ያሳያል። ታጣቂዎች በቅርቡ ተቆጣጥረዋት እንደነበር በተነገረላት በካማሺ ዞን ስር በምትገኘው የሴዳል ወረዳ ግን በተጠቀሰው ጊዜ የመራጮች ምዝገባ እንደማይከናወን በቦርዱ መግለጫ ተብራርቷል።  

ምርጫ ቦርድ፤ ከሶማሌ እና አፋር ክልሎች ውጪ ባሉ እና የጸጥታ መደፍረስ ባልተስተዋለባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች፤ የመራጮች ምዝገባን በሁለት ሳምንት መራዘሙ ይታወሳል። የተራዘመው የመራጮች ምዝገባ ጊዜ የሚጠናቀቀው ከሁለት ቀናት በኋላ በመጪው አርብ ሚያዝያ 29፤ 2013 ነው። 

የምርጫ ጣቢያዎች በበዓል ቀናት ከመዘጋታቸው አስቀድሞ፤ እስካለፈው ሳምንት ሐሙስ ሚያዝያ 21 ድረስ፤ የተመዘገቡ አጠቃላይ መራጮች ብዛት 26.1 ሚሊዮን መድረሱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጿል። ከተመዘገቡት መራጮች መካከል 1.4 ሚሊዮን ያህል የሚሆኑት በአዲስ አበባ የሚገኙ መሆናቸውን ቦርዱ አስታውቋል። 

ምርጫ ቦርድ ከአንድ ሳምንት በፊት ባወጣው መረጃ እስከ ሚያዝያ 14 ባለው ጊዜ 18,427,239 መራጮች መመዝገባቸውን ይፋ አድርጎ ነበር። ይህ መረጃ ከተለቀቀበት ጊዜ አንስቶ ባለው አንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ለመምረጥ የተመዘገቡ ሰዎች ቁጥር ወደ ስምንት ሚሊዮን ይጠጋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)