በቅድስት ሙላቱ
የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ የሚካሄደውን ስድስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ ላለመታዘብ ያስተላለፈውን ውሳኔ መልሶ እንዲያጤነው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጠየቀ። ምክር ቤቱ፤ የአውሮፓ ህብረት እስካሁን የተደረጉትን የይስሙላ ምርጫዎችን ሲታዘብ ኖሮ በዘንድሮው ምርጫ ከታዛቢነት ለመውጣት የወሰነበት ምክንያትን ለኢትዮጵያ ህዝብ ሊያሳውቅ ይገባል ብሏል።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ይህን ያለው ዛሬ አርብ ሚያዝያ 29 በጽህፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ የሚደረገውን ምርጫ እንዲታዘብ ጥልቅ ፍላጎት እንዳለው የገለጸው ምክር ቤቱ፤ ህብረቱ ምርጫውን ላለመታዘብ የያዘውን አቋም በድጋሚ ተመልክቶ ታዛቢዎቹን እንዲልክ አሳስቧል።
የኢትዮጵያ መንግስትም አሁን የያዘውን አቋም ከዓለም አቀፍ የምርጫ ታዛቢነት ህጎች ጋር በማገናዘብ፤ ጉዳዩን መልሶ በድርድር እንዲመለከተው ምክር ቤቱ ጥሪ አቅርቧል። ድርድሩ መደረግ ያለበትም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በማይጻረር መልኩ መሆኑንም አክሏል።

የአውሮፓ ህብረት ባለፈው ሰኞ ባወጣው መግለጫ፤ በመጪው ግንቦት ወር በኢትዮጵያ በሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ላይ ታዛቢዎችን ለመላክ የያዘውን እቅድ መሰረዙን አስታውቆ ነበር። ህብረቱ እቅዱን የሰረዘው የምርጫ ታዛቢዎችን ለመላክ በቁልፍ መለኪያዎች ረገድ ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር ባለመስማማቱ መሆኑን ገልጿል።
ውሳኔውን በተመለከተ የኢትዮጵያን አቋም የገለጹት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቃባይ ዲና ሙፍቲ፤ ህብረቱ ምርጫውን ላለመታዘብ በምክንያቶች የጠቀሳቸው ጉዳዮች “የኢትዮጵያን ነጻነት፣ ሉዓላዊነት እና ደህንነት የሚጻረር ነው” ማለታቸው ይታወሳል። በኢትዮጵያ በኩል የተነሳው የሉዓላዊነት ጥያቄ በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይም አነጋግሯል።

መግለጫውን ከታደሙ ጋዜጠኞች “በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት አንደራደርም እየተባለ የአውሮፓ ህብረት ምርጫውን መዳኘት አለበት ማለታችሁ እርስ በእርሱ አይጣረስም ወይ?” የሚል ጥያቄ ተነስቷል። ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ዶ/ር ራሔል ባፌ ምላሽ፤ የኢትዮጵያ መንግስት ምክንያቱ ምን እንደሆነ በግልጽ ያሳወቀው ነገር የለም ብለዋል። የኢትዮጵያ መንግስት ከአውሮፓ ህብረት ጋር ተነጋግሮ ያልተስማማባቸውን ጉዳዩች በግልፅ ሪፖርት እንዲያቀርብላቸው እንደሚጠይቁም ጨምረው ገልጸዋል።
የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ገብሩ በርሔ፤ ሁለቱንም አካላት በጋራ ወይም በተናጠል የመጠየቅ ውሳኔ የተላለፈው የጋራ ምክር ቤቱ በዚህ ሳምንት ባካሄደው ጉባኤ እንደሆነ አብራርተዋል። “የሁለቱንም ሃሳብ ካገኘን በኋላ ጥፋተኛ በሆነው አካል ላይ action እንወስዳለን” ብለዋል።
“እንደ ሀገር የኢትዮጵያን ህዝብ ወክለን ነው አውሮፓ ህብረትን የምንጠይቀው። እኛ ኃላፊነታችንን እየተወጣን ነው። የመቀበል እና ያለመቀበል ጉዳይ ግን የእነሱ ነው”
አቶ ገብሩ በርሔ – የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ
የምክር ቤቱን ውሳኔ ተቀባይነት የተጠየቁት አቶ ገብሩ “እንደ ሀገር የኢትዮጵያን ህዝብ ወክለን ነው አውሮፓ ህብረትን የምንጠይቀው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። “እኛ ኃላፊነታችንን እየተወጣን ነው። የመቀበል እና ያለመቀበል ጉዳይ ግን የእነሱ ነው” ሲሉም አክለዋል።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፤ የአውሮፓ ህብረት ምርጫውን ላለመታዘብ የያዘውን አቋም አጠናክሮ የሚቀጥል ከሆነ ገዢው ፓርቲ እንደከዚህ ቀደሞ አጭበርብሮ ማለፍ ሳይሆን፤ ምርጫው ነጻ እና ፍትኃዊ መሆኑን የማረጋገጥ ኃላፊነት አለበት ሲል በመግለጫው አሳስቧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)