የእነ እስክንድር ነጋ የምስክሮች አሰማም ሂደት በስር ፍርድ ቤት በድጋሚ ክርክር እንዲደረግበት ተወሰነ

በቅድስት ሙላቱ

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በእነ አቶ እስክንድር ነጋ መዝገብ የተጠየቀውን የምስክሮች አሰማም ሂደት፤ የስር ፍርድ ቤት እንደገና እንዲመለከተው ውሳኔ አስተላለፈ። ውሳኔውን ያስተላለፈው ዛሬ ማክሰኞ ግንቦት 4 ያስቻለው ሁለተኛ የወንጀል ይግባኝ ሰሚ ችሎት ነው።

የምስክሮች አሰማም ሂደት በዝግ ችሎት እና ከመጋረጃ ጀርባ ይሁን በማለት ዐቃቤ ህግ ባቀረበው ይግባኝ ላይ ሁለቱንም ወገኖች ያከራከረው ችሎቱ፤ በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረው ለሚያዝያ 26፤ 2013 ነበር። በዕለቱ በነበረው የችሎት ውሎ መዝገቡ ተመርምሮ አለማለቁን ያሳወቀው ፍርድ ቤቱ፤ ለዛሬ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። 

ፍርድ ቤቱ በዛሬው ውሎው፤ ዐቃቤ ህግ ለምስክሮች ጥበቃ አድርጊያለሁ በማለቱ የምክሮች አሰማም ሂደቱ በዝግ ችሎት እና ከመጋረጃ ጀርባ እንዲደረግ ያቀረበውን ይግባኝ መመርመሩን ገልጿል። ዐቃቤ ህግ ካቀረባቸው ምስክሮች ውስጥ 16 ያህሉ በዝግ ችሎት እንዲመሰክሩ፤ ሌሎች አምስት ምስክሮች ደግሞ ከመጋረጃ ጀርባ የምስክርነት ቃላቸውን እንዲሰጡ በይግባኙ ጠይቋል። 

ይግባኙን የመረመረው ፍርድ ቤቱ፤ ዐቃቤ ህግ ከዚህ በፊት ባደረገው የቃል ክርክር ላይ፤ በምስክሮች ጥበቃ ጉዳይ ላይ ለመወሰን ፍርድ ቤት ስልጣን የለውም ማለቱን እንደ አንድ ጭብጥ ይዞታል። ፍርድ ቤቱ ይህን ጭብጥ ከኢፌዲሪ ሕገ መንግስት፣ ከወንጀል ምስክሮችና ጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጅ እንዲሁም ከተለያዩ አለማቀፍ ህጎች ጋር አገናዝቧል። 

በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 20 ላይ ተከሳሾች በግልፅ ችሎት የመዳኘት መብታቸው በመርህ ደረጃ እንደተቀመጠ የጠቀሰው ፍርድ ቤቱ፤ በልዩ ሁኔታ ግን ይህ መብት የሚገደብበትን አግባብ ፍርድ ቤት እንደሚወስን አጠያያቂ አለመሆኑን ገልጿል። በመቀጠልም በወንጀል ምስክሮች እና ጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጅ ስር ለዐቃቤ ህግ ብቻ የተሰጡ ስልጣኖችን እና ለፍርድ ቤት ቀርበው መወሰን ያለባቸውን ጉዳዮች ፍርድ ቤቱ ለይቷል። 

በአዋጁ አንቀፅ 4/1 ስር የተዘረዘሩት የአካል እና የንብረት ጥበቃ፣ የመኖሪያ ስፍራ እና ማንነትን መቀየር እንደዚሁም ባለንብረትነትን መደበቅ የሚሉት የምስክር ጥበቃ አይነቶች፤ የፍርድ ቤት ጣልቃ ገብነት ሳያስፈልግ ለዐቃቤ ህግ የተሰጡ ስልጣኖች መሆናቸውን ችሎቱ አመልክቷል። ነገር ግን በዚሁ አንቀጽ ስር የተጠቀሱት በዝግ ችሎት እና ከመጋረጃ ጀርባ የሚደረጉ የአሰማም ሂደቶች፤ ዐቃቤ ህግ ለፍርድ ቤት ማመልከቻ አቅርቦ ፍርድ ቤቱም እንደ አግባብነታቸው የሚወስናቸው መሆኑን ችሎቱ አብራርቷል። 

ይሁን እንጂ አዋጁ ፍርድ ቤት በምን አይነት መንገድ መመርመር እንዳለበት ዝርዝር ድንጋጌ ባለማስቀመጡ ምክንያት፤ ይህንን ለመበየን “የህግ ትርጓሜ ያስፈልገዋል” ብሏል። በመሆኑም በምስክሮች አሰማም ሂደት ላይ የፍርድ ቤትን ስልጣን በሚመለከት ችሎቱ የህግ ትርጓሜ ሰጥቷል። 

በትርጓሜውም የፍርድ ቤቶች የስረ-ነገር ስልጣን (judicial power) በሁለት ተከራካሪ ወገኖች የሚቀርቡትን መከራከሪያዎች መርምሮ አግባብ ያለውን ውሳኔ መስጠት እንጂ ከአንድ ወገን ብቻ የቀረበን አቤቱታ ተቀብሎ ማፅደቅ አይደለም በማለት ችሎቱ በውሳኔው ላይ አትቷል። የወንጀል ስነ ስርአት ህግን በተጨማሪ አስረጂነት የጠቀሰው ፍርድ ቤቱ፤ የተከሳሾችን መብት በማይጣረስ መልኩ የመተግበር ስልጣን ለፍርድ ቤት የተሰጠ ነው በማለት ወስኗል። 

በመሆኑም ፍርድ ቤት የተከሳሾችን መብት እና የምስክሮችን ጥበቃ በበቂ ምክንያት አመዛዝኖ የመወሰን ስልጣን አለው በማለት ዐቃቤ ህግ ከዚህ ቀደም ያቀረበው መከራከሪያ “የፍርድ ቤቱን ሚና ያላገናዘበ ነው” በማለት ውድቅ አድርጎታል። ይህንን ተከትሎም ዐቃቤ ህግ በምስክሮች ላይ የሚደርሱ ስጋቶችን ዘርዝሮ አቤቱታውን ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንዲያቀርብ ችሎቱ ወስኗል።

የስር ፍርድ ቤትም ተጨባጭ ስጋት መኖሩ እና አለመኖሩን መርምሮ ተገቢውን ብይን እንዲሰጥ ሲልም ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል። ችሎቱ በመጨረሻም ምስክሮች ቃላቸውን የሚሰጡበት ሂደት በተቻለ ፍጥነት እንዲጀመር ወደ ፍሬ ነገር ክርክር እንዲገባ ውሳኔ አስተላልፏል።

በዛሬው የችሎት ውሎ እስክንድር ነጋን ጨምሮ በእስር ላይ የሚገኙት አራት የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ አመራሮች በአካል አልተገኙም። ተከሳሾቹ ፍርድ ቤቱ በጉዳዩ ላይ ሁለቱንም ወገኖች ባከራከራበት ወቅት በፕላዝማ ቴሌቪዥን የችሎት ውሎውን የመከታተል ዕድል አግኝተው የነበረ ቢሆንም ዛሬ ግን በዚህ የመገናኛ ዘዴም ሳይቀርቡ ቀርተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)