የባልደራስ የአዲስ አበባ ማኒፌስቶ ምን ይዟል?

በሃሚድ አወል

በመጪው ምርጫ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ የሚወዳደረው ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ፤ ለከተማይቱ ያዘጋጃቸውን አበይት የፖሊሲ አቅጣጫዎች የተነተነበትን ሰነድ በትላንትናው ዕለት ይፋ አድርጓል። በ120 ገጾች የተዘጋጀው የከተማይቱ ማኒፌስቶ፤ ፓርቲው ባለፈው መጋቢት ወር ለህዝብ ይፋ ባደረገው የምርጫ ማኒፈስቶ ላይ የተመሰረተ መሆኑ ተገልጿል። 

“ይህ የአዲስ አበባ ከተማ ማኒፌስቶ ፓርቲያችን የህዝብ ውክልና ቢያገኝ በከተማዋ ሁለንተናዊ ለውጥ እና ልማት ረገድ የሚከተላቸውን የፖሊሲ አቅጣጫዎች በስፋት እና በጥልቀት የሚተነትን ነው” ሲል ባልደራስ በማኒፌስቶው መግቢያ ላይ አመልክቷል። አዲሰ አበባ የተጋረጡባት ዘርፈ ብዙ ችግሮች እና ተግዳሮቶች “ስርዓት ወለድ ናቸው” ብሎ የሚያምነው ባልደራስ፤ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የሚከተላቸውን ፖሊሲዎች ስትራቴጂዎች እና ስልቶች በማኒፌስቶው ላይ በዝርዝር አቅርቧል። 

ፓርቲው በሰነዱ ላይ የፖሊሲ አቅጣጫዎቹን በዝርዝር ያስቀመጠው በስድስት ንዑስ ክፍሎች ከፋፍሎ ነው። ከእነዚህ ንዑስ ክፍሎች ቀዳሚ ቦታ የተሰጠው የህጋዊ እና አስተዳደራዊ መዋቅሮች ጉዳይ ሲሆን በዚህ ስር ባልደራስ በዋነኛነት ከሚያቀነቅናቸው ጉዳዮች አንዱ የሆነው የአዲስ አበባ የራስ ገዝነት ጥያቄ ተካትቷል። ፓርቲው ትላንት ባሰራጨው የከተማይቱ ማኒፌስቶ የጀርባ ሽፋን ላይ ጭምር ይህንን የራስ ገዝ አስተዳደር ጉዳይ በመፈክር መልክ አትሟል። 

ባልደራስ አዲስ አበባ በንጉሱ፣ በደርግ እና በኢህአዴግ የሽግግር ወቅት ወደ ነበረችበት የራስ ገዝ የአስተዳደር ደረጃ ልትመለስ ይገባል የሚል ጽኑ አቋሙን በማኒፌስቶው አንጸባርቋል። የከተማይቱ የይዞታ ዳር ድንበርም ከ1987 በፊት ወደ ነበረው የ122 ሺህ ሄክታር ይዞታ መመለስ እንደሚኖርበትም ፓርቲው ይሟገታል። 

ይህንኑ የፓርቲውን አቋም፤ ባልደራስን ወክለው በአዲስ አበባ አራዳ ክፍለ ከተማ ለምርጫ የሚወዳደሩት አቶ ሳምሶን ገረመው በማኒፌስቶው ይፋ ማድረጊያ ስነ ስርዓት አጽንኦት ሰጥተው አንስተውታል። “አዲስ አበባ አስቀድሞም ቢሆን ራሷን የቻለች እና ራስ ገዝ አስተዳደር ነች” የሚሉት አቶ ሳምሶን፤ ከተማዋ 50 በመቶ የሚሆነው ይዞታዋ በኦሮሚያ ክልል ስር እንዲካለል በመደረጉ ቀድሞ የነበራት የቆዳ ስፋት እንዲያንስ መደረጉን በቁጭት ይጠቅሳሉ። 

የአዲስ አበባ ነባር ይዞታ “መቀማት”ን ጉዳይ በማኒፌስቶው ፖለቲካዊ እና አስተዳደራዊ ተግዳሮቶች ማዕቀፍ ስር የተነተነው ባልደራስ፤ በተመሳሳይ ንዑስ ክፍልም ከተማይቱ ከሕገ መንግስቱ ጋር በተያያዘ አጋጥሟታል ያለውን ችግር ዳስሷል። ፓርቲው ህገ መንግስቱ ለአዲስ አበባ ነዋሪ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ቢሰጥም፤ ለክልሎች፣ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች የተሰጠው የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ግን የከተማይቱ ነዋሪዎች አለማግኘታቸውን ይጠቅሳል።  

ከዚህ መብት ባሻገርም የአዲስ አበባ አስተዳደር ተጠሪነት ለፌደራል መንግስቱ መሆን እና ከተማይቱ በፌደሬሽን ምክር ቤት ውስጥ ውክልና ማጣቷ ሌሎቹ የሕገ መንግስት ችግሮች ናቸው በሚል በማኒፌስቶው ላይ ተነስተዋል። ይህ አካሄድ የአዲስ አበባን ነዋሪ “በሀገሪቱ ወሳኝ ጉዳይም ሆነ በከተማዋ ጉዳይ ላይ ባይተዋር ያደርገዋል” ሲል ፓርቲው በማኒፌስቶው ተችቷል።

“ይህም በመሆኑ አዲስ አበባ (አዲስ አበቤ) በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 62 ላይ የተዘረዘሩትን እንደ ህግ መተርጎም፣ የራስን ዕድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል መብት የመወሰን፣ በክልሎች መካከል በሚደረግ አለመግባባት ላይ መፍሔ የመስጠት፣ የፌደራል መንግስቱ ጣልቃ እንዲገባ የማዘዝ ስልጣን የመሳሰሉት ተሳትፎ የለውም፤ ተጠቃሚም አይደለም” በማለትም የከተማይቱ ነዋሪዎች በሕገ መንግስቱ ምክንያት ተነፍገዋቸዋል ያላቸውን መብቶች እና ስልጣኖች ዘርዝሯል። 

በማኒፌስቶው በፖሊሲ አቅጣጫነት ከተቀመጡት ውስጥ የመሰረተ ልማትና ህዝባዊ ግልጋሎቶችን በሚመለከተው ንዑስ ክፍል ስር፤ ፓርቲው በከተማይቱ በጉልህ የሚስተዋለውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ ሊተገብራቸው ያቀዳቸውን ሁለት የመፍትሄ አማራጮች አስቀምጧል። የመጀመሪያው የፓርቲው አማራጭ ከተማዋን በአዲስ መልክ አፍርሶ መገንባት እና ሌሎች አማራጭ ከተሞችን መመስረት የሚል ነው። 

ፓርቲው በሁለተኛነት ያቀረበው መፍትሔ ደግሞ፤ የከተማዋ ነዋሪዎች በአምስት አመት ውስጥ አንድ ሚሊዮን ቤቶች እንዲገነቡ ማድረግን ነው። “የሚሊዮን ቤቶች ፕሮጀክት” የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህን አማራጭ መፍትሄ ለማሳካት፤ በአሁኑ ወቅት ለዘርፉ የሚውለውን መዋዕለ ንዋይ ከሶስት በመቶ ወደ አምስት በመቶ እንደሚያሳድግ ፓርቲው ለከተማይቱ ባዘጋጀው ማኒፌስቶ ላይ ቃል ገብቷል። ከዚህ በተጓዳኝም በደርግ መንግስት አላግባብ ቤታቸው የተወረሰባቸው እና አነስተኛ ካሳ ያገኙ ዜጎች ተመጣጣኝና ተገቢ የሆነ ካሳ እንዲያገኙ እንደሚደረግ በማኒፌስቶው ተገልጿል።

በአዲስ አበባ “በቂ የሆነ የቤት ግንባታ” አለመከናወኑን የሚገልጹት የባልደራስ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ጌታነህ ባልቻ፤ ለዚህ ደግሞ ዋና ምክንያቱ “መንግስት ዘርፉን በሞኖፖል መቆጣጠሩ ነው” ሲሉ በማኒፌስቶው ይፋ ማድረጊያ ስነ ስርዓት ላይ ተናግረዋል። “የከተማዋን የመሰረተ ልማት ችግር ለመቅረፍ ስር ነቀል የሆነ ለውጥ ያስፈልጋል” ብለዋል። 

ባልደራስ ስር ነቀል ካላቸው ለውጦች መካከል፤ ለቤቶች ግንባታ ዘርፍ “ማነቆ ሆኗል” ያለውን የመሬት ፖሊሲ ማሻሻል አንዱ ነው። የከተማዋን የቤት ችግር ለመቅረፍ በአስተዳደሩ ባለቤትነት የሚመራ “የሞርጌጅ ባንክ” ማቋቋም ሌላው ፓርቲው ለመተግበር ያቀደው መፍትሔ ነው። ፓርቲው የውጭ ሀገር ሞርጌጅ ባንኮችም ወደ ከተማዋ የሚገቡበት ሁኔታ ይመቻቻል ሲል በማኒፌስቶው ላይ ጠቅሷል።

የመሰረተ ልማትና ህዝባዊ ግልጋሎቶችን የሚመለከተው የማኒፌስቶው ክፍል ከመኖሪያ ግንባታ ሌላ የትምህርትና ስልጠና፣ ጤና አጠባበቅ እና የህዝብ መጓጓዣን የተመለከቱ የፖሊሲ አቅጣጫዎቹን አቅርቧል። የጤና ኬላዎች እና ጤና ጣቢያዎች ሽፋን መዛባት፤ በጤና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ በዜጎች መካከል ልዩነት ፈጥሯል የሚል አቋም ያለው ባልደራስ፤ ይህንን ለማሻሻል ሊወስደው ያሰበውን እርምጃ በማኒፌስቶው ላይ አመልክቷል። 

ፓርቲው የጤና አገልግሎትን ለሁሉም የከተማይቱ ነዋሪዎች ተደራሽ ለማድረግ በከተማዋ ውስጥ የሚገኙትን ጤና ጣቢያዎች ሙሉ በመሉ ወደ ሆስፒታል የመቀየር ዕቅድ እንዳለው በሰነዱ አስታውቋል። የሚቀየሩት ጤና ጣቢያዎች ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ መስፈርት የሚያሟሉ ሆስፒታሎች እንደሚሆኑም ጠቁሟል። 

በባልደራስ የፖሊሲ አቅጣጫዎች ከተቀመጡት ውስጥ “ምጣኔ ሃብታዊ ትኩረቶችን” የተመለከቱ ጉዳዮች ራሱን የቻለ አንድ ንዑስ ክፍል ተመድቦላቸዋል። “የባልደራስ ተቀዳሚ ዓላማ የኢኮኖሚ ስርዓቱን ለሁሉም በእኩልነት እና በፍትሃዊነት የሚያስተናግድ እና ተጠቃሚ ማድረግ ነው” የሚለው ፓርቲው፤ የኢኮኖሚ መርሁ በውድድር ላይ በተመሰረተ የገበያ ኢኮኖሚ አካሄዶች የሚመራ መሆኑን አስታውቋል። የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ እንዲያብብም አስፈላጊ የሆኑ ድጋፎች ከአስተዳደሩ እንዲያገኙ እንደሚደረግም በማኒፌስቶው ተገልጿል።  

ፓርቲው አዲስ አበባን የምስራቅ አፍሪካ የንግድ፣ ኢንቨስትመንትና ፈጠራ ማዕከል የማድረግ ዕቅድ አለው። ለዚህ ዕቅድ መሳካትም በከተማ አስተዳደሩ ባለቤትነት የአዲስ አበባ ኢንቨስትመንት ባንክን ለመመስረት ወጥኗል። ባልደራስ አዲስ አበባን የማስተዳደር ስልጣን በከተማይቱ ህዝብ ቢሰጠው የሃገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እንዲከፈት ከፌደራል መንግስት ጋር ድርድር ያደርጋል ሲሉ አቶ ጌታነህ ባልቻ በማክሰኞው የማኒፌስቶ ይፋ ማድረጊያ ስነ ስርዓት ላይ ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)