ኢትዮ ቴሌኮም “ቴሌብር” የተሰኘ የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ጀመረ

ኢትዮ ቴሌኮም “ቴሌብር” የተሰኘ የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት መጀመሩን በዛሬው ዕለት ይፋ አድርጓል። የገንዘብ ማስተላለፊያ እና የመገበያያ ዘዴ የሆነው ይሄው አገልግሎት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በተገኙበት ዛሬ ማክሰኞ ግንቦት 3 ምሽት አዲስ አበባ በሚገኘው የወዳጅነት አደባባይ ተመርቋል።

ሃምሳ ሶስት ሚሊዮን የሚጠጉ የተንቀሳቃሽ ስልክ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ያሉት ኢትዮቴሌኮም፤ የ“ቴሌብር” አገልግሎቱን ኢንተርኔት ለሚጠቀሙም ሆነ የድምጽና አጭር አገልግሎት ብቻ ለሚጠቀሙ ደንበኞቹ እንዳቀረበ አስታውቋል።

ከኢትዮ ቴሌኮም የሞባይል አገልግሎት ደንበኞች መካከል 25 ሚሊዮን ያህሉ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች መሆናቸውን የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ በዛሬው የማስመረቂያ መርሐ ግብር ላይ ተናግረዋል። ከእነዚህ የድርጅቱ ደንበኞች መካከል 44 በመቶ ያህሉ የዘመናዊ ስልክ (ስማርት ፎን) ተጠቃሚ መሆናቸው የሞባይል ገንዘብ አገልግሎትን በቀላሉ ለመጠቀም የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)