በቅድስት ሙላቱ
በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች እየተከሰቱ ያሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለመግታት፤ መንግስት አስቸኳይ እርምጃዎች ካልወሰደ የመብቶቹ ቀጣይ እጣፋንታ “በእጀጉ አሳሳቢ” እንደሆነ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ገለጸ። ተቋሙ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች “አደጋ ላይ” ናቸውም ብሏል።
ኢሰመጉ ይህን ያለው ዛሬ ሐሙስ ግንቦት 5 “መፍትሔ የሚሹ የሰብዓዊ መብቶች ጉዳዮች” በሚል ርዕስ ባወጣው ባለ ሶስት ገጽ መግለጫ ነው። የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ በዚሁ መግለጫው በኦሮሚያ፣ በደቡብ እና በአማራ ክልሎች እንደዚሁም በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ግለሰቦች ላይ ተፈጽመዋል ያላቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ዘርዝሯል። ከዚህ በተጨማሪም ከመጪው ምርጫ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን አንስቷል።
በኦሮሚያ ክልል ባለፈው ሚያዝያ ወር በምዕራብ ጉጂ እና በጅማ ዞኖች ላይ በርካታ ንፁሃን ዜጎች መገደላቸውን በመግለጫው የጠቀሰው ኢሰመጉ፤ አምስተኛ ቀኑን ባስቆጠረው የግንቦት ወር ደግሞ ሁለት ሰዎች በታጣቂዎች እና በመንግስት የጸጥታ አካላት መገደላቸውን አስታውቋል። በተመሳሳይ ሁኔታ ባለፈው ወር በአማራ ክልል በምዕራብ ጎንደር ዞን በታጠቁ ኃይሎች በተሰነዘረ ጥቃት የሰዎች ህይወት ማለፉን መግለጫው አንስቷል። በዚሁ ወር በክልሉ ለሰላማዊ ሰልፍ የወጡ ወጣቶች መታሰራቸውንም ገልጿል።
የኢሰመጉ መግለጫ በደቡብ ክልል እና በአዲስ አበባ በግለሰቦች ላይ የተፈጸሙ እስራቶችንም አካትቷል። በሁለቱም ቦታዎች በቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦች የተያዙበት አካሄድ ህግን የተከተለ አለመሆኑን መግለጫው አመልክቷል።
ከምርጫ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በተጨማሪነት የዳሰሰው መግለጫው፤ በተለያዩ አካባቢዎች የምርጫ ጣቢያዎች መቃጠላቸውን በተመለከተ መረጃ እንደደረሰው ጠቅሷል። ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ተፈናቅለው በአማራ ክልል ቻግኒ አካባቢ የሚገኙ ዜጎች የመምረጥ መብትም ምላሽ አለማግኝቱን ጨምሮ ገልጿል።
ኢሰመጉ በመግለጫው ላይ በዝርዝር ላስቀመጣቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የሚሆኑ ዘጠኝ የመፍትሄ ሀሳቦችንም አቅርቧል። መንግስት የግለሰቦችን የመኖር መብት የሚጻረሩ፤ ከፍርድ ውጪ የሆኑ ድርጊቶችን አጣርቶ ህጋዊ እርምጃ መውሰድ አለበት የሚለው ኢሰመጉ፤ ይህ ካልሆነ ግን በቀጣይ ተመሳሳይ ጥሰቶች እንዲፈጸሙ “የልብ ልብ የሚሰጥ” መሆኑን መንግስት ሊረዳው ይገባል ብሏል። መንግስት በህገ ወጥ መንገድ ታጥቀው ንፁሃን ላይ ጥቃት የሚፈፅሙ ኃይሎች ላይ የማያዳግም እርምጃ ወስዶ ዜጎችን ከሰብዓዊ መብት ጥሰት የመጠበቅ ግዴታውን እንዲወጣም ኢሰመጉ በመግለጫው አሳስቧል።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ምርጫን በተመለከተ ባቀረበው የመፍትሔ ሀሳቡ፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ጣቢያዎችን ደህንነት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ማስጠበቅ እንዳለበት ጠቁሟል። ምርጫ ቦርድ የዜጎችን የመምረጥ መብት በአግባቡ መጠበቅ አለበትም ሲል አክሏል።
ኢሰመጉ በመግለጫው መደምደሚያ ላይ፤ መንግስት ከዚህ ቀደም ላቀረባቸው የመፍትሄ ሀሳቦች ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቋል። መንግስትሰብዓዊና ቁሳዊ ጥፋቶች እንዳይደርሱ ኃላፊነቱን ካልተወጣ ግን ተጠያቂ እንደሚሆን ጉባኤው አሳስቧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)