በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር ወድቃ ነበር የተባለችው የቤኒሻንጉል ወረዳ ሰሞነኛ ክራሞት

በቅድስት ሙላቱ

ወጣት ነው። ያለፉትን 23 ዓመታት ያሳለፈው ተወልዶ ባደገባት ዲዛ ከተማ ነው። ይህቺ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሺ ዞን ስር የምትገኝ አነስተኛ ከተማ ቅርብ ጊዜ ድረስ ስሟ በብዙዎች ኢትዮጵያውያን ዘንድ እስከናካቴውም የሚታወቅ አልነበረም። ባለፈው ሚያዝያ ወር አጋማሽ በከተማይቱ እና በአካባቢዋ የተከሰተው ሁነት ግን ከተማይቱን በብዙዎች አፍ እንድትገባ ያደረገ ብቻ ሳይሆን በሀገሪቱ ያለው የጸጥታ ሁኔታ ምን ያህል አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደደረሰ ገሃድ ያወጣ ነበር። 

አነጋጋሪው ክስተት ከተማይቱ የምትገኝበትን የሴዳል ወረዳ በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር ለቀናት እንድትገባ ያደረገ ነው። በሺህዎች የሚቆጠሩ የአካባቢውን ነዋሪዎች ህይወትም እስካሁንም እንዳመሳቀለ ያለው ይህ ክስተት የጀመረው ሰኞ ሚያዝያ 11፤ 2013 ለሊት ላይ ነበር። በዕለቱ ወጣቱን ጨምሮ በጥልቅ እንቅልፍ ውስጥ የነበሩ የከተማይቱ ነዋሪዎች በተደጋጋሚ በሚሰሙት የተኩስ እሩምታ ነበር ከእንቅልፋቸው የነቁት። 

አነጋግ ላይ የጀመረው ተኩስ እኩለ ቀንን ተሻግሮ ወደ ከሰዓት ሲንደረደር፤ ወጣቱ እና ቤተሰቦቹ ከአንድ ውሳኔ ላይ ደረሱ – ከተማይቱን ለቅቆ መሸሽ። ከቀኑ አስር ሰዓት ገደማም ጨርቄን ማቄን ሳይሉ ከተማይቱን ጥለው ወደ አሶሳ አቅጣጫ መሸሽ ጀመሩ። ያኔ ነበር ቀኑን ሙሉ ማየት ባልቻለው ከተማ የደረሰውን ዘግናኝ ጥቃት በወፍ በረርም ቢሆን መመልከት የቻለው። 

“በ100 እና 200 ሜትር ልዩነት ላይ የወደቁ ሰዎች ነበሩ። ግን ይሙቱ ወይ በህይወት ይኑሩ አላረጋገጥኩም ” ይላል ወጣቱ በዚያን ቀን የተመለከተውን መተረክ ሲጀምር። “ከዚህ ቀደም ብዙ ችግሮችን አልፈናል። ይሄ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ የተከናወነ አይመስልም። መሞታችንን እርግጠኛ ሆነን ንስሀ እየገባን ነበር” ሲልም የሁኔታውን አስከፊነት ያስረዳል።

እንደ ወጣቱ ሁሉ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ሌላ የከተማይቱ ነዋሪም፤ በወቅቱ በተመሳሳይ ስሜት ውስጥ እንዳሳለፉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። “ሰዎችን አስረው ይዘው ሲሄዱ ቤት ውስጥ ሆነን እንሰማ ነበር። ሰዎችን ሲወስዷቸው እና መኪናዎችን ሲያቃጥሉ ስናይ ቤት ውስጥ ተንበርክከን መጸለይ ጀመርን” ይላሉ። የከተማይቱ ሁኔታ እየተባባሰ መምጣቱን ሲመለከቱ፤ “በቢላዋ ከመታረድ በጥይት መሞት ይሻላል ብለን ወጣን” ሲሉም መሰደድን በመጨረሻ አማራጭነት መጠቀማቸውን ይገልጻሉ።

“ሰዎችን አስረው ይዘው ሲሄዱ ቤት ውስጥ ሆነን እንሰማ ነበር። ሰዎችን ሲወስዷቸው እና መኪናዎችን ሲያቃጥሉ ስናይ ቤት ውስጥ ተንበርክከን መጸለይ ጀመርን”

– የዲዛ ከተማ ነዋሪ

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በስልክ ያነጋገረቻቸው ሶስተኛ የከተማይቱ ነዋሪም የእኚህን ነዋሪ ገለጻ ያረጋግጣሉ። ከእሳቸው መኖሪያ ቤት አጠገብ ሶስት ሰዎች እንደተገደሉ የሚናገሩት ሶስተኛው ነዋሪ፤ ሁለቱን በስለት አርደዋቸው አንዱን ግቢ ውስጥ በጥይት እንደመቱት እማኝነታቸውን ይሰጣሉ። “የሁለት አመት ልጅ፤ ሬሳ ላይ አስቀምጠዋት ሄዱ” ሲሉም በወቅቱ የነበረውን ዘግናኝ ሁኔታ ያስረዳሉ። 

የመንግስት ሰራተኛ የሆኑ ሌላ የዓይን እማኝ፤ የዲዛ ከተማን ተቆጥጥሮ የነበረው ታጣቂ ኃይል ተኩስ የጀመረው በከተማይቱ ባለው ፖሊስ ጣቢያ ላይ መሆኑን ይገልጻሉ። ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት ጀምሮ ከተማዋ ሙሉ በሙሉ በታጣቂው ቁጥጥር ስር መዋሏን የሚናገሩት እኚሁ ነዋሪ፤ በዕለቱም ቡድኑ የመንግስት መስሪያ ቤቶችን በመቆጣጠር ንብረት ሲያቃጥል መመልከታቸውን ያክላሉ።

ታጣቂዎቹ “በፖሊስ ጣቢያው የሚገኙትን እስረኞች አስመልጠዋል” የሚሉት የመንግስት ሰራተኛው፤ ለብዙ ሰዓታት ከቆየ የተኩስ ልውውጥ በኋላ የክልሉ ልዩ ፖሊስ አባላት ጭምር ሁኔታው ካቅማቸው በላይ በመሆኑ መሸሻቸውን ተናግረዋል። ለደህነንታቸው በመስጋት ከተማውን ጥለው ከወጡት መካከል የሴዳል ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ቤከማ ጉዲና አንዱ ናቸው። 

ጥቃቱ በተሰነዘረበት ወቅት ለ12 ሰዓታት የቆየ “ኃይለኛ” የተኩስ ልውውጥ የሚያስታውሱት አስተዳዳሪው፤ የክልሉ ልዩ ኃይል እና ሚሊሺያ የመከላከል ሙከራ ከአቅም በላይ በመሆኑ ህዝቡን ይዘው መሸሻቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የመከላከያ ሰራዊት ከተማይቱን መልሶ እስኪቆጣጠር ባለው ጊዜ እርሳቸውን ጨምሮ 17 የአካባቢው አመራሮች በጫካ ውስጥ ተሸሽገው መቆየታቸውን አክለዋል። 

ከዲዛ ከተማ 10 ኪሎ ሜትር ርቀት ገደማ ላይ ባለው በዚሁ ጫካ ወደ 15 ሺህ ገደማ የአካባቢው ነዋሪዎች እንደነበሩ አቶ ቤከማ ይገልጻሉ። በሴዳል ወረዳ ላይ የተነዘረውን ጥቃት ተከትሎ ወደ አሶሳ ከተማ እና በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ወደ ምትገኘው መንዲ ወረዳ የገቡትን ጨምሮ ከ25 ሺህ በላይ ዜጎች መፈናቀላቸውን አስተዳዳሪው ተናግረዋል።

ቀያቸውን ለቅቀው ወደ አሶሳ ከተሰደዱት ውስጥ የ23 ዓመቱ የዲዛ ከተማ ነዋሪ ይገኝበታል። ከእህት እና ወንድሞቹ ጋር ከተማይቱን ለቅቀው ከወጡ በኋላ በእግር፣ በመኪና፣ በሞተር ሳይክል እያፈራረቁ አስቸጋሪውን ጉዞ ተወጥተውታል። ወጣቱ በአሶሳ ከተማ አንድ ቀን ካሳለፈ በኋላ አካባቢው ተረጋግቶ መሆኑን ለማጣራት ቢነሳም መጓዝ የቻለው ግን በአሶሳ ዞን ስር እስካለችው ዳለቲ ከተማ ድረስ ብቻ ነበር። “ከዚያ በላይ ማለፍ ያለው ስጋት ከፍተኛ በመሆኑ ተመልሼያለሁ” ይላል ወጣቱ።

ከቀናት በኋላ አካባቢው በመከላከያ ሰራዊት ቁጥጥር ስር መዋሉ መረጃ የደረሰው ወጣቱ፤ ተወልዶ ያደገባትን ከተማ ሁኔታ ለመመልከት ከሌሎች የዲዛ ነዋሪዎች ጋር ባለፈው ሳምንት አርብ ወደ ስፍራው ተጉዟል። እርሱም ሆነ ቤት ንብረታቸውን ለማየት ወደ ወደ ከተማይቱ የሄዱ ነዋሪዎች ግን እንዳሰቡት ወደ ከተማይቱ ወዲያውኑ መግባት አልቻሉም። “የጸጥታ ኃይሎች ካልፈቀዱ በስተቀር መግባት አይቻልም’’ ተብለን ነበር ይላል።

በስተመጨረሻ ተፈቅዶላቸው ወደ ዲዛ ከዘለቁ በኋላ ከተማይቱ ሙሉ በሙሉ በመከላከያ ሰራዊት አባላት ቁጥጥር ስር እንዳለች መመልከታቸውን ይገልጻል። በከተማይቱ በነበረው የሰዓታት ቆይታ በርካታ የተቃጠሉ ቤቶች እና ተሽከርካሪዎችን ማየቱንም ይናገራል። “ከተማው ኦና በኦና ሆኗል” የሚለው ወጣቱ፤ በዚያ ያሉ ነዋሪዎችም ቢሆኑ ከጸጥታ አካላት ፈቃድ ውጪ መንቀሳቀስ እንደማይችሉ ያብራራል። 

የመከላከያ ሰራዊት አባላት በጥቃቱ ወቅት ሸሽተው በአጎራባች አካባቢዎች ተሸሽገው የነበሩ ነዋሪዎችን ሰብስበው በዲዛ ከተማ ውስጥ በሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት ውስጥ እንዳሰፈራቸው ማየቱንም ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድቷል። የነዋሪዎቹን ብዛት በቁጥር መገመት ያልቻለው ወጣቱ፤ በደፈናው “በጣም ብዛት ያላቸው ናቸው” ሲል ይገልጻቸዋል። 

የሴዳል ወረዳ አመራሮች በአሁኑ ሰዓት በመከላከያ ካምፕ ውስጥ እንዲቆዩ መደረጋቸውን የሚናገረው ወጣቱ፤ “ወዴትም እንዳይወጡ ሲጠበቁ ነበር’’ በማለት የተመለከተውን አጋርቷል። ከሴዳል ወረዳ አስተዳዳሪ በስተቀር ሌሎቹ መንቀሳቀስ አይችሉም የሚለው ወጣቱ ምክንያቱን ግን ማወቅ እንዳልቻለ ይናገራል።

የመከላከያ ሰራዊት ከዲዛ ከተማ ባሻገር በአቅራቢያው የሚገኙ የቲንጋ እና መርሾ ቀበሌዎችንም ጨምሮ ቢቆጣጠርም የታጠቁት ኃይሎች ግን አሁንም ቤኒሻንጉል ጉሙዝን ተሻግረው ጥቃት መሰንዘራቸውን እንደቀጠሉ ያስረዳል። ከሴዳል ወረዳ እና ከአካባቢው የሸሹት ታጣቂዎች ባለፈው ሳምንት በምዕራብ ወለጋ ዞን መነሲቡ ወረዳ፤ ዳንጊ ቀበሌ በመግባት የአራት ሰዎች ህይወት እንዳጠፉም በማስረጃነት ይጠቅሳል። 

የሴዳል ወረዳ የምትገኝበት የካማሺ ዞን የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቦካ አቦሴ ታጣቂዎቹ ወደ ሌሎች ቦታዎች መሸሻቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። “የሴዳል ወረዳን የመከላከያ ሰራዊት ከተቆጣጠረ በኋላ በአካባቢው ጥቃት ሲያደርስ የነበረው ኃይል ወደ አጎራባች የገጠር ቀበሌዎች እና ጫካዎች እንዳፈገፈጉ መረጃ ደርሶኛል” ብለዋል ኃላፊው።

“የታጣቂው ኃይል ርዝራዦች በየጫካው እየተሽሎኮሎኩ ጥቃት አያደርሱም ማለት አይቻልም”

አቶ አብዮት አልቦሮ- የቤኒሻንጉል ጉሙዝ የሰላም ግንባታና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ

ስለ ጉዳዩ የተጠየቁት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ የሰላም ግንባታና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዮት አልቦሮ፤ ተመሳሳይ ምላሽ ሰጥተዋል። የመከላከያ ሰራዊት አባላት በአካባቢው ሰላም እንዲመለስ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሆነ የገለጹት አቶ አብዮት፤ ታጣቂዎቹ ወደ ጫካ መሸሻቸውን ተናግረዋል። “የታጣቂው ኃይል ርዝራዦች በየጫካው እየተሽሎኮሎኩ ጥቃት አያደርሱም ማለት አይቻልም” ሲሉም አክለዋል።   

የዲዛ ከተማን ተቆጣጥሮ የነበረው እና በአካባቢው አሁን ጥቃት መፈጸሙን ቀጥሏል የተባለው የታጠቀ ኃይል በጉሙዝ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉህዴን) ስር ያለ እንደሆነ የአካባቢው ባለስልጣናት ይወነጅላሉ። የሴዳል ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ቤከማ ጉዲና “ቡድኑ አሁን በተባለው ወረዳ ብቻ ሳይሆን ከዚህ ቀደም በመተከል ዞንም ችግር ሲፈጥር ነበር” ሲሉ ይከስሳሉ።

በህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲነት ተደራጅቶ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ሲንቀሳቀስ የቆየው ጉህዴን፤ በዘንድሮው ምርጫ ላይ ለመወዳደር ጭምር ዝግጅት ሲያደርግ የነበረ ነው። ፓርቲው ከ2010 ጀምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ አባላቱ ያለምንም ፍርድ ታስረው እንደሚገኙ በተደጋጋሚ ሲያስታውቅ ቆይቷል። 

ጉህዴን በምርጫ መሳተፍም ሆነ በህጋዊ ፓርቲነት የመንቀሳቀስ ፍቃዱ አደጋ ውስጥ የወደቀው፤ ምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአዲስ መልክ እንዲመዘገቡ ጥሪ ካቀረበ በኋላ ነው። ቦርዱ በተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅ መሰረት መስፈርቶችን አላሟሉም በሚል ከሰረዛቸው ፓርቲዎች ውስጥ ጉህዴን አንዱ ሆኗል። ቦርዱ በጉህዴን ላይ ውሳኔውን ያስተላለፈው ፓርቲው በተደጋጋሚ በሰነዶች ላይ ማስተካከያ እንዲያደርግ ቢነገረውም ያንን መፈጸም ባለመቻሉ መሆኑን በወቅቱ አስታውቆ ነበር። 

የአካባቢው ባለስልጣናት በሴዳል ወረዳ ለደረሰው ጥቃት የጉህዴን ታጣቂዎች ላይ ጣታቸውን ቢቀስሩም የዲዛ ከተማ ነዋሪዎች ግን ተጠያቂነቱን ወደ ራሳቸው ባለስልጣናቱ ያዞራሉ። የ23 ዓመቱ ወጣት በዲዛ ጥቃቱን ከፈጸሙት ውስጥ “አንዳንዶቹ አብረን ያደግን ልጆች ናቸው” ይላል። አብዛኞች ታጣቂዎች የአካባቢው ነዋሪ መሆናቸውም የሚናገረው ወጣቱ፤ በወረዳው በኃላፊነት ቦታ ላይ ከነበሩ አመራሮች ውስጥ አብዛኞች “በጥቃቱ እጃቸው አለበት” ሲል ይወነጅላል። 

በዲዛ ከተማ የመንግስት ሰራተኛ የሆኑት ነዋሪ በበኩላቸው የመከላከያ ሰራዊት ወደ ቦታው ላይ ከገባ በኋላ በቁጥጥር ስር ከዋሉ ሰዎች መካከል የሴዳል ወረዳ ሰላም ግንባታ እና ጸጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አንዱ መሆናቸውን በማስረጃነት ይጠቅሳሉ። ኃላፊው “የሽፍታውን ጦር እየመራ ስለነበር በቁጥጥር ስር ውሏል” ሲሉ ነዋሪው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። 

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ የሰላም ግንባታና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዮት አልቦሮ ግን እስካሁን በቁጥጥር ስር የዋሉ አመራሮች የሉም ሲሉ አስተባብለዋል። የአካባቢው አመራሮች በጥቃቱ እጃቸው ይኖርበት ወይም አይኖርበት እንደው የሚረጋገጠው ከዚህ በኋላ በሚደረግ ምርመራ እንደሆነም ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)